×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
FAQ

ኢየሱስ ለምን ሞተ?

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

ኢየሱስ ስለምን ሞተ? (የኢየሱስ መሞት ፋይዳው ምንድን ነው?) ስለእኛስ መሞት ለምን አስፈለገው?

የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን ሰቀሉት ምክንያታቸውም አምላክ ነኝ ብለህ የስድብ ቃል ተናግረሃል የሚል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ገደሉት፡፡ በእርግጥ ግን ይህንን የማድረግ ሥልጣን ነበራቸውን?

ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ፣ የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር ሞቶ ለአራት ቀናት በመቃብር ውስጥ ቆይቶ ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን በህዝብ ሁሉ ፊት ከሞት አስነሣው፡፡ ደዌንና ህማምን ሁሉ ፈውሷል… ከመወለዳቸው አንስቶ ዐይነ ስውር የነበሩትን፣ ፈጽሞም መራመድ የማይችሉትን እንኳን ፈውሷል፡፡ ኢየሱስ እጅግ በርካታ ተዓምራትን አድርጓል፡፡ በተዓምራቶቹም ምክንያት ከመሰቀሉ ጥቂት ቀደም ብሎ “ተመልከቱ ዓለሙ ሁሉ ተከትሎታል” ብለው ተናግረውለት ነበር፡፡ እርሱ ደግሞ ደጋግሞ ይናገረው የነበረውን መለኮትነቱንና ከአብ ጋር አንድ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ የማይገደብ ኃይልም ነበረው፡፡

በዚህም መሠረት፣ ጅራፉ፣ በራሱ ላይ የተጠመጠመው እሾህ፣ በእጁ አንጓ እና በእግሮቹ ላይ የተቸነከሩት ሚስማሮች አልገደሉትም፡፡ በመስቀሉም ላይ ቀስ በቀስ ታፍኖ አልሞተም፡፡ ኢየሱስ በየትኛውም ሰዓት ከመስቀል መውረድ ይችል ነበር፡፡

ኢየሱስ ሞትን የመረጠበትን ሁኔታ ስንመለከት አንድ ሰው ራሱን ሊያድን የሚችልበት አቅም እያለው ግን ሆን ብሎ ራሱን በውሃ ውስጥ በመዝፈቅ ሰጥሞ መሞትን ምርጫው የማድረግ አይነት ነው፡፡

በዚህ ረገድ ኢየሱስ ዓላማው ግልፅ ነው፡፡ ለእኛ ሲልም ነፍሱን አሳልፎ መስጠትን እንደመረጠም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡” ግን፣ ለምን?

ምክንያቱም ልባችንን ሲያይ፣ ድርጊታችንን ሲመለከት፣ ህመምተኞች፣ የተቸገርን፣ ደካሞች፣ ኃጢአተኞች፣ የታወርን እና የጠፋን ነበርን፡፡ ምንም ባንወድደውም፣ ኢየሱስ ስለ እኛ የሚመለከተው ይህንን ነው፡፡ ይህንን ብቻ ሳይሆን እኛም ደግሞ ስለነዚያ ነገሮች እርሱ ያደረገልንንም እንድንመለከት ያሻል፡፡ እርሱ ድካማችንን አይቶ፣ በሩቅ ቆሞ አልፈረደብንም ወይንም አልረገመንም፡፡ እንደገባችሁ ተወጡት አይመለከተኝም አላለምም ወይንም ችግራችን የማይገባው አልሆነም፡፡ ከእርሱ ጋር ተስማማችሁም አልተስማማችሁም እጅግ ረዳት የሚያስፈልገን ሆነን ይመለከተናል፡፡ እርሱ ለእኛ ያዘጋጀውንም መልካምነት በሙላት መኖር የማንችል፣ ሕይወታችንም የተመሰቃቀለ ሆኖ ይመለከተናል፡፡

ከዚህም ሁሉ ባሻገር፣ በዘላለምም ሞት ከእርሱ ተለይተን በመኖር፣ የዘላለምን ሕይወት ጨርሶውኑ ባለመለማመድ አደጋም ውስጥ ሆነን ያየናል፡፡ በኃጢአታችንም ምክንያት ከእርሱ ተቆርጠን ያየናል፡፡ ስለዚህም (ሞትን በመምረጡ) አነዚህን ሁሉ መሻቶቻችንን ሊያሟላልን ወደደ፡፡

ብናመሰግነውም ባናመሰግነውም፣ ይህ ችግር እንዳለብን ብንረዳም ባንረዳም፣ የሞት ቅጣታቸንን ወሰደ፣ እኛ ልንቀበለው የሚገባንን እርሱ ራሱ ወሰደ፡፡ እንግዲያው እነዚህ ተግባራት ስለ ሰው ግድ የማይለው ሰው ተግባር ሊሆኑ ጨርሶ አይችሉም፡፡

መዳንን የምንሻ፣ ይቅር መባልን የምንሻ፣ መሆናችንን በማመን ይህንን ሁሉ አስደናቂ ርቀት ስለ እኛ ተጓዘ፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንዲያው የፍቅር መግለጫ ለማድረግ ያህል አልተሰቃየም አልሞተምም፡፡ በእርሱ አመለካከት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነበር፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት ለዘላለም ከእርሱ ተለይተን እኛ መሞት አሊያም እኛ በሕይወት እንኖር ዘንድ እርሱ መሞት ነበረበት፡፡ እርሱም መሞትን መረጠ በዚያም እኛ ይቅር ተባልን፡፡ እርሱንም ለዘላለም አወቅነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲገልፀው፣ “ለደግ ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል” ይላል፡፡

ከመሰቀሉ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ፣ የማይቀረውን ሞቱንና ትንሣኤውን ሙሉ በሙሉ በማወቅ፣ ከአባቱ ጋር ሲነጋገር የሚያደርገውን ሁሉ የሚያደርግበትን ምክንያት “አንተ እንደ ላክኸኝና እኔን በወደድኸኝ መጠን እነርሱንም እንደወደድሃቸው ዓለም ያውቅ ዘንድ” በማለት ገልጦታል፡፡

ይህም፣ መዳን ያስፈልገናልን? በእኛ ውስጥ ያለ እኛ የማናየው ኢየሱስ የሚያየው ምንድን ነው? ለመገረፍና ስለ እኛም ለመሞት ወደ መስቀል ለመሄድ መምረጡ ይህ ለምን አስፈላጊ ሆነ?

ምናልባት እኛ የተሳነንን እርሱ ያይ ይሆናል፡፡ ቁጡነታችንን፣ ጥላቻችንን፣ ትዕግሥት ማጣታችንን፣ ልብ ሰባሪ ድርጊቶቻችንን እና ተግባሮቻችንን ሁሉ ማለት ነው፡፡ ሌሎችን እንበድላለን፣ አንዳንድ ጊዜም ሌሎች እኛን ይበድላሉ፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ባቀደልን የመልካምነት ደረጃ ልክ መኖር አንችልም፡፡ እንኳን የእርሱን፣ እኛ ልንኖር ይገባል የምንለውን ያህል እንኳን መኖር አንችልም፡፡ እውነተኞች እንሁን ካልን፣ አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን የሚያሳፍር ድርጊት እንኳን እንፈፅማለን፡፡ እንግዲያው ፍፁም ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር የሚያየው ምንድን ነው?

እኛ አንፈልግህም የማለታችንስ ጉዳይ? በሕይወታችን ጣልቃ እንድትገባ አንፈልግም የማለታችንስ ነገር?

ለምን ትቶን አልሄደም? ለምን ጀርባውን አልሰጠንም?

እኛ የኀጢአታችንን ፍዳ እንድንቀበል ከመተው ይልቅ፣ ትቶን ዘወር ከማለት ይልቅ ወደ እኛ መጣ፡፡ ወደ እኛም ዓለም ገባ፡፡ የኀጢአታችንንም ቅጣት ተቀጣልን እርሱ ራሱም ሞታችንን ሞተ፡፡

“…እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው”

ኀጢአታችንን ለምን ዐይቶ እንዳላየ አያልፈውም፣ በአንድስ ቃል ለምን ምሬአለሁ አይልም? ለእኛ እንዲህ ማድረግ የሚቻል ይመስለናል፣ ነገር ግን እንዲያው ያለዋጋ መደምሰስ ጨርሶ የከፋ ነው፡፡ የኀጢአታችን ብርቱነትና እርሱ ለእኛ ያለው ፍቅር የእርሱን ተግባራዊ ምላሽ ይፈልጋል፡፡

ይህንን ነገር የምንረዳው አንድን ሰው ይቅር በማለት ሂደት ውስጥ ስናልፍ ነው፡፡ ምናልባትም አንድ ሰው በእኛ ላይ ፈፀመ የምንለው የከፋ በደል ሲኖር፣ ያንን ሰው ይቅር ማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው የምንለውን በደል እናስብ፡፡ እንግዲህ ኢየሱስ ይቅር ሊለን የፈለገው ዘላላማዊ ጥልቀት ባለው መንገድ ነው፡፡ የሚፈልገውም ሙሉ በሙሉ ይቅር እንድንባል ነው፡፡ እርሱ የሚፈልገው እኛን ሙሉ በሙሉ ሊቀበለንና ኀጢአታችንም ከእንግዲህ በእኛና በእርሱ መካከል ግድግዳ እንዳይሆንብን ነው፡፡ “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው፡፡”

እርሱ ስለ እኛ ኀጢአት ሞተ፣ ከሦስት ቀናትም በኋላ ሁሉን ድል አድርጎ ከሞት ተነሣ፡፡ እርሱንም ኀጢአትም ሆነ ሞት ሊይዙት አልቻሉም፡፡ እኛም በእርሱ ሆነን ይህንኑ እንድንለማመድ ይፈልጋል፡፡ ወደ እርሱም በመሄድ፣ ይቅር እንዲለንና ወደ ሕይወታችን እንዲገባ በመጠየቅ እርሱ ያዘጋጀልንን ይቅርታ መቀበል የእኛ ውሳኔ ነው፡፡

ዮሐንስ ይህንን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በደንብ ገልጦታል፣ “ስለዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፤ በፍቅሩም እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል፡፡ በዚህም ዓለም እርሱን እንመስላለንና፡፡ በፍርድ ቀን ድፍረት ይኖረን ዘንድ፣ ፍቅር በዚህ ዐይነት በመካከላችነ ፍጹም ሆኗል፤”

ኢየሱስ ክርስቶስን አሁን ወደ ሕይወትህ እንዲመጣ ልትጋብዘው ትወዳለህን? እንግዲያው ይህን ማድረግ የምትችልበት መንገድ እነሆ፡-

“ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ ሕይወቴ እንድትመጣ እለምንሃለሁ፡፡ ኀጢአቴን ይቅር በለኝ፡፡ ስለ እኔ በመስቀል ላይ ስለሞትክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ሕይወቴን አንተ እንደምትፈልገው ምራ፡፡ አሁን ወደ ሕይወቴ ስለመጣህና ከአንተም ጋር ህብረት እንዲኖረኝ ስለፈቀድክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አሜን፡፡”

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More