×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
እግዚአብሔርን ማወቅ

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በመላው ዓለም በታላላቅ ድምቀቶች የሚከበሩ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የሰው ዘሮች የሚያሳትፉ፣ በርካታ በዓላት አሉ። ከነዚህም መካከል በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በነጩም በጥቁሩም፣ በባለጠጋውም በምስኪኑም በተማረውም በመሃይሙም፣ በከተሜውም በገጠሬውም፣ በወጣቱም በአረጋዊውም፣ በወንዱም በሴቱም እንደየ ባህሉና አቅሙ የሚከበረው ክሪስ - ማስ በመባል መጠሪያ የሚታወቀው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል ከፍ ያለውን ስፍራ ይይዛል። ይህ ክብረ በዓል በተለይ በአውሮፓውያኑ ዘንድ ድምቀትን እንዲያገኝ ካበቁት ምክንያቶች አንዱ በዓሉ ከአውሮፓውያኑ የአዲስ ዓመት መግቢያ ጋር የቅርብ ትስስር ያለው መሆኑ ሲሆን፣ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከበዓሉ ጋር ተያይዘው የሚታወሱት የክሪስ ማስ ትሪና ሳንታ ክላውስ ናቸው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህማ የታሪኩ ባለቤት በእነዚህ በሁለቱ ጭራሹኑ እየተሰወረ፣ የታሪኩ ባለቤቶች እየሆኑ መጥተዋል። ስለዚህም ዘመነኛውን ወጣት ስለ ክሪስ ማስ ብትጠይቁት ክርስቶስን ሳይሆን ሳንታ ክላውስን ይተርክላችኋል። ከእርሱ ጋር የጠበቀ ፍቅርና ወዳጅነት እንዳለው፣ በየዓመቱም በናፈቆት እንደሚጠብቀው በደስታ እየተፍነከነከ ያወራላችኋል።

መቼም በዓላት ሁሉ በህዝብ ልብ ውስጥ ሊቀመጡና ሊታወሱ ሚችሉባቸው መታሰቢያዎች ሊኖሯቸው የሚገባ መሆኑ እሙን ነው። ሆኖም መታሰቢያዎቹ ዋናውን ባለቤት ከሰወሩት ግን ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። ስለዚህ የገና ዛፍና ሳንታ ክላውስ ክርስቶስን ሊተኩብንና ዋናውን ሊሰውሩብን አይገባም።

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል እንደተፃፈው አማኑኤል ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። ይህንን ብቻ ስትገነዘቡ ጉዳዩ ከሳንታ ክላውስ አብሮነት ምን ያህል የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው በእጅጉ ትረዳላችሁ። ጉዳዩ እንዲህ ነው። የፍጥረተ-ዓለሙ ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ቀደምት ወላጆቻችንን አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ዘወትር ከእነርሱ ጋር በገነት ይኖር፣ አብሯቸው በአንድነት ያሳልፍ እነርሱም በእርሱ ከእነርሱ ጋር መኖር እጅግ ደስ እየተሰኙ ከእርሱ የተቀበሉትን ምድርን መንከባከብና የመጠበቅ በፍጥረታትም ላይ ባለሥልጣን ሆኖ የመግዛት ተግባራቸውን ያከናውኑ ነበር። በመካከላቸውም ፍፁም ፍቅር ኅብረትና አንድነት ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትተው የሰይጣንን የማታለል ድምፅ በመስማታቸውና እርሱ አታድርጉ ያላቸውን በማድረጋቸው ከዚህ ከሚናፈቅና ከሚወደድ የእግዚአብሔር አብሮነት ተባረሩ። በምድርም ተነከራታችና ተቅበዝባዥ ሆኑ። በፍፁም ደስታ ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነዋሪ መሆናቸውም በሞትና በተገደበ ዘመን ተተካ።

በምህረቱ ባለጠጋ የሆነው እግዚአብሔር ግን ለፍጡሩ ካለው ፍቅርና ርኅራኄ የተነሣ፣ የሰው ልጅ በወደቀበት በዚያው ቅፅበት አንድ ቀን ከወደቀበት አንስቶ ከእርሱ ጋር አብሮ ለዘላለም የሚኖርበትን ሥራ እንደሚያከናውን ተስፋን ሰጠው። የሰውን ልጅ በማታለል ወደ ውድቀት የነዳውን የዲያቢሎስን ጭንቅላት የሚያፈርስ፣ የሰውን ዘር ኃጢአት አስወግዶ በእግዚአብሔርና በሰው ልጅ መካከል የገባውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አዳኝ ከሴቲቱ ዘር እንደሚወጣ ጽኑ ተስፋን ሰጠ። ያም ተስፋ “ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና። ጌታ በነቢዩ (በኢሳያስ) እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈፀም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤ ትርጉሙም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ማለት ነው።”1 በሚለው የወንጌል ቃል ተፈፀመ። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በበደላችንና በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተን የነበርን የሰው ዘር ሁላችን በእርሱ ሥራና መሥዋዕትነት እንደገና ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድንኖር የተነገረልንን ተስፋ ተፈፅሞ ያየንበት እጅግ የሚወደድና የሚናፈቅ የድል ቀናችን ነው።

ከድንግል መወለዱና አባቱ እግዚአብሔር አብ መሆኑ ከሴቲቱ ዘር ሚወጣው ያለምንም አዳማዊ የወንድ ዘር ንክኪ ፍፁም ንፁህ ሆኖ የሰውን ዘር ኃጢአት ሊያስወግድ የሚችል አዳኝ የመሆኑን የተስፋ ፍፃሜ ያመለክታል። ፍፁም ሰውነቱ ደግሞ የሰው ዘር ምትክ ሆኖ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ለመመመለስ ብቃት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል። እንግዲህ ይህንን ትልቅ የድነታችንንና የደስታችንን የምሥራች ቀን በጥቃቅን የበዓል መታሰቢያዎች መተካት ነውር ነውና ወደ ዋናው ልባችንን ልንመልስ።

በመንደርደሪያዬ እንዳነሳሁት የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በነጩም በጥቁሩም፣ በባለጠጋውም በምስኪኑም፣ በወንዱም በሴቱም፣ በአረጋዊውም በወጣቱም፣ በጠቅላላው በሰው ዘር በሙሉ መከበሩ አግባብነት አለው። ምክንያቱም “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋልና”2 ተብሎ ስለተፃፈ፣ ሁሉ ለኃጢአታቸው መድኃኒት ያስፈልጋቸዋልና ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው ከሰማየ ሰማያት የወረደውን ከድንግል የተወለደውን ኢየሱስን ሊያስቡ ነፍሳቸውንም አሳልፈው ሊሰጡትና የራሳቸው ሊያደርጉት ይገባቸዋልና ነው። ይህ ሲሆን ግን ጉዳዩ በዓመት አንድ ሰሞን ነገሩን በመታሰቢያነት መዘከር ማለት አይደለም። ይልቁኑ በዚያን ሰሞን የተከናወነው ተግባር የህይወት ጨለማ በብርሃን የተለወጠበት፣ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጠበኝነት በፍቅርና በምህረት የታደሰበት፣ በበደላችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ርቀን የነበርን ወደ እኛ በፍቅር ከመጣው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ የተነሣ ወደ እግዚአብሔር የቀረብን መሆኑን እግዚአብሔርም በአንድያ ልጁ ከእኛ ጋር የሆነበት እለት መሆኑን በማስታወስ ዓመቱን ሙሉ ከእርሱ ጋር በፍጹም ኅብረትና አንድነት ለመኖር ቃል ኪዳናችንን የምናድስበት ሊሆን ይገባዋል።

ይህን ምስጢር የተረዳችሁና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር በልጁ አማካይነት እንዳለ የገባችሁ ሁሉ፣ ኢየሱስ በተወለደባት ሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ የነበሩት እረኞች እንዳደረጉት ሁሉ ከሰማያት በበራው ብርሃንና በተነገራቸው የምሥራች ተነክተው ይህን የገለጠልንን ለሰዎች ሁሉ እንንገር ብለው የምሥራቹን ይዘው እንደወጡ እናንተም ይህንን ለሰው ዘር ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች ለማብሰር ቃል ኪዳናችሁን አድሳችሁ ተነሱ። የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚዘከር ብቻ ሳይሆን የሚመሰከርና ለሰው ሁሉ የሚነገር የሰው ልጅ ትልቅ ዕድል ነው።

ይህን ምስጢር ያልተረዳችሁ ሁላችሁ ደግሞ፣ ይህ የዘንድሮው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መታሰቢያ በዓል ከኃጢአት ሊያድናችሁ የመጣውን ከድንግል የተወለደውን ኢየሱስ ክርስቶስን በግላችሁ የምትተዋወቁበት፣ ራሳችሁን አሳልፋችሁ የምትሰጡበት፣ እርሱም ሠርቶ በፈፀመው ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር የምትታረቁበትና እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ወደምትሉበት ድንቅ ኅብረት የምትገቡበት እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ። ይህንን ትልቅ ዕድል የራሳችሁ ለማድረግ የሚጠበቅባችሁ ከዚህ በታች የተገለጠችውን አጭር ዐረፍተ ነገር በልመና መልክ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ብቻ ነው።

“ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ በአባታችን በአዳም ምክንያት በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የተላለፈው የኃጢአት ዘር በእኔም ውስጥ እንዳለ፣ በዘመኔም ኃጢአትን እንዳደረግሁ አውቃለሁ። ሆኖም፣ አንተ ከኃጢአቴ ልታድነኝ የመጣህ መሆኑን ተረድቻለሁ። በአንተ በማመን ከእግዚአብሔር ጋር በመታረቅ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር የመሆኑን በረከት ላጣጥመው እፈልጋለሁ። በደሌን አስወግደህ የራስህ አድርገኝ። ብርሃንህንም አብራልኝ። ይህ የልደት በዓል የሕይወቴ አቅጣጫ የሚቀየርበት አድርግልኝ።” አሜን።

በፓ/ር እሸቴ በለጠ

 ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) የማቴዎስ ወንጌል 1፡21-23 (2) ሮሜ 3፡23


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More