×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
ወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት

ወሲብና የፍቅር ጓደኛ ፍለጋ

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በሪቻርድ ፐርነል

ዶክተር ብራንድት “Collegiate Challenge” በሚለው መጽሔት በጻፉት መጣጥፍ ላይ « በማማከር አገልግሎታቸው ውስጥ አንድ የተገነዘቡትን ነገር አስፍረዋል። ይኸውም ብዙ ጊዜ ሁለት የፍቅር ጓደኛሞች እሳቸው እኔ ጋ ምክር ፍለጋ ሲመጡ እንዲህ ይላሉ፡-« በመጀመሪያ ወሲብ ስንፈጽም እጅግ በጣም አስደሳች ነበር፤ ጥቂት ቆይቼ ስለሆነው ነገር ሳስብ ስለራሴ መላቅጡ የጠፋና የንዴት ስሜት ተሰማኝ። በጣም በጸጸት ተሞለሁ። ጥቂት ቆይቼ ስለ ፍቅር ጓደኛዬ የተሰማኝ ስሜትም ደስ የማይልና ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ሆነ። ከዛም ጥቂት ቆይተን እርስ በርሳቸን መጨቃጨቅና አልፎ ተርፎም መጣላት ጀመርን፤ በመጨረሻም ተጣላን፣ አሁን ጠላቶች ሆነናል። ብለው ይነግሩኛል። » በማለት ልምዳቸውን በመጽሔቱ ላይ አስፍረው ነበር።

ይህንን ዓይነት የሥነ ልቡና በሽታ የንጋት በሽታ ብዬዋለሁ። ከእንቅልፋቸን ብንን ብለን ከመኝታችን ስንነሳ ያ ፍቅርና መቀራረብ ዕውነት እንዳልሆነና በቦታውም እንደሌለ እንረዳለን። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የወሲብ ግንኙነት ደስታን የሚፈጥርልን ነገር አይሆንም። መጨረሻው እንደጠበቅነው አይሆንም። የሚሆነው ነገር ምንድነው ? ሁለት የራሳቸውን ርካታ ብቻ ማዕከል ያደረጉ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሰዎች የየራሳቸውን ርካታ በመፈለግ ዓላማ ብቻ ተቀራርበው የሚከወነውን ነገር ፈጽመው ተለያዩ ማለት ነው። የሆነው ታሪክ ከዚህ ውጭ አይደለም። እውነተኛ ፍቅርና ከልብ የሆነ መቀራረብ በአንድ አፍታና በለብለብ የሚገኝ ነገር አይደለም። ስለዚህ በዚህ አካሄድ ሚዛናዊና የተጣጣመ ፍለጋ ስለማይካሄድ ትርፉ የልብ ስብራትና ሃዘን አልፎም ተርፎም ለመጥፎ የሥነልቡና ቀውስ መጋለጥ ይሆናል።

የፍቅር ጓደኝነት በአካል ከመቀራረብ የላቀ ነው።

የእያንዳንዳችን ሕይወት አምሥት በውል የታወቁ ክፍሎች አሉት። እነርሱም አካላዊ፣ ስሜታዊ ፣ ሕሊናዊ ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ናቸው። እነዚህ አምሥቱም የሕይወታችን ክፍሎች እርስ በርሳቸው ልክ እንደጠንካራ ገመድ ተሸራርበውና ተጣጥመው እንዲሰሩ ተደርገው ነው የተፈጠሩት። በፍቅር ጓደኝነት ፍለጋ እንቆቅልሻችን ዛሬ ወይም ቢቻል ትላንት እንዲፈታ እንፈልጋልን። ከችግሮቻችን መካከል አንደኛው የአንድ አፍታ ርካታን አጥብቀን መፈለጋችን ነው። ስለዚህ የፈለግነው ለአፍታ የምንረካበት መንገድ ወይም መፍትሄ እንጂ እውነተኛ የፍቅር አይደለም። ካሉን አምሥት የስብዕናችን ክፍሎች ውስጥ አንዱን ብቻ ነው መርጠን መልስ ልንሰጠው የቻልነው። የአካላችንን ፍላጎት ብቻ ነው ማስተናገድ የቻልነው። ችግሩ ደግሞ ከማንም ጋር በአካል ብቻ እጅግ በጣም የቀረበ ግንኙነትን በቀላሉ መፍጠር የሚቻል ቢሆንም በሌሎቹ በአራቱ የስብዕናችን ክፍሎች ግን እንዲህ በቀላሉ የምንከውነውና እንደ ገለባ እሳት አንድደን የምናጠፋው ዓይነት አይደለም። ከአንድ ሰዓት ወይንም ከግማሽ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ተቃራኒ ጾታ ጋር ተቀራርበህ አካላዊ ውህደት መፍጠርና መቋጨት ትችላለህ፤ ። ነገሮችህን በዚህ መልክ ከቋጨህ በኋላ በደቂቃዎች ውስጥ ወሲብ ለውጭያዊ ፍላጎት ጊዜያዊ ማስተንፈሻ ብቻ እንደሆነ ትረዳለህ። አሁንም ደጋግሞ እንዲገባን የሚያስፈልገው ዕውነተኛ የፍቅር ጓደኝነት ከዚህ በላቀ ሁኔታ በሂደት ውስጥ አልፎ የሚገኝ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።

ለመሆኑ ደጋግማችሁ ወሲብ ካደረጋችሁ ፍላጎታችሁ የሚቀንስ ይመስላችኋል? ምናልባት « ፍቅር ስለያዘኝ ነው? » ትሉ ይናል። ውስጣችሁ ግን ባለመርካት ይታመስና ሕሊናችሁም በከባድ ጸጸት ውስጥ ይወድቃል። ኮሌጆች ውስጥ የሚገኙ አያሌ ተማሪዎች እወነተኛ ፍቅር ጓደኛ ፍለጋ ከአንዱ ግንኙነት ወደሌላው ሲባዝኑ አስተውያለሁ። እየባዘኑ እያለ በእያንዳንዳቸው ግነኙነታቸው ውስጥ ራሳቸውን፡- « ይህ እንግዲህ የመጨረሻውና ትክክለኛው ምርጫዬ ነው ፤ አሁን ግን አግኝቻታለሁ ። አሁን በቃ የነፍስ አጋሬን አግኝቼዋለሁ» ይላሉ።

እኔ እንደማምንበት ለፍለጋ የምንባዝነው ለወሲብ ሳይሆን ፍቅርን ፍለጋ ነው።

ዛሬ የፍቅር ጓደኝነት ማለት የወሲብ ጓደኝነት የሚለውን ትርጉም ይዞ ነው የተገኘው። ሆኖም ግን የፍቅር ጓደኝነት ትርጉሙ ከዚያ እጅግ ያለፈ ነው። የፍቅር ጓደኝነት ሕይወታችንና የስብዕናችን ክፍሎች ያካትታል፤ - አዎ ! አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ሕሊናዊ፣ ማህበራዊና መንፈሳዊ ስብዕናችንን ይጨምራል። እውነተኛ የፍቅር ጓደኝነት ማለት ሕይወትን አንድም ሳያስቀሩ ማካፈል ማለት ነው። ታዲያ ሁላችንስ ብንሆን አንድም ሳናስቀር ህይወታችንን ለሌላው የማካፈል ስሜት ውልብ አላለብንም?

ፍቅርን ባሰብን ቁጥር የሚያስበረግገን ፍርሃት ምን ይሆን?

ማርሻል ሆጅ የተባለ ሰው በፍቅር ላይ ያለህ ፍርሃት የሚል መጽሐፍ ጽፏል። በመጽሐፉ ውስጥ እንዲህ ብሏል፡- « ሁላችንም ፍቅርን ስለመግለፅ እናልማለን፣ ለነፍስ አጋራችን ቅርበታችንንና የምንገልፅበት ቀን እንናፍቃለን። ሆኖም ወሳኝ በሆነ ወቅት እውነትም ፍቅራችን በተግባር የሚገለጽበት ደረጃ ላይ ስንደርስ ማጣፊያው ያጥረንና ማፈግፈግ እንጀምራለን። የተቀኘንለትና ያደናነቅነውን ፍቅር መልሰን እንፈራዋልን። መቀራረብን እንሸሸዋለን። » ። በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ሆጅ እንዲህ ሲል ቀጠለ፡- « አንድን ሰው ይበልጥ በቀረብከው ቁጥር በዛው ልክ ይዞት የሚመጣውም መዘዝና የሚያሳዝንም ነገር መፈጠሩ በዛው ልክ የመጨመር ዕድሉ የሰፋ ነው። » ። ለዚህም ነው ይህንን ህመምና ሃዘን ከመፍራታችን የተነሳ ከትክክለኛ የፍቅር ጓደኝነት ስናፈገፍግና ከአንዱ ወደ አንዱ ስንባዝን የምንኖረው።

በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተከታታይ ትምህርት አስተምር ነበር። አንድ ቀን ከትምህርቴ በኋላ አንዲት ሴት ወደ እኔ መጥታ « ስለ ወንድ የፍቅር ጓደኛዬ አንድ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ። » ስላለችኝ አንድ ቦታ አረፍ ብለን ስለደረሰባት ችግር አወጋችኝ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እንደዚህ አለችኝ። « እኔ አሁን ከዚህ በኋላ እንደገና መጎዳት ስለማልፈልግ የማያዳግም እርምጃ ወስጃለሁ።» አለችኝ። እኔም ተቀብያት « በሌላ አባባል ዳግመኛ በፍቅር ላለመውደቅ ወይንም ዳግመኛ ላለመውደድ የማያዳግም እርምጃ ወስደሻል ማለት ነው። » አልኳት። ትክ ብላ ተመለከተችኝና የነገረችኝን ያልተረዳኋት መሰላትና ፣ በመቀጠል እንዲህ አለች፡- « እንደዚያ ማለቴ አይደለም፤ ሁለተኛ ራሴን ለጉዳት አሳልፌ አልሰጥም ነው እያልኩ ያለሁት ። ከዚህ በኋላ የልብ ስብራትን የሚያስተናግድ አቅም የለኝም።» አለችኝ። እኔም ፡-« ገባኝ እንግዲህ በሕይወትሽ ፍቅር አትፈልጊም ማለት ነው ። » አልኳት ። አያችሁልኝ ህመምና የሌለው ፍቅር የለም ማለት ነው። ወደ አንድ ሰው ይበልጥ በተጠጋችሁ ቁጥር የበለጠ ለልብ ስብራት የመጋለጥ ዕድላችሁ የሰፋ ነው ።

እናንተም ቢሆን ከዚህ በፊት በነበራችሁ የፍቅር ጓደኝነት ተመሳሳይ ልምምድ ውስጥ ገብታችሁ እንደነበር እገምታለሁ ። ዋናው ጥያቄ ግን በፍቅር የተነሳ ተመሳሳይ በሆነ የልብ ስብራት ውስጥ ማለፋችሁ ሳይሆን ያንን የልብ ስብራት በምን ዓይነት ሁኔታ አስተናገዳችሁት የሚለው ነው። የልብ ስብራታችሁን ለመደበቅ ብዙዎቻችን እኔ አሁን መንታ ምልክት ብዬ የምጠራውን አቋም ታንጸባርቃላችሁ። እንዲህ በማለት፤- « እኔ አንተ ወይንም አንቺ እንድትቀርበኝ ወይም እንድትቀርቢኝ እፈልጋለሁ፤ መወደድም እፈልጋለሁ፤ ሆኖም ትንሽ ጊዜ መውሰድ እፈልጋለሁ፤ ከዚህ በፊት ጉዳት ደርሶብኛል፤ ስለጉዳዩ ላነሳ አልፈልግም ተከድኖ ይብሰል፤ ያሳለፍኩትንና እነዚያን ድምጾች ደግሜ መስማት አልፈልግም። » እንላለን። ስለዚህ የልባችንን ቅጥር ልክ እነደቻይናው ግንብ ዙርያውን ገንብተን ሌላ ሰው እንዳይጎዳውና እንዳይሰብረው ከፍተኛ ጥንቃቄ ለማድረግ እንሞክራለን። ከውጭ የሚመጣ ጥቃት እንከላለከልበታለን ብለን ያጠርነው ግንብ እኛኑ መልሶ ልባችንን ወህኒ ውስጥ እንደገባች ወንጀለኛ ጠፍንጎ አስሮ በመጨረሻ ውጤታችን ምን ይሆናል? የብቸኝነት በሽታ ይጸናወተንና የፍቅር ጓደኝነት ለእኛ እንደናፈቀን እንቀራለን።

ይህ አይነቱ ፍቅር በሕይወታችሁ ቢገጥማችሁስ?

ፍቅር ከስሜት በላይ ነው፤ እንደዚሁም ከመልካም ስሜትም በላይ ነው። ሆኖም ማህበረሰባችን እግዚአብሔር አምላክ ፍቅርን፣ ወሲብንና የፍቅር ጓደኝነትንም አስመልክቶ የሰጠውን ብያኔ ለውጦና አዛብቶ በቀላሉ ወደ ስሜትና ፍላጎት ላይ ብቻ ወስኖ አስቀመጠው። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እግዚአብሔር ፍቅርን አስመልክቶ በሚገባ ዝርዝር መግለጫ ነው የሰጠው። በተለይ በ 1ኛ ቆሮንቶስ መልዕክት በ13ኛው ምዕራፍ ውስጥ። እግዚአብሔር ስለፍቅር የሰጠውን ወሰነ ትርጉም በደንብ እንዲገባን በመልዕክቱ ውስጥ 4 እስከ 7 ድረስ ያሉትን ቁጥሮችን በዝርዝር እንድንመለከታቸው እፈልጋለሁ። (1ኛ ቆሮ 13፥4-7) እግዚአብሔር እንዳስቀመጠው እንደ እግዚአብሔር ሃሳብ አንድ ሰው ቢያፈቅራችሁ ወይንም እናንተም ብታፈቅሩትና የፍቅር ጓደኛችሁ፡-

  • ታጋሽ ፣ ቸርና የማይቀና ቢሆንስ ወይም ብትሆንስ?
  • የማይታበይና የማይመካ ቢሆንስ ወይም ብትሆንስ?
  • የማይገባውን የማያደርግና ራስወዳድ ባይሆንስ ወይም ባትሆንስ?
  • ስህተትን ወይም በደልን የማይቆጥር ቢሆንስ ወይም ብትሆንስ?
  • ከእውነት ጋር ሁሌ ደስ የሚለው የማያታልል ቢሆንስ ወይም ብትሆንስ?
  • ስለአንተ ወይም ስለአንቺ ሁሌ መልካም የሚያስብ ፣ የሚያምንሽ ወይንም የምታመኚው ፣ ካንቺ ወይንም ካንተ ጋር መጋጨት የማይፈልግ ወይንም የማትፈልግ ቢሆንስ ወይንም ብትሆንስ?

በፍቅር ጓደኝነት ውስጥ ልንለማመድ የሚገባውን ፍቅር እግዚአብሔር የሰጠን ይህንን ዓይንት ፍቅር ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር ለሌላው ሰው ትኩረት የሚሰጥ ፍቅር እንደሆነ ማስተዋል ትችላላችሁ። መስጠት እንጂ መቀበልን ዓላማው ያላደረገ ፍቅር ነው። ከዚህ ውጭ መኖር ስንፈልግ ያኔ ችግር ቢፈጠር ምን ይደንቃል!

በዚህ መልክ ለመውደድ አስቀድመን መወደድ ሊሰማን ይገባናል

በፍቅር ጓደኝነት ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለመለማመድ አስቀድመን የእግዚአብሔርን ፍቅር ልንለማመድ ይገባል። እግዚአብሔር ለእርሱ ያለውን ፍቅር ሳይለማመድ ማንም ሰው እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለሌላው ሰው ሳያቋርጥ ማሳየትና መለማመድ አይችልም። አንተን የሚያውቅህና ስለአንተ ሁሉንም ነገር የሚያውቀው እግዚአብሔር ፍጹም በሆነው ፍቅር ይወድሃል።

እግዚአብሔር አምላክ በነቢይ በኤርምያስ በኩል እንዲህ ተናግሯል። « እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ።»1 ከዚህ መልዕክት የእግዚአብሔር ፍቅር የማይለወጥና ዘላለማዊ እንደሆነ እንረዳለን።

እግዚአብሔር አምላክ እኛን የወደደን አንድያ ልጁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ከኃጢአታችን እንነጻ ዘንድ ስለ እኛ ኃጢዓት ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስኪሞት ድረስ ነበር።(በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መገደል በጥንት ጊዜ የነበረ የቅጣት ዓይነት ነው።)በእግዚአብሔር ቃልም በዮሐንስ 3፥16 ላይ « በእርሱ የሚያምን ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና። »2 ተብሎ ተጽፏል። ወደ እግዚአብሔር ስንመለስና ምህረቱን ስንቀበል፥ የእርሱን ፍቅር መለማመድ እንጀምራለን።

« . . . በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። . . .»3 በማለት ይናገረናል። እግዚአብሔር አምላክ ኃጢዓታችንን ይቅር ማለት ብቻ ሳይሆን ፣ አስከመጨረሻው ያነጻናል ዳግመኛም አያስታውሰውም።

በዚህ ዓይነት ፍቅር መወደድ ምን ይመስላል?

በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እግዚአብሔር አምላክ እኛን መውደድ አያቋርጥም። ብዙ ጊዜ ጓደኝነት ወይም የፍቅር ግንኑነት በውስጡ አንድ ነገር ሲለወጥ እንደቀድሞው መቀጠል አይችልም። ለምሣሌ አደጋ ሲደርስ፥ የገንዘብ እጥረት ሲገጥምና የአቅም ማነስ ሲከሰት የቀደመው ፍቅር እንደበረታ መዝለቅ ይሳነዋል። የእግዚአብሔር አምላክ ፍቅር በአቋማችን ወይም በማንነታችን ላይ የተመሰረተ አይደለም።

እንደተመለከታችሁት የእግዚአብሔር አምላክ ፍቅር ማህበረሰባችን እንዲህ ነው ብሎ ከሚገልጽልን ፍቅር የተለየ ነው። ለመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ፍቅር ይኖራል ብላችሁ ትገምታላችሁ? እግዚአብሔር በቀላሉ ፍቅሩንና ምህረቱን በመጠየቅ ብቻ እንደሚሰጠን ይነግረናል። ለእኛ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው። ነገር ግን የእርሱን ስጦታ ለመቀበል ባንፈልግ፥ እኛው ራሳችን ነን ከእርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያልፈለግነው፤ ለሕይወታችን ዕውነተኛ ዓለማ እንዳይኖረን ያደረግነው እኛው ነን ማለት ነው።

የእግዚአብሔር ፍቅር መልስን ይሰጠናል። እኛ ማድረግ የሚጠበቅብን ዕምነትና ቁርጠኝነትን ለርሱ እንደምላሽ ማቅረብ ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በዮሐንስ 1፥12 ላይ ስለ ኢየሱስ «. . . ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤. . . »4 በማለት ይገልጽልናል ።

እግዚአብሔር አምላክ አንድያ ልጁን በእኛ ፈንታ ይሞት ዘንድ ወደ ዓለም ላከው። ሆኖም ታሪኩ በዚያ ላይ አላቆመም። ከሦስት ቀንም በኋላ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። እርሱ አምላክ ነውና ዛሬም ሕያው ነውና በልብህ ፍቅሩን ሊያሳድር ይሻል። አንድ ጊዜ እርሱን ተቀብለኸው ካመንክ በኋላ በሕይወትህ የምታየው ለውጥና ከሌሎችም ጋር ያለህ ግንኙነት መለወጥ አንተኑ መልሶ ያስደንቅሃል።

የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል።- « . . . በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። . . .»5 እግዚአብሔር አምላክ ለእኛ እንዲሆን የሚፈልገው የዛሬን ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሕይወትን እንድናገኝ ነው። ይህንን ለመቀበል ካልፈለግን ፥ ምርጫችን የሚሆነው የኃጢዓት ዋጋ የሆነው ሞትና ከእርሱ ለዘላለም መለየትን ነው ማለት ነው።

የእግዚአብሔርን ፍቅር ማወቅ ጥቅሙ ምን ይሆን?

ጌታን እንደ ግል መድኃኒታችን አድርገን ተቀብለን በእርሱ ታምነን መኖር ስንጀምር ሕይወታችን ሚዛኑን የጠበቀ ይሆናል። በእግዚአብሔር መታመን ማለት ከእግዚአብሔር ያልተገደበ ይቅርታን ያስገኝልናል። ተደብቀን ወደራሳችን መንገድ መሄድ አይኖርብንም። እርሱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው። በእርሱ ሰላም አለን። ዕምነታችንን አንድ ጊዜ በእርሱ ላይ ካኖርንና በእርሱ ከታመንን በኋላ፥ እርሱም ውስጣችንን መኖርያው አድርጎ በመቀመጥ የበለጠ ወደ እኛ ጋር ይቀርባል። ከኃጥዓት ሊያነጻን ፣ አስሮ ከያዘን ራስወዳድነት ሊፈታን፣ በየጊዜው ከሚገጠሙን ተግዳሮቶችና የሕይወት ትግሎች ነጻ ሊያወጣን ምህረቱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ስንመለከት እግዚአብሔር አምላክ ወሲብን አስመልክቶ ያለው አቋም ግልጽ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ወሲብን የፈቀደው ለጋብቻና ለጋብቻ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይህን ድንጋጌ ያስቀመጠው እኛ ደስተኞች እንዳንሆን ስለሚፈልግ አይደደለም፣ ልባችንን ከስብራት ሊጠብቅ እንጂ። ጽኑ የሆነ መሠረት ሊያኖርልን ስለሚፈልግ ነው። ስለዚህ ወደ ጋብቻ ሕይወት ስንገባ ግንኙነታችንና ፍቅራችን እግዚአብሔር አስቀድሞ በውስጣችን በገነባው በፍቅርና በጥበብ መሠረት ላይ የጸና ይሆናል።

ማንነታችንን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ አሳልፈን ስንሰጥ፣ አዲስ ፍቅርና ኃይል በየዕለቱ ይሞላናል። ይህ እንግዲህ ከፍቅር ጓደኝነት ስንፈልገው የነበረው ርካታን ማለት ነው። እግዚአብሔር አምላክ በቀላሉ የማይቋረጥ ፍቅር ይሰጠናል። እርሱ የሚሰጠን ፍቅር በዓመታት መካከል የሚጸናና፣ በየጊዜው የማይለወጥ ፍቅር ነው። የእርሱ ፍቅር እርሱን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሁለት ሰዎችን ወደ አንድ የሚያመጣ ፍቅር ነው። በእጮኛምነት አብራችሁ በምታድጉበት ጊዜ ዕድገታችሁ መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን፣ ማህበራዊ ፣ ሕሊናዊና ፣ ስሜታዊ ይሆንና ለፍቅር ጓደኞቻችሁ ታማኝ ከመሆናችሁም በላይ ለፍቅረኞቻችሁ የምታስቡና የምትንከባከቡ ሆናችሁ የፍቅር ጓደኞቻችሁን የምታስደንቁ ትሆናላችሁ። ፍቅራችሁም በጋብቻ ድምዳሜ ሲያገኝ በወሲብ ግንኙነታችሁ ቀድሞ ስትገነቡት የነበረውን መሠረት የበለጠ ታሳድጉታላችሁ።

የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማወቅ ከኛ ምን ይጠበቃል?

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል መድኃኒትህ አድርገህ በጸሎት መቀበል ትችላለህ። ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው። እግዚአብሔር አምላክ ልባችንን ስለሚያውቅ በአንደበታችን ከምንናገረው ቃላት ጋር አይደለም፤ እርሱ የሚመለከተው ልባችንና የውስጥ ዝንባሌያችንን ነው። የሚከተለው ጸሎት እንዴት እንደምትጸልይ ሃሳብ ይሰጥሃል። « ጌታ ኢየሱስ ሆይ ታስፈልገኛለህ፤ ስለእኔ ኃጢዓት ስትል በመስቀል ላይ ስለሞትክልኝ አመሠግንሃለሁ። የሕይወቴን በር ከፍቼልህ አዳኜ አድርጌ እቀበልሃለሁ። ኃጢዓቴን ይቅር ብለህ የዘላለም ሕይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሕይወቴን ተቆጣጠርና አንተ የምትፈልገው ሰው ዓይነት አድርገኝ። አሜን። »

ለመሆኑ ይህ ጸሎት የልብህን ፍላጎት ይገልጻል? መልስህ አዎ ከሆነ፤ ይህንን ጸሎት አሁኑኑ እንድትጸልይ እመክርሃለሁ። ዕምነትህን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማድረግ እንደተስፋ ቃሉ መሰረት እርሱም ወደ አንተ ሕይወት ይመጣል። ይህ ሂደት የበለጠ እያደገ ለሚሄደው ከእርሱ ጋር ለሚኖርህ ግንኙነትና እርሱን የበለጠ ለማወቅ መልካም ጅማሬ ይሆናል። በሕይወትህ ውስጥ በሚኖረው ማዕከላዊው ሥፍራ፣ ሕይወትህ በተለያየ አቅጣጫ ማለትም መንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊው በመጣጣም ግንኙነቶችሁ ሁሉ ስኬታማ ይሆናሉ።

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ኤር 31፡3 (2) ዮሐንስ 3፡16 (3) 1ኛ ዮሐንስ 1፡9 (4) ዮሐንስ 1፡12 (5) ዮሐንስ 3፥36


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More