×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
ወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት

የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ጋብቻ

«የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።» (ሮሜ 12፡2)

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

የእግዚአብሔር ፈቃድ፡-

1. በጎ ነው። በጎ ማለት ደህና፣ ጤናማ፣ መልካም፣ መጥፎ ያልሆነ ማለት ነው።

2. ደስ የሚያሰኝ ነው። ደስ የሚያሰኝ ማለት ልብ የሚፈልገውን ሁሉ በማግኘት በስሜት መፈንደቅ ማለት አይደለም። የሚያስፈልገንን ከእርሱ ተቀብለን ማረፍ፣ በሰላም መሞላት፣ መርካትና መረጋጋት ማለት ነው።

3. ፍጹም ነው። ፍጹም የሚለውን ቃል ስናስብ ፈጥኖ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ትርጉም እንከን የሌለው የሚል ነው። ብዙዎች በእጃቸው ያለውን ሰው ለትዳር ለመቀበል ሰውየው ወይም ልጅቱ በሁሉም የሰው መመዘኛ እንከን የለሽ መሆን አለበት/ባት ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ፍጹም የሚለው ቃል ትርጉም፡- ሙሉ፣ ያደገ፣ የበሰለ፣ ተቀባይነት ያለው ማለትም ነው። ማንኛችንም አንከን የማይገኝብን ባለመሆናችን እንከን አልባ ሰው ልንጠብቅ አይገባም። ሆኖም በመንፈሳዊ ሕይወቱ/ቷ እንጭጭ ያልሆነ/ች በሳል ሰውና ውስጣችን የሚቀበለው/ላት ብለን ብንተረጎመው በቂ ነው።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ማለት ብዙዎቻችን እንደምናስበው ውስብስብ፣ ከእኛ በጣም የራቀ፣ ልንደርስበት የማንችለው፣ ፈልገን የማናገኘው ነገር አይደለም። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰው ሁሉ ሊረዳው በሚችልበት ልክ የተዘጋጀና ግልፅ ነው።1

የእግዚአብሔር ፈቃድ ማለት፡- የእግዚአብሔር ባሕሪ ማለት ነው። እግዚአብሔር የሚወደውና የሚጠላው ነገር ማለት ነው። ክርስቲያናዊ ጋብቻን በተመለከተ እግዚአብሔር የሚወደውና የሚጠላው ነገር በቃሉ የተገለጠ ነው። ለምሳሌ፡- አማኞች ከክልላችን ወጥተን የማያምኑ ሰዎች ማግባታችን እግዚአብሔርን ደስ አያሰኘውም።2

በቅድስና ራሳችንን ጠብቀን መኖራችን እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።3 ለትዳር ጓደኞቻችን በዘመናችን ሁሉ ታማኞች መሆናችን እርሱን ደስ የሚያሰኘው ነገር ነው።4 እግዚአብሔር ፍቺን ይጠላል።5 ትዳርን ስንመሰርት ከፍቺ አማራጭ ጋር ልንመሰርተው አይገባም።

ክርስቲያናዊ ትዳር በመተው፣ በመጣበቅና አንድሥጋ በመሆን መሠረት ላይ እንዲመሠረት እግዚአብሔር ይፈልጋል።6 እግዚአብሔር ትዳርን ያቀደው ሰዎች መልካም ካልሆነው ብቸኝነት እንዲላቀቁበትና ምቾትና የጓደኝነትን ደስታ እንዲያገኙበት ነው።7 የእግዚአብሔር ፈቃድ፡- ጋብቻ ላይ ስንደርስ ብቻ በተለየ መንገድ የምንፈልገው አይደለም። ወይም ለተለዩ ጉዳዮቻችን ብቻ የምንፈልገው አይደለም።

እንደ ክርስቲያን የሕይወት መመሪያችን ሊሆን ይገባል። ዕለታዊ ፀሎታችንም እንኳ በእኛ ፈቃድ ላይ የእርሱ ፈቃድ እንዲሰለጥን መፍቀድ ሊሆን ይገባል።8 «ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን» «በሰማያት ያለችው ፈቃድህ በእኔም ላይ ትሁን» ማለት ነው።

እንደተገለጠው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይህንን ዓለም በመመሰል ወይም በዓለማዊ ፍልስፍና ማወቅ አንችልም።9 የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ የምንችለው በተለወጠ ወይም በእርሱ መነፈስ በታደሰ ልብ መሆን ስንችል ነው። እኛ ለመታደስና ለመለወጥ ለእርሱ መንፈስ ራሳችንን ሳናስገዛ በሌሎች መንፈሳዊ ሰዎች ናቸው ብለን በምንገምታቸው ሰዎች ባቋራጭ ለማወቅ አንታገል።10

በመሰረት ከበደ የተዘጋጀ

 ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ዘዳግም 30፡11-14 (2) 2ቆሮንቶስ 6፡14-18 (3) 1ተሰሎንቄ 4፡2-7 (4) ምሳሌ 5፡15-20 (5) ሚልኪያስ 2፡13-16 (6) ዘፍጥረት 2፡24-25 (7) ዘፍጥረት 2፡18 (8) ማቴዎስ 6፡10 (9) ሮሜ 12፡2 (10) 1ሳሙኤል 28፡8-14


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More