×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
ወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት

የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ጋብቻ

«የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።» (ሮሜ 12፡2)

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

ይህ ጽሁፍ ራስን በራስ የማርካትን የፍትወት ፈተና ድል ማድረግና በክርስቶስ ኢየሱስ በሚገኘው ፀጋ የነፃንን ሕይወት መምራት የሚሹትን ሁሉ ለመርዳት ታልሞ የተዘጋጀ ነው። ራስን በራስ የማርካት ፈተና በእርግጥም ድል ሊነሳ የሚችልና ወንዶችና ሴቶችም ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት ለአማኞች ሁሉ ያስገኘውን የነፃነት ሕይወት ለመምራት የሚችሉበት ነው።

በክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ውስጥ ራስን በራስ ማርካት ኃጢአት ሳይሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች ብንጠቀምበትም ተቀባይነት ያለው ነው የሚል እውነትነት የሌለው አስተሳሰብ አለ።

አንዳንዶች ራስን በራስ ማርካት በሚከተሉት ሁኔታዎች ተቀባይነት አለው ብለው ያምናሉ፡

  1. ለላጤዎች /ባላገቡ
  2. ከትዳር ጓደኛቸው ለረጅም ጊዜ ለተለዩ ባለትዳሮች
  3. ከግብረ-ሥጋ ግንኙነት ጋር ከተያያዙ ወንጀሎች ለመጠበቅ

የንፅህና ጎዳና በተሰኘው እና ምርኮኞችን ነፃ ማውጣት በተሰኘው ኮርስ ተካፋይ ከሆኑት መካከል አንዱ ራስን በራስ ስለማርካት በአንድ መጋቢ የተፃፈ አንድ ጽሑፍ ላከልን። በዚህ ጽሁፉ፣ በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ማለትም “ላጤዎችን ከጫና ለመገላገል”፣ “ከትዳር ጓደኛ በሚራቅ ወቅት ከሚፈጠር ጫና ለመተንፈስ ” እና “ግብረ-ሥጋ ነክ ወንጀሎችን ለመከላከል” ራስን በራስ ማርካትን መፍትሄ አድርጎ ያለማወላወል አቅርቧል። በተጨማሪም “ከጋብቻ በፊት የፍትወት እርካታ እንድናገኝ” እግዚአብሔር ራስን በራስ ማርካትን ሰጥቶናል በማለት ወጣት ልጆችን ያለሃፍረት ያስተምራል።

ይህ መጋቢ ምርኮኞችን ነፃ ማውጣት በተሰኘው በዚህ ትምህርታችን ከሚሳተፉት መካከል በፖርኖግራፊ ተጠቃሚ ሳይሆኑ እንኳን ሥጋቸውን በማርካት ለባርነት ራሳቸውን የሰጡ ሰዎች የላኩልንን ማንበብ ቢችል እወዳለሁ። ለገዛ ፍትወታቸው ባሮች ሆነዋል፤ ከጌታ ጋር ያላቸውንም ርምጃ ካሽመደመደ ከዚህ አድካሚ ስቃይ ራሳቸውነ ነፃ ማውጣት አልቻሉም። ይህንን ባህርይ ሊያቆሙ ባለመቻላቸው ምክንያት፣ ይከሰሳሉ አንዳንዶቹም ያፍራሉ ደግሞም ተስፋ ይቆርጣሉ። በዚህ ባህርይ የገፉበት ሰዎች በማኅበራዊ ጉዳዮች የመሳተፍ ችግር ይገጥማቸዋል ምክንያቱም ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ባሪያ የሆኑበት የተሰወረ ድብቅ ምስጢር አላቸውና ነው። ከዚህም ባሻገር፣ ይህ መጋቢ፣ እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች ራስን ከማርካት ደዌ ነፃ እንዳወጣቸው ደግሞም ከድብርት፣ ሰውን ሁሉ እንደ ጠላት ከመቁጠር በሽታ፣ ከጭንቀት ደግሞም ሥጋዊ ፍትወታቸውን ከማርካት፣ ደግሞም ከሁሉም ዓይነት የግብረ ሥጋ ንፅህና ጉድለቶች እግዚአብሔር እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው የጻፉትን ኢ-ሜይል ቢያነብብ እወዳለሁ።

አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ራስን በራስ ማርካት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተለይቶ ስላልተጠቀሰ፣ የተግባሩን አስፈላጊነት ወይንም አላስፈላጊነት እግዚአብሔር ከግምት ውስጥ አላስገባውም ብለው ያምናሉ። ይህ ግን ትክክለኛ ነውን? ለመሆኑ እግዚአብሔር በእውነት ራስን በራስ ስለማርካት ምንም አልተናገረምን? “ራስን በራስ ማርካት/ masturbation” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ስላልተጠቀሰ ወንዶችና ሴቶች የስጋቸውን ምኞች እንዲፈፅሙ እግዚአብሔር ፈቀደላቸው ማለት ነውን? ልብ በሉ፣ “pornography” የሚለው ቃል ራሱ በቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተቀመጠም (ምንም አንኳን ስርወ ቃሉ ቢኖርም)፣ ስለ ፖርኖግራፊና ራስነ በራስ ስለ ማርካት የሚናገሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆች ግን አሉ። “ማጨስ” የሚለው ቃልም ሆነ የሥጋ ኃጢአቶችን የሚዘረዝሩ ቃላቶችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሱም። ሆኖም ግን፣ ከእነዚህ ኃጢአቶች ራሳችንን ለማራቅ በስም በስማቸው ይዘርዘሩልን ብለን ልንጠይቅ አንችልም።

ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ “ራስን በራስ ማርካት/ masturbation” የሚለውን ቃል ባይጠቀምም፣ ጉዳዩ ትክክል ወይን ስህተት ስለ መሆኑ እናዳናውቅ በድንግዝግዝ ውስጥ አላስቀመጠንም። ራስን በራስ ማርካት ለላጤዎች የተሰጠ “የእግዚአብሔር ስጦታ” ወይንም “የግብረ-ሥጋ ወንጀሎች መከላከያ” ሳይሆን ወደ ኃጢአት ባርነት የሚመራ ፍትወተ ሥጋ ነው። “ኃጢአትን የሚያደርግ የኃጢአት ባሪያ ነው”1 የሚለው የኢየሱስ ንግግር ራስን ለማርካት የሚደረጉ የትኞቹንም እንቅስቃሴዎች ይመለከታል።

ራስን በራስ ማርካት በሥጋ እየተቀሰቀስን መኖርን እንድንጀምረው የሚያደርግ ሲሆን “ለሥጋ ልቅነት” ባሪያዎች እንድንሆን ያደርገናል። “እንደ ሥጋ ፍቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ” በማለት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስጠነቅቁን ሲሆን፣ “ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ” በማለት እንዴት እንደምናቆመው ይነግረናል።2 እንደ እውነቱ፣ ራስን በራስ ማርካት የሥጋ ልቅነትና የራስ ፍትወታዊ ጣዖት መገለጫ ነው። ራስን ማሳትና ባርነት ነው። እነዚህን እውነቶች ከቅዱሳት መጻሕፍት እንመልከት።

ስለ ሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኵስነትና ለዓመፃ ባሪያዎች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ፥ እንደዚሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ።
የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና።3

ይህ ጥቅስ ራስን መስጠት ወደ ባርነት እንደሚመራ ያስተምረናል። “የሰውነታችንን ክፍሎች” ለአመፃ ካቀረብን፣ የኃጢአት ባሪያዎች እንሆናለን። አንዳንዶች ራስን በራስ ማርካት “ከውጥረት ተንፈስ ያረገናል” ስለዚህም የትዳር ጓደኛችን ባይኖርም በነፃነት እንንቀሳቀሳለን ወይንም ከከፋ የፍትወተ ስጋ ተግባር የተጠበቅን እንሆናለን ይላሉ። ራስን በራስ ማርካት “ውጥረትን የሚያቀልልልን” ለጊዜው ነው። ውጥረቱ ብዙም ሳይቆይ ይመጣል ስለዚህም ራስን በራስ የማርካቱ ፍላጎት መልሶ መላልሶ ይመጣል። ይህም ማለት በቀላሉ ለሥጋ ባርነት ታልፈን ተሰጠን ማለት ነው። ሰውነታችንን ግን ለፅድቅ ካስገዛን ግን፣ የጽድቅ ባሪዎች እንሆናለን። ስለዚህ፣ ሰውነታችሁን ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ እናም የክርስቶስ ባሪያዎች መሆናችሁ ከራስ ልቅ ምኞት ነፃ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል።

ራስን በራስ ማርካትን ጥብቅና ሊቆምለት የሚሻ ሌላው ሙግት ደግሞ፣ ነገሩ እንደ ምግብ አመጋገብ ዓይነት ነው፤ ራሳችንን ልቅ ካደረግን፣ ባሪያዎች እንሆናለን። ማድረግ ያለብን የምግብ ፍላጎታችንን ለመቆጣጠር መሞከር ነው እንጂ መብላት ማቆም አይደለም። እንግዲያው መብላት ኃጢአት እንዳልሆነ ሁሉ፣ ራስን በራስ ማርካትም ኃጢአት አይሆንም፤ የሚያስፈልገን ባሪያ እንዳያደርገን መጠንቀቅ ነው። ይህ መከራከሪያ ትልቅ ችግር አለበት። ችግሩም፡ መብላት ስነ-ሕይወታዊ ህግ ነው። ካልበላን እንሞታለን። ግብረ-ሥጋ ግን ሥነ-ሕይወታዊ ግዴታ አይደለም ይልቁኑ መሻት ነው።

እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።4

ራስን በራስ ማርካት ልቦና በሥጋ ፍላጎት ላይ እንዲያርፍ ያደርጋል፣ የራቁትነትን እና የፍትወተ ሥጋ ምስልንም በልብ ውስጥ ይቀርፃል። ራስን በራስ ለማርካት በተሞከረ ቁጥር፣ ምስሉ ግልፅ እየሆነና ውጥረቱም እየናረ ይሄዳል፣ ሰይጣንም የሃሳብ ግዛት የሚመሠርትበት መሣሪያ ይሆንለታል።5

በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።6

ራስን በራስ የማርካት እውነተኛ ችግር ይህ ነው፡ ራሳችሁን በራሳችሁ ማርካት ስትሞክሩ፣ ደስ የምታሰኙት ራሳችሁን ብቻ ነው። ያላችሁት በሥጋ ስለሆነ ድርጊቶቻችሁ እግዚአብሔርን ደስ አያሰኙም ይልቁኑ የፍትወት ባሪያ ትሆናላችሁ። ብልቶቻችሁንም የኃጢአት ባሪያዎች አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ ልቡናችሁም የሚያሰላስለው የስጋ ፍላጎታችሁን ብቻ ነው።

ከሥጋ ባርነት ነፃ የምንሆንበት መንገድ አለ፣ ስለዚህም ሰበብ ልንደረድርለትና “ለተወሰኑ ችግሮች ተቀባይነት እንዲኖረው” ልንሟገትለት እኛንም የሚያምኑንን ሰዎች ወደ ባርንት ልንገፋፋቸው አይገባም።

ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።
ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።7

ራስን በራስ ማርከት ኃጢአት የሚሆነው ለምንድን ነው? ኃጢአት የሚሆንበት ምክንያት ራሳችንን ለማርካት ስንሞክር “የሥጋን ምኞት መፈፀማችን” ሲሆን በመንፈስ ስንመላለስና ስንኖር ልናደርገው የማይገባን ነው ማለት ነው። ነጥቡን ግልፅ እናድርገው። በመንፈስ ስንመላለስና በእምነት ስንኖር፣ የሥጋን ምኞት አንፈፅምም።

ለአንተ ያለህ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ለራስህ ይሁንልህ። ፈትኖ መልካም እንዲሆን በሚቈጥረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ ብፁዕ ነው።
የሚጠራጠረው ግን ቢበላ በእምነት ስላልሆነ ተኮንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው።8

ራስን በራስ ማርካት ኃጢአት ነው ምክንያቱም ከእምነት የሚመነጭ አይደለምና። የሚያስፈልገኝን ሁሉ እንደሚሰጠኝ እግዚአብሔር በሰጠኝ ተስፋ ላይ አልታመንም9፣ ከፈተና የምወጣበትን ምንገድም ማየት አልችልም10፣ ከውድቀትም አይጠብቀኝም11፣ ይልቁኑ የሥጋን ምኞት ለማርካት የተሰጠሁ እሆናለሁ።

ከዚህ ፈተና ነፃ የሚወጣበት መንገዱ ዘወትር ሙሉ በሙሉ እና በፍፁምነት መቃወም ነው። የረከሰ አስተሳሰብ እንዲኖረን ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ራሳችንን ልናርቅ፣ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በጥልቀት ልናስገባ እና ባለትዳር ከሆንን፣ የግብረ ሥጋ እርካታ ለማግኘት ወደ ትዳር ጓደኛችን ልንመለስና ከኃጢአት እስረኝነት ነፃ ሆነን ልንመላለስ ይገባል። ራስን በማስደሰት ፈተና ላይ “በሩን ከቆለፍንበት”፣ “ላይከፈትም ከከረቸምነው” ደግሞም “ጠባቂን” ካቆምን፣ በእርግጥም ከእርሱ ነፃ እንወጣለን12

ሰዎች እግዚአብሔር በጉዳዩ ላይ ዝም ማለቱን ተገን አድርገው “ራስን በራስ ማርካት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም” ስለዚህም ፈቅዷል ማለት ነው ብለው ሲነግሩኝ፣ ቃሉ በቀጥታ ስላለመጠቀሱ የምስማማ መሆኔን እነግራቸውና እግዚአብሔር ፈቅዶት ቢሆን ኖሮ ሊጠቀስ ይገባ ነበር በማለት እንዲያስተውሉ እረዳቸዋለሁ። ለምሳሌ፣ ይህንን ምንባ እንመልከት፡

ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ። እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤
ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።13

እግዚአብሔር ራስን በራስ ማርካትን ሊጠቅስ ቢገባው ኖሮ ሊጠቅሰው የሚገባ ምቹ ስፍራ ይህ ነበር ወይንም ቢያንስ ቢያንስ ራስን ስለማርካት ይናገር ነበር፣ በመሠረቱ አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ ይችል ነበር። ጳውሎስም፣ “በፍትወት ከመቃጠል ይልቅ ራሱን በራሱ ቢያረካ ይሻላል” በማለት መጥቀስ ይቀለው ነበር። ግን አላደረገውም፣ ራስን በራስ ማርካት የሚለውን ቃል አልጠቀሰም ወይንም ራስን በራስ ከፍትወተ ስጋ ስለ ማሳረፍ ፍንጭም አልሰጠም። ይህ በፍትወት መቃጠል የተፈቀደለት መተንፈሻ ከትዳር ጓደኛ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈፀም ብቻ ነው። የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ከትዳር ውጪ የተዛባ ተግባር ስለሆነ ሊወገድ ይገባዋል።

እግዚአብሔር አብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንዲህ ብሏል፣ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ፣ ይህ ነው”። ለምን? ምክንያቱም እስከ ሞት ድረስ፣ በመስቀልም ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዝዟልና። ስለዚህ በየዕለቱ መስቀላችንን በመሸከም እስካልተከተልነው ድረስ ደቀመዛሙርቱ ተብለን ልንጠራ አይገባንም። መስቀላችንን መሸከም ማለት፣ ሥጋችንን መስዋዕት ማድረግ እንጂ መሻቱን ልናረካለት አይገባም። ይህም ማለት ለራስ መሞት፣ እንጂ ሥጋን ደስ ማሰኘት አይገባም ማለት ነው። በዚህ ረገድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አብዝተን ልንማር ያስፈልገናል። መስቀል የአንድ ሰው ሥጋ መሰቀሉን እንጂ “በቁጥጥር ስር መዋሉን” አያመለክተንም። መስቀል “ውጥረትን ስለማርገብ” ሳይሆን ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ ስለ መጋደል ይነግረናል። ራስን በራስ ማርካት በአንዳንድ ሁኔታዎች እንዲፈቀድ ማድረግ፣ እኛ ክርስቲያኖች ለራሱ የሞተውን እርሱን እንድንከተል የታዘዝንበትን መስቀሉነ መካድ ነው።

የነገሩ እውነታ ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ ሙሉ በሙሉ መስቀል የሚቀልል መሆኑ ነው። ለስጋ ጥቁት ቀዳዳ የምንሰጥ ከሆነ፣ የረከሱ አስተሳሰቦቻችንን ያቀጣጥላቸዋል ደግሞም ያተነክራቸዋል፣ ደግመን ደጋግመን እንድናደርገውም ያነሳሳናል ነገሩም ቀለል እያለን ይመጣል። ስለዚህ ሥጋን ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ የራስን በራስ እርካታ ጨርሶውኑ ልንክደውና ልንቃወመው ይገባል። ቅዱሳት መጻሕፍት ሥጋችንን እንድንቆጣጠር ምንም ትዕዛዝ አልሰጠንም፣ እንድንክደው እና እንድንሰቅለው ግን ብዙ ጊዜ አዝዞናል።

እንግዲያው፣ በዚህ ርዕስ ረገድ ተግባራዊ እንሁን። አብዛኞቻችን ለአቅመ አዳም ወይንም ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ልጆች አሉን ራሳቸውን በራሳቸው ለማርካት እንደሚሞክሩም እናውቃለን። ከእነርሱ ጋር እንዴት በጉዳዩ ላይ መወያየት እንችላለን?

በመጀመሪያ፣ ስለ መስቀሉ መግለጫ እንስጣቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ እንደሰጠ እና እኛም ሕይወታችንን አሳልፈን እንድንሰጥ እንደሚጠብቅብን ለልጄ እነግረዋለሁ። ሰውነቱንም ለአብ መስዋዕት አድርጎ አቅርቧል፣ እኛም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ሰውነታችንን ሕያው መስዋዕት አድርገን ማቅረብ እንችላለን። ኢየሱስ የሥጋውን ምኞት እንዲያረካ በሰይጣን በተፈተነ ወቅት፣ ሥጋውን በመስቀል ላይ በሚስማር በመጠረቅ ፈተናውን እንዳሸነፈ እንነጋገራለን። በተመሳሳይ መንገድ እኛም ሰውነታችንን ለኃጢአት ሙት እንደሆነ ልንቆጥር ይገባናል። ብልቶቹን ለኃጢአት ባሪያ አድርጎ ካቀረበ፣ ራስን በራስ ለማርካት መጣር የሚያስከትልበትን ባርነት በግልጽ እነግረዋለሁ። የሚሰሙት ስሜቶች ከእግዚአብሔር የተሰጡና በጋብቻ ውስጥ ደስ እንዲሰኝባቸው እንጂ ለራስ ወዳድነት እንዳልታቀዱ እነግረዋለሁ። ክርስቶስን መከተል ማለት ራስን በራስ ማርካትን ምርጫ ማድረግ አለመሆኑን ይረዳል። ፈተና በሚመጣበት ወቅት፣ ለመቆጣጠር ወይንም ለምኞቱ አልፎ ከመሰጠት ይልቅ ጨርሶውኑ እንደ አማራጭም እንዳይቆጥረው ማድረጉ የሚቀልለው ሆኗል።

በስተመጨረሻ፣ ምርኮኞቹን ነፃ ማውጣት በተሰኘው ፕሮግራማችን ያገኘነውን ምስክርነት በማቅረብ ላጠናቅቅ። ምስክርነቱ የንፅህና ጎዳና የተሰኘውን ኮርስ የመጨረሻ ሳምንት ከሚካፈልና ራስን በራስ ለማርካት ከመሞከር ባርነት ነፃ ከወጣ በሳል ሰው የተገኘ ነው። ምስክርነቱም እነሆ፡

“ችግሬ የጀመረው የወጣቶች መጋቢያችን መጽሐፍ ቅዱስ ራስን በራስ ስለማርካት ምንም ስለማይናገር፣ እግዚአብሔር አልኮነነውም ማለት ነው ብሎ በነገረኝ ወቅት ነው። ወደፊት የትዳር ጓደኛችን ከምትሆነው ጋር የሚኖረንን ግንኙነት እያሰብን ራሳችንን ለማርካት ከሞከርን ጉዳዩ ኃጢአት አይሆንም ብሎ ነገረን። ራሴን በራሴ ለማርካት የመሞከሩን ሥራ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ በማድረግ ቀስ በቀስ ነው የጀመርኩት። ሥጋን ከመካድ ይልቅ፣ ለኃጢአት ታልፌ የተሰጠሁ ያህል ኩነኔ ይሰማኝ ጀመር። መጋቢዬ ግን በትክክል ከተጠቀምሁበት ከግብረ ሥጋ ወንጀል የምጠበቅበት መሣሪያ መሆኑን ነው የነገረኝ። ተላላ ነበርሁና፣ አመንሁት። ብዙም ሳልቆይ ብልቶቼን ለሥጋ ፍትወት አሳልፌ መስጠቴ የፍትወት ስሜቴን እንደማይቀንሰው ወይንም ከጫናውም እንደማይገላግለኝ ተረዳሁ። በተቃራኒው ግን ራሴን በራሴ ለማርካት በሞከርኩት ቁጥር የበለጠ ተነከርኩበት። ”

አንድ ቀን ወደ እርሻው በሚወስደው መንገድ ዘወር ብዬ ራሴን የማርካት ሙከራዬን እንደጨረስሁ፣ የገጠመኝ ምን እንደሆነ በውል አላወቅሁም፣ ያን ቀን ለሦስተኛ ጊዜ ማድረጌ ሲሆን፣ እንደ ሆነ ነገር ሲጫነኝ የዚያ ተግባር ባሪያ መሆኔ ታወቀኝ። በሃይማኖት ባለሥልጣነት ሙሉ ይሁንታ ባለማወቅ የተጀመረ ነገር፣ በውስጤ ያለችውን መንፈሳዊ ሕይወት ደብዛዋን አጠፋት።

ያ መጋቢ ምንም እንኳን ታዋቂ ባያደርገውም እውነተኛውን ቃል ቢሰብክ ምንኛ ጥሩ ነበር ብዬ ተመኘሁ። ራሴን እስካልካድሁና መስቀሉንም ዕለት ዕለት እስካልተሸከምሁ ድረስ የእርሱ ደቀ መዝሙር ልሆን እንደማይገባኝ አብራርቶልኝ ቢሆን ብዬ ተመኘሁ። ስለ ባርነት መርሆ ነግሮኝ ቢሆን ማለትም ራሴን ለሰጠሁበት ነገር ባሪያ እንደምሆን ምናለ በነገረኝ ብዬ ተመኘሁ። እቆጣጠረዋለሁ ብዬ ራሴን ከማታለል ይልቅ፣ ወይንም በተወሰኑ ሁኔታዎች ብቻ እጠቀምበታለሁ ብዬ እንደ አማራጭ ልይዘው ከመሞከር ይልቅ ራስን በራስ ማርካትን ፈፅሞ መጠየፍ እንደሚቀልል ግልጥና ቀላ አድርጎ ቢያቀርብልኝ ተመኘሁ። “መጽሐፍ ቅዱስ አልጠቀሰውም” የሚለውን ርካሽ ቃል ከመጠቀም ይልቅ፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆችን ቢያስተምረኝ ጥሩ ነበር።

የቀደመውን እረኛዬን መውቀስ አልሻም፤ አሳቹ ልቤ የሚሰብከውን መስማት ደስ ይለው ነበር እናም ለራሴው ድርጊት ተጠያቂው እኔ ነኝ። ሰበብ ፈጥሬ ላፀድቀው ከመሞከር ይልቅ እንድክደውና እንድሰቅለው ሊረዳኝ የሚችል የእግዚአብሔር ሰው ባገኝ ብዬ ተመኘሁ።

ይህንን ፅሁፍ ልንደመድም ስንቃረብ በንፅህና ጎዳና ኮርስ ላይ ሌላ አንድ ሰው ገጠመን። ይህ የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ፅፏል፡

“ወስጤ በተነሳሳበት ወቅት ሁሉ፣ ራስን በራስ የማርካት ፍላጎቴን መቋቋም አልችልም። ለረጅም ዓመታት ልፋለመው ሞከርኩ፣ ምንም እንኳን ጥቂት ጊዜያዊ ድሎችን ባገኝም፣ ጨርሶውኑ ድል መንሳት ግን አልቻልሁም። ህይወቴን በሙሉ ለክርስቶስ መኖር ምኞቴ ነው፣ ይህን አረመኔ ድል እስካላደረግሁት ድረስ ግን ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ለወደፊቷ ሚስቴ ታማኝ መሆን እሻለሁ ግን በዚህ ጎዳና ላይ ከዘለቅሁ፣ ይህ ምኞቴ ግን እውን ሊሆን አይችልም።”

ራስን በራስ ለማርካት መሞከር የባርነት በር ነው! እግዚአብሔር ለዚህ ወጣት በክርስቶስ ነፃነትን ይስጠው።

አዎን፣ ከዚህ አረመኔ የኃጢአት ልማድ ነፃ መሆን ይቻላል። በእግዚአብሔር ጸጋ፣ ዲያቢሎስን መቃወምና ሥጋችንንም መርታት እንቸችላለን። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ልንመጣና የእርሱን ብርቱ እርዳታ ልናገኝ፣ ለትዳር ጓደኛችን ልናሳይ የሚገባንን ፍቅር መስረቃችንን ልናቆምና በምትኩ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን ወደ ትዳር ጓደኛችን ፊታችንን ልንመልስ ይገባናል። በዚህም በሰውነታችን እግዚአብሔርን ማክበር እንችላለን። ላጤዎቹ ደግሞ ለራስ ደስታ ከመኖር ወደ ክርስቶስ ዘወር ሊሉና በሚያስፈልጋቸው ወቅትም ከእርሱ ብርቱ እርዳታን ሊያገኙ ይገባል። በክርስቶስ ኃይል እኛን ባሪያ ለማድረግ የሚታገሉትን የጨለማ ኃይላት ድል እናደርጋለን። በኢየሱስ ነፃነት ይገኛል፣ ያም እውነተኛና ለዘላለም የሆነ ነፃነት ነው። ራሳችንን በራሳችን በማርካት ደስ ለመሰኘት ከመሞከር ይልቅ፣ ሰውነታችንን ሕያው መስዋዕት አድርገን ለጌታ የምናቀርብበትን ጸጋ እግዚአብሔር ይስጠን፣ ያገባን ከሆንንም ወደ ትዳር አጋራችን እንመለስ።

ከማይክ ክለቨል እና የስራ ባልደረቦቹ ከSettingCaptivesFree.com

የተወሰደ።

 ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ዮሐንስ 8፥34 (2) ሮሜ 8፥13 (3) ሮሜ 6፥19-20 (4) ሮሜ 8፥5 (5) 2ኛ ቆሮንቶስ 10፥3-5 (6) ሮሜ 8፥8 (7) ገላ 5፥16-17 (8) ሮሜ 14፥22-23 (9) ፊልጵስዩስ 4፥19 (10) 1ቆሮ 10፥13 (11) ይሁዳ 24 (12) ዮሐ 8፥36 (13) 1ቆሮ 7፥8-9


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More