×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
የህይወት ጥያቄዎች

እግዚአብሔር ብቁ ዳይሬክተር ነውን?

እንዴ ምን እየሆነ ነው? ለምንድነው ከክፋትና ከሥቃይ ነፃ የሆነች ዓለም የማትኖረን?

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

ለምሳሌ አንድ ሰው መጥቶ ምንም ቢሆን በዚህ ምድር ላይ ብቁ ነው የምለው የፊልም ዳይሬክተር እንዳለ አላምንም፤ ምክንያቱም የማያቸው ፊልሞች ሁሉ ፈጽሞ ቀልዶች እንጂ በሚገባ የተዘጋጁና ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም፣ » ቢላችሁስ?

እስቲ ክርክሩን አስፍተን በሌላ አገላለጽ እንመልከተው። ጥሩና ደረጃውን የጠበቀ ፊልም ማዘጋጀት ይቻላል፤ ከሚለው ማዕከላዊ አስማሚ ሃሳብ እንጀምር። ከዚያም በመነሳት በማስፋት እንዲህ ማለት እንችላለን። «ጥሩና ደረጃቸውን የጠበቁ ፊልሞችን ማዘጋጀት እንደሚቻል አስካመንኩ ድረስ፣ ሆኖም ያየኋቸው ፊልሞች ሁሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁና የተዋጣላቸው እስካልሆኑ ድረስ፣ ብቃትና ችሎታ ያላቸው የፊልም ዳይሬክተሮቸ ያሉ አይመስለኝም።» እንግዲህ ይህ ነው የክርክራችን አካሄድ ማለት ነው።

ከእግዚአብሔር መኖርና አለመኖር ጋር በተያያዘ የሚቀርቡት ክርክሮች አካሄዳቸው ይህንኑ ነው የሚመስለው። ሰዎች «ይህ አለም የማያስደስትና አስከፊ ስለሆነ በእግዚአብሔር ህልውና አላምንም።» ሊሉ ይቸላሉ። ይህ ማለት እንደዚህ ዓይነት ዕምነት ያላቸው ሰዎች ገባቸውም አልገባቸውም መልካምና የተሻለች ዓለም እንዳለች ያምናሉ ማለት ነው።

መልካምና የምትመች ዓለም ትኖር ይሆን?

ከሆነስ አዚህች መልካምና የተሻለችው ዓለም እንዴት መድረስ ይቻላል? በዝግመተ ለውጥ አካሄድ ይሆን? በዝግመተ ለውጥ አካሄድ ናሙናዎችን እንደተመለከተው ከሆነ በለውጥ ሂደት ውስጥ ያለ ነገር በየጊዜው መሻሻልን ማሳየት አለበት። የሚል ድምዳሜ አለው። ስለዚህ በዝግመተ ለውጥ ሂደት በቂ ጊዜ ሰጥተን ከጠበቅን ምናልባት በመጨረሻ የተሻሉ ፊልሞችንም ማዘጋጀት እንችላለን። በዚህ አካሄድ ካየነው ዓለምንም በዝግመተ ለውጥ ሂደት እንድታልፍ ካደረግን፣ መሻሻል የሚጠበቅ ውጤት ነው። ነገር ግን ዕውነታው ከዚያ ተቃራኒ ነው። ይኸውም ዓለም ምንም በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ ነች ብለን ብናስብም ያሳየችው መሻሻል ሳይሆን ወደ በለጠ ጦርነት፣ ወደበለጠ ወንጀል፤ ወደበለጠ ፍትህ አልባነት ፣ ወደበለጠ የትዳር ፍች፣ ወደበለጠ ብልሽት ውስጥ ተዘፍቃ ነው ያገኘናት። ይኼንን ይሆን መሻሻል የምንለው? በዚህ ተጠየቅ ውስጥ ከሄድን የቱንም ያህል መሻሻል ቢኖርም ወደፊት ምንም ዓይነት የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ ፊልም ከማዘጋጀት ይለቅ ይበልጥ እየተበላሸና እየወደቀ ይሄዳል ፤ ወደሚለው ድምዳሜ ይደረሳል ማለት ነው።

ምናልባት ይህንን ፍጥጥ ያለውን ዕውነት ነው ለመጋፈጥ የማንወደው፤ እኛ ራሳችንን ቀድሞዉኑ መጥፎ መሪዎች ስለሆንን ዓለምን ወደ መልካምና ምቹነት መምራት አንችልም። እኛ ራሳችን ችግር ያለብን ነን፣ የኃጢዓተኝነት ስብዕና የተጫነን ነን፣ ከዚህ ባህርያችን ብንነሳ ከኛ መልካም ነገር መጠበቅ አንችልም። ድንቅ የሆነ ሥልጣኔና የቴክኖሎጂ ምጥቀት በምድር ላይ የተንሰራፋውን የክፋት ፣ የወንጀል ፣ የስግብግብነት ፣ ታማኝ ያለመሆንን በፍፁም አይቀርፈውም። ዋናው ችግር ያለው በሰው ልብ ውስጥ ነው። የቱንም ያህል በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ ብናልፍም፣ ልባችንን አንበርክኮ ከገዛው ራስወዳድነትና እኔነት መሻሻል አንችልም፤ ተሻሽለናል፣ ከተባልንም ወደበለጠ ራስወዳድነትና እኔነት እናድጋለን እንጂ ከዚያ በተቃራኒ ወደሚገኘው አቅጣጫ እንደምንሄድ አይጠበቅም። የዝግመተ ለውጥ ሂደት ሕግም ተግባራዊ የሚሆነው ብርቱ ደካማውን አሸንፎ ልቆ መገኘትን ስለሚያደፋፍር ከዚህ ውጭ አዲስ መሻሻል የምንለው ነገር አይጠበቅም።

ይህን ዓለም በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች

<ጥያቄ አንድ ብለን ብንጀምር ፣ በውኑ ይህች ዓለም እግዚአብሔርን ደስ የምታሰኝ ነችን? የዚህን መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ፤- «በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በርሱ ውስጥ የለም። »1 ዓለም ለሥጋ ምኞት ነው የሚሮጠው (ይህን ደግሞ ሰብዐዊነቴ የምፈልገው ነገር ነው።) የዓይን አምሮት በዓለም ውስጥ ሞልቷል። (ይሄም ሰብዐዊነቴ በጣም የሚፈልገው ነገር ነው።) ስለገንዘብ መመካት የዓለም ዋንኛ ባህርይ ነው። (ይህንንም በጣም የምፈልገው ነገር ነው።) ታዲያ እነዚህ ዐበይት አጥፊ ጉዳዮች የዓለም ዋንኛ ችግር ናቸው ቢባል ስህተት ነው? ታዲያ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔርን ያስደስታሉ?

ጥያቄ ሁለት ብለን ስንቀጥል ደግሞ ሁሉም ነገር የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ነው ወይ? የሚለው ሲሆን፤ መጽሐፍ ቅዱሰ ያለው መልስ «አዎ» እንዲሁም «አይደለም» የሚለው ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ቻይና ሉአላዊ አምላክ ነው። ሆኖም ለእኛ የምርጫ ነጻነትን ሰጥቶናል። እያንዳንዱን ሃሳባችንንና ተግባራችን እየተከታተለ በእርሱ ምርጫ ብቻ እንድናከናውን አያደርግም። ይህ ነጻነት ነው እንግዲህ መጥፎውን ፊልም ያመጣው። በተጨማሪም የምድር ሁሉ ንጉሥ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ እንደገና መጽሐፍ ቅዱሳችን የተወሰኑ ምክንያቶችን አስቀምጦ የዚህች ዓለም ገዥ ሰይጣን እንደሆነ ይገልጽልናል። እንደዚሁም እግዚአብሔር አምላክ ሉዐላዊ ሆኖ ሳለ፣ መልሶ ለእኛ በራሳችን ላይ ነጻ የምርጫ ውሳኔ እንድናደርግ ዕድሉን ሰጥቶናል።

ጥያቄ ሦስት ስንል ደግሞ ለመሆኑ ይህች ዓለም የእግዚአብሔር መንግሥት ነችን? ብለን እንጠይቃለን። የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ «አይደለችም» ነው የሚለው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ አለ። «የእኔ መንግሥት በዚህች ምድር ላይ አይደለም» አለ። በዚህ ጊዜና ሰዓት የእግዚአብሔር መንግሥት በገሃዱ ዓለም የምትታይ አይደለችምና መንፈሳዊ ነች። ምንም እንኳ እርሱ በሁላችንም ላይ ንጉሥ ቢሆንም፣ ሁላችንም እርሱ በልባችንና በሕይወታችን ይነግስ ዘንድ አልፈቀድንለትም። በስሙ ያመኑ ክርስቲያኖች ግን የማትታየዋ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል ስለሆኑ እግዚአብሔር የእነርሱ ንጉሥ ነው። (ምንም እንኳ በዚህች ዓለም ሥጋ የሚኖሩ ቢሆኑም።)

መልካሚቱ ዓለም . . .

ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘጋጀው ፊልም ገና አልታየም። የተቀጠረለት ጊዜ ሲመጣ «የዚህች ዓለም መንግሥት የመሲሁ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ትሆናለች።» የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ ፊልም ማየት የምንችለው እንግዲህ ያኔ ነው። ከሁሉም የተሻለውን ለብቃቱ እንከን የማይወጣለት ባለሙያ ያዘጋጀው ማለት ነው። እግዚአብሔር የተሻለች ዓለም ህልውና እንድታገኝ በዕቅዱ ውስጥ ነች። ከዚህችኛዋ ዓለም ጋር አንድም አምሳያ አይኖራትም። እርሱ ፍጹም ብቃት ያለው እንከን የማይወጣለት የፊልም ዳይሬክተር ነው። እስቲ የፊልሙን ቅንጫቢ እናሳያችሁ።

«የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው፤ ከእነርሱም ጋር ያድራል። እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል። ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።»2

 ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) 1ኛ ዮሐንስ 2፡15-16 (2) ራዕይ 21፡3-4


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More