×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
ወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት

የወሲብ ፊልም ምርኮኛ

አንዲት የኮሌጅ ተማሪ የወሲብ ፊልም ሱስ ልምዷን ካካፈለችው የተወሰደ

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

አሥራ ሥምንት ዓመቴ ነው። አልፎ አልፎ ከሚታይብኝ የእፍረት ስሜት በቀር በራሴ የመተማመን ስሜት ያለኝ ነኝ። ዕድገቴ ሙሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን አንድ የአምልኮ ዝማሬ መሪዎች ቡድን ሲቋቋም በመዘምራን ቡድኑ ውስጥ ከበሮ እንድጫወት ስጠየቅ አኔም በእሽታ ተቀብዬ ከመዘምራን ቡድኑ ጋር ተቀላቀልሁ። ሕይወት እጅግ መልካም ነበር ። ውስጤ ግን ባዶ ነው።

ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ይህ በውስጤ የነበረው ባዶነት የበለጠ እየሰፋ መጣ። ስለዚህ ይህን ባዶነቴን የሚሞላልኝን ነገር ፍለጋ ቀጠልኩ። ምንም ነገር አያረካኝም ነበር። ይህንኑ ርካታ ፍለጋ አንዳንድ ትናንሽ ነገሮችን ማድረግ ሞከርኩ። አጫሽ ከነበረው አጎቴ ሲጋራዎችን መስረቅና ማጨስ ጀመርኩ። ሆኖም ይህ ርምጃዬ ምንም ፈቅ አላለም ሕይወቴን አልለወጠም፤ ባዶነቴንም አልሞላም። ያም ሆኖ በቀላሉ ተስፋ አልቆረጥኩም። እኔኮ ጄኒፈር ነኝ እንደብረት ጠንካራ ! እንዴት በቀላሉ እጄን እሰጣለሁ። የምፈልገውን እስካገኝ ድረስ እረፍት የለኝም። አብዛኛው ሰው በቀላሉ የማያውቀውን ኮምፒውተር የመጠቀም ችሎታ አለኝ። ይኼኔ ነው የምፈልገውን ያገኘሁት። ያም የወሲብ ፊልም።

ዬሄ ነገር ሱስ ሆኖብኝ አረፈው:: በእርግጥም ይህ በሽታ በሕይወቴ ውስጥ ወሲብን የሚተካ አልነበረም። ባይገርማችሁ ወንድ የማላውቅ ድንግል ነበርኩ፤ አሁንም ድንግል ነኝ። ይህን ነገር ግን የተጠቀምኩበት እንደው ዝም ብዬ በሕይወቴ ውስጥ የሚሰማኝን የቦዶነት ሕይወት ቢሞላልኝ ብዬ ነው። ትንሽ ትካዜ ሲሰማኝ ወይም ሲከፋኝ። ቀኑም እየደበረኝ ሲመጣ፤ በቀላሉ ወደ መኝታ ቤቴ ገብቼ በሬን እዘጋና፣ በዚህ በማየው ፊልም ራሴን እያከምኩ እዝናናለሁ። መልካም ስሜቴ ተመልሶ ይመጣል። ነጻ ነው ፤ ጉዳት የለውም ፤ በጊዜው የማስበው እንደዛ ነበር። እንደዚህ እንደማደርግም ማንም አያውቅም። የማየው የማይበቃኝና ጥማቴን የማያረካልኝ ስለሆነ በየጊዜው ኢንተርኔት ከፍቼ ማየት የዘወትር ተግባሬ ሆነ። ልክ በቀላሉ ገብቶ ወደ ከባዱ አደንዛዥ እጽ እየተለመደ እንደሚገባ ሁሉ እኔም እግዚአብሔር እስኪደርስልኝ ድረስ ልማዴ ባደረብኝ የወሲብ ፊልም ማየት ሱስ የተነሳ የበለጠ ማየት የሚያስችለኝን ድረገጽ ሳስስ መቆየት ነበር።

መቼ ፣እንዴት፣ለምን እንደሆነ እስካሁን በርግጥም አልገባኝም (የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ቢሆንም) አንድ ቀን በድንገት እያደረግኩ ስላለው ነገር ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ? ሕይወቴን እያበላሸሁትና ልወጣ ወደ ማልችለው አዘቅት ውስጥ እየገባሁ እንደሆነ እየተገለጠልኘ መጣ። ይህም ሰጋቴ ሆነ። አባቴ አጫሽ ነበር ፤ ሲያቆም ግን በሂደት ሳይሆን በአንድ ጊዜ ነው ቁርጥ አድርጎ ያቆመው። ይህን አውቃለሁና እኔም እንደዚያ ቁርጥ አድርጌ ማቆም እንዳለብኝ ተገነዘብሁ። በዛውም በውስጤ ሲያባዝነኝ የነበረውን የውስጤን ባዶነት መሙላት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ተረዳሁ። ከዛም ተነስቼ በኮምፒውተሬ ውስጥ ያጠራቀምኳቸውን የወሲብ ፊልሞች ፋይሎች ሁሉንም አንድም ሳላስቀር ደመሰስኳቸው። በዝርዝር የያዝኳቸውን የወሲብ ድረገጾችንና የምሥጢር ቁልፎችንም ሁሉንም ሰረዝኳቸው። እንደገና ወደ ኋላ መመለስ አልፈለግኩም። ስጀምር ጉዳት አልባ የመሰለኝ ነገር ኋላ ላይ እግር ተወርች አስሮ ሱሰኛው እንዳደረገኝ አውቃለሁ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ አንድ የክርሰቲያኖች የሱባኤ ስብሰባ ላይ ሄድኩኝ። በሕይወቴ ያየሁት ለውጥ እጅግ በጣም አስደነቀኝ። ይህን ዓይነቱን ለውጥ እግዚአብሔር በአፋጣኝ በሕይወቴ ይፈጽማል የሚል ግምት አልነበረኝም። በዚያ በሱባኤ ቆይታዬ ላይ እንደገና ሕይወቴን ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ አሳልፌ ሰጠሁኝ። ይህም ማለት ለእግዚአብሔር እንደገና እንዲህ አልኩት፡- «በፍጹም ሙሉ በሙሉ ለአንተ መኖር እፈልጋለሁኝ፤ በ2ኛ ቆሮ 5፥17 ላይ « ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። » ተብሎ እንደተጻፈው አዲስ ፍጥረት መሆን እፈልጋለሁኝ ባሳየኸኝ ፍቅር ሕይወቴ እንዲለወጥ እፈልጋለሁ ። አልኩት ። በኢሣ 64፥6 ላይ « ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። » ተብሎ በቃሉ እንደተጻፈው ብዙ እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ነገሮች እንዳደረግሁ አውቃለሁ። ብቃት ሳይኖረኝ እንኳ ጽድቅ የመሰለ ነገርም ለማድረግ ደፍሬአለሁ ። ይሁንና የእግዚአብሔር ምህረት ታላቅ እንደሆነም አውቄያለሁ። በእኛ ሥራ ሳይሆን በምህረቱ ብዛት እንደምንድን ተረድቻለሁ። በቲቶ 3፥4-5 « ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤» ተብሎ የተጻፈውም ለዚህ ነው። ከዚያም ቀን አንስቶ ለእግዚአብሔር አምላኬ ቁርጠኝነቴን ገለጽሁ። ዓለምና እኔ የምናስበውን ሳይሆን እርሱ ብቻ የሚያስበውን ነገር ለእርሱ ክብር በሕይወቴ ለመፈጸም ቆረጥኩ።

በዛ የሱባኤ ስብሰባ ሐይወቴ የተለወጠበትን መንገድ እስካሁን ሳስበው ደስ ይለኛል። እግዚአብሔር አምላክ እንደሚወደኝ አውቃለሁ ግን ይህን ያህል ብዬ ግን አላሰብኩም ነበር። በዙርያዬ በግራም በቀኝም ሆነው የሚያገለግሉኝ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ለኔ ሲጸልዩልኝ ፣ ምክር ሲለግሱኝ፣ ፍቅራቸውን ሲገልጹልኝ ሳይ በጣም ነው የተደነቅሁት። ግን ፈጽሞ የማያውቁኝ ለምንድነው የወደዱኝ? መጽሐፍ ቅዱስ በ1ኛ ዮሐንስ 4፥19 ላይ እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወደደን እንደሆነ ይነግረናል። ስለዚህ የወደዱኝ እግዚአብሔር እነሱን የወደዳቸውን ፍቅር ከውስጥ ሲሰማቸው ሊወዱኝ ቻሉ። እኔም አሁን ያ የእግዚአብሔር ፍቅር ከውስጤ እየተሰማኝ ነው። ይህንን ፍቅር ለዓለም ሁሉ አካፍላለሁ። ካገኘሁት ፍቅር በተጨማሪ በአምልኮ መዝሙሬ ውስጥ ከዚህ በፊት ተለማምጄ በማላውቀው መንገድ እግዚአብሔርን ማምለክ ችያለሁ። የድሮ ክርስቲያኖችን ቀርቤ ጓደኞቼ አደረግኳቸው አዳዲስ የጌታ ልጆችንም አገኘሁ። ከዛ የሱባኤ ስብሰባ በኋላ ኡየሱስ ክርስቶስ በፊቴና በተግባሬ ያንጸባርቅ ነበር። በየዕለቱ እግዚአብሔር አምላኬን የማመሰግንበት ጉዳይ አላጣም። በውስጤ ምንም ባዶ የለም። ብቸኝነትም የለም። ኃዘንም ጠፍቷል። ፍርሃትም ከውስጤ ተወግዷል። መዝሙረኛው በ119፥62 ላይ « ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ።» እንዳለሁ እኔም በቀንም በሌሎት እግዚአብሔር በምሥጋናና በዝማሬ ሞላኝ።

አሁን የሚሰማኝ ይህ ነው። እኔንና ጓደኞቼን ሕይወታቸንን ስለለወጠ ልክ በእኩለ ሌሊት ለምሥጋናና ለዝማሬና ለዓምልኮ እንደሚነሳ ሰው ዓይነት ስሜት ይሰማኛል። አግዚአብሔር ሲለውጥ ብትሸመግሉም ሆነ ወጣት ብትሆኑም ምንም ልዩነት አይኖረውም። አንድ ዓይነት ነው። ለዚህም ነው ሃዋሪያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን «ይህን እዘዝና አስተምር። በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ፥ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው።» 1ኛ ጢሞ412 በማለት የመከረው።

ወገኔ ! ዛሬ ሙሉ በሙሉና ፍጹም ሕይወትህን ለክርስቶስ እንድትሰጥ እመክርሃለሁ። የዘላለም ሕይወት ታተርፋለህ እንጂ ምንም የምታጣው ነገር አይኖርም ። ሃዋሪያው ጳውሎስ በሮሜ 6፥23 ላይ፡- « የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።» እንዳለ፣ ይህን የዘላላም ሕይወት የሆነውን የእግዚአብሔርን ነጻ ሥጦታ ተቀበልና ከዘላለም ኩነኔ ዳን። ወደ ጌታ ወደ አምላክህ ና አንተ ለዘላለም የእርሱ ነህና። ዓለም ሁሉ ሲለወጥብህና ፊቱን በአንተ ላይ ሲያዞር ካንተ ጋር የሚሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ምክንያቱም እርሱ ያለ የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነውና።

ከጀነፈር ፁሁፍ ትርጉም የተወሰደ

 ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር
 ጥያቄ አለኝ

ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More