በhabeshastudent.com
መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በ40 ጸሐፊዎች በ1500 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው። ከሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ የእውነተኛ ክስተቶችን፣ ቦታዎችን፣ ሰዎችን እና ንግግሮችን ዘገባ ይዟል። የታሪክ ምሁራን እና የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎች ትክክለኛነቱን ደጋግመው አረጋግጠዋል።
የፀሐፊዎቹን የራሳቸውን የአፃፃፍ ስልቶች እና ስብእናዎች በመጠቀም እግዚአብሔር ማንነቱን እና እrሱን ማወቅ ምን እንደሚመስል ያሳየናል።
በአርባውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በተከታታይ የተገለጸ አንድ ማዕከላዊ መልእክት አለ - ሁላችንን የፈጠረው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ግንኙነትን ይፈልጋል። እርሱን እንድናውቀው እና እንድናምነው ይጠራናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን የሚሰጠን ብቻ ሳይሆን ሕይወትን እና እግዚአብሔርን ያስረዳናል። ሊኖረን ለሚችሉት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ባይሰጥም፣ በቂ መልስ ግን አለው። በዓላማ እና በርህራሄ እንዴት እንደምንኖር ያሳየናል። ከሌሎች ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን። ጥንካሬና ምሪትን ለማግኘት እና ለእኛ ባለው ፍቅር እንድንደሰት በእግዚአብሔር ላይ እንድንታመን ያበረታታናል። የዘላለም ሕይወት እንዴት ማግኘት እንደምንችልም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።
በርካታ የማስረጃ ምድቦች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ትክክለኛነት እንዲሁም መለኮታዊ ጸሐፊነት ይደግፋሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ማመን የሚትችሉባቸው ጥቂት ምክንያቶች እነዚህ ናቸው።
የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ነገሥታትን፣ ከተማዎችን እና በዓላትን በተደጋጋሚ አግኝተዋል - አንዳንድ ጊዜ የታሪክ ጸሐፊዎች እንደዚህ ያሉ ሰዎች ወይም ቦታዎች አሉ ብለው ባላሰቡበት ጊዜ ጭምር። ለምሳሌ፣ የዮሐንስ ወንጌል ኢየሱስ በቤተሳይዳ መጠመቂያ አጠገብ አንድ ሽባን እንደፈወሰ ይናገራል። ጽሑፉ ወደ መጠመቂያው የሚወስዱትን አምስት የእግረኛ መንገዶች እንኳን ይገልጻል። የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎች ከአምስቱ የእግረኛ መንገዶች ጋር ከምድር በታች አርባ ጫማ እስኪያገኙት ድረስ ምሁሩ መጠመቂያው ነበር ብለው አላሰቡም።1
መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ በጣም ብዙ ታሪካዊ ዝርዝሮች አሉት፣ ስለዚህም በውስጡ የተጠቀሱት ሁሉም ነገሮች በአርኪኦሎጂ ገና አልተገኙም። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር የሚጋጭ አንድም የአርኪኦሎጂ ግኝት አልተገኘም።2
በአንፃሩ የዜና ዘጋቢ ሊ ስትሮቤል ስለ መጽሐፈ ሞርሞን እንዲህ ብሏል - “አርኪኦሎጂ በአሜሪካ ውስጥ ከረጅም ጊዜ በፊት ተከሰቱ ስለተባሉት ክስተቶች በመጽሐፈ ሞርሞን ላይ የተጻፈውን ማረጋገጥ በተደጋጋሚ አልቻለም። የሞርሞኒዝምን ጽሑፎች የሚደግፍ ማስረጃ ስለመኖሩ ለመጠየቅ ለስሚዝሶኒያን ኢንስቲትዩት መጻፌን አስታውሳለሁ። ነገር ግን የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎቻቸው ‘በአዲሲቱ ዓለም አርኪዎሎጂ’ እና በመጽሐፉ ውስጥ ባሉ ነገሮች መካከል ምንም ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለ’ በማያሻማ ቃላት መልስ ሰጡኝ።” የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎች በመጽሐፈ ሞርሞን ውስጥ ያሉትን ከተማዎችን፣ ሰዎችን፣ ስሞችን ወይም ቦታዎችን በጭራሽ አላገኙም።3
በአዲስ ኪዳን በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በሉቃስ የተጠቀሱት ብዙ ጥንታዊ ስፍራዎች በአርኪኦሎጂ ተገኝተዋል። በአጠቃላይ ሉቃስ ሰላሳ ሁለት አገሮችን፣ ሃምሳ አራት ከተማዎችን እና ዘጠኝ ደሴቶችን ያለ ምንም ስህተት ጽፏል።4
አርኪኦሎጂ እንዲሁ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶችንም አስተባብሏል። ለምሳሌ፣ ዛሬም ድረስ በአንዳንድ ኮሌጆች ውስጥ የሚሰጠው አንድ አመለካከት ሙሴ ኦሪትን (የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን) መጻፍ እንደማይችል ይናገራል፣ ምክንያቱም ጽሁፍ በዘመኑ አልተፈጠረምና። ከዚያ የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች ጥቁር ስቲልን አገኙ። "በላዩ ላይ ለየት ያሉ ቅርጽ ጽሁፎችን ነበሩበት ሲሆን የሃሙራቢ ዝርዝር ህጎችን ይዟል። ከሙሴ በኋላ ነበር? በፍፁም! ቅድመ-ሙሴ ነበር፤ ያ ብቻ አይደለም፣ ቅድመ-አብርሃም ነበር (ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓ.ዓ. በፊት)። የሙሴን ጽሑፎች ቢያንስ በሦስት ምዕተ ዓመታት ይቀድማቸዋል።"5
አርኪኦሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ትክክለኛነት በተደጋጋሚ አረጋግጧል።
አንዳንድ ዋና ዋና የአርኪዎሎጂ ግኝቶችን የሚዘረዝር ሰንጠረዥ ለማየት ይህንን ይጫኑ
ዋና ዋና የአርኪኦሎጂ ግኝቶችን የሚዘረዝርበት ሰንጠረዥ
የአርኪዎሎጂ ግኝት | አስፈላጊነት |
የማሪ ጽላቶች | እስከ አብርሃም ዘመን ድረስ የሚያጣቅሱት ከ20 ሺህ በላይ የኪዩኒፎርም ጽላቶች ብዙ የዘፍጥረትን የአባታዊ ትውፊቶች ያብራራሉ። |
የኤብላ ጽላቶች | ከ20,000 በላይ ጽላቶች፣ ብዙዎች ከዘዳግም ሕግ ኮድ ጋር የሚመሳሰል ሕግን ይዘዋል። በዘፍጥረት 14 ውስጥ ቀደም ሲል የሉም ተብለው የታሰቡት አምስቱ ከተሞች (ሰዶም፣ ገሞራ፣ አዳማ፣ ሲባዮ እና ዞዓር) ተለይተዋል። |
የኑዚ ጽላቶች | ለመካን ሚስቶች ሴት ባሪያዎች ልጆችን እንደሚወልዱ ያሉ የ14ኛው እና የ15ኛው ክፍለዘመን ከአባቶችን ልምምዶችን ይዘዋል። |
ጥቁር ስቴል | ጽሑፍና የጽሑፍ ሕጎች ከሙሴ ሕጎች ከሦስት መቶ ዓመታት በፊት እንደነበሩ አረጋግጧል። |
የካርናክ፣ ግብፅ መቅደስ ግንቦች | ከክርስቶስ ልደት በፊት 10 ኛው ክፍለዘመን አብርሃም ተጠቅሶ ይገኛል |
የእሽኑና ህጎች (ከክርስቶስ ልደት በፊት 1950 ዓ.ዓ. ገደማ)፤ የሊፒት-ኢሽታር ኮድ (ከክርስቶስ ልደት በፊት 1860 ዓ.ዓ. ገደማ)፤ የሃሙራቢ ህጎች (ከክርስቶስ ልደት በፊት 1700 ዓ.ዓ. ገደማ) | የኦሪት የሕግ ኮዶች ለዚያ ጊዜ በጣም የተራቀቁ እንዳልነበሩ ያሳያል። |
የራስ ሻምራ ጽላቶች | ስዕብራይስጥ ግጥም መረጃ ያቅርባሉ። |
የላኪሽ ደብዳቤዎች | ናቡከደነፆር ይሁዳን ስለ መውረሩ እና ስለ ኤርምያስ ዘመን ማስረጃ ይሰጣሉ። |
የጎዶልያስ ማኅተም | በ2ኛ ነገሥት 25፥22 ውስጥ ስለተጻፈለት ጎዶልያስ ማጣቀሻዎችን ይሰጣል። |
የቂሮስ ሲሊንደር | አይሁዶች በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ እንደገና እንዲገነቡ ለማስቻል የቂሮስን ትእዛዝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫ ያረጋግጣል (2ኛ ዜና መዋዕል 36:23፤ ዕዝራ 1:2-4ን ተመልከቱ)። |
የሞዓባዊ ድንጋይ | ስለ ስድስተኛው የእስራኤል ንጉስ ስለ ዖምሪ መረጃ ይሰጣል። |
የሻልማንሴር III ጥቁር ኦቤሊስስክ | የእስራኤል ንጉሥ ኢዩ ለአሦር ንጉስ እንዴት መገዛት እንደነበረበት በምሳሌ ያስረዳል። |
ቴይለር ፕሪዝም | በእስራኤል ንጉሥ በሕዝቅያስ ዘመን ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ የሰነዘረውን ጥቃት በዝርዝር የሚገልጽ የአሦራውያንን ጽሑፍ ይዟል። |
የተቃዋሚዎች ወቀሳ | የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎች መልስ |
ከጽሁፍ ከመፈጠሩ በፊት ይኖር ስለነበር ሙሴ የኦሪትን መጽሐፍት ሊጽፍ አይችልም ነበር። | መጻፍ ከሙሴ በፊት ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ነበር ፡፡ |
የአብርሃም የትውልድ ከተማ ኡር የለም። | ኡር ተገኝቷል። ከአምዶቹ አንዱ “አብራም” የሚል ጽሑፍ ነበረው። |
“ፔትራ” የተባለችው ከአለት የተገነባችው ከተማ የለችም። | ፔትራ ተገኝታለች። |
የኢያሪኮ መውደቅ ታሪክ አፈታሪክ ነው። ከተማዋ በፍፁም አልነበረችም። | ከተማዋ ተገኝታ ተቆፍራ ወጥታለች። ግንቦቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ትረካ በተገለጸው ትክክለኛ መንገድ እንደወደቁ ተገኝቷል። |
“ኬጢያውያን” አልነበሩም። | ስለ አስገራሚ የኬጢያዊ ስልጣኔዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ማጣቀሻዎች ተገኝተዋል። አንድ ሰው በቺካጎ ዩኒቨርስቲ በኬጢያዊ ጥናቶች የዶክትሬት ዲግሪ ማግኘት ይችላል። |
ብልጣሶር እውነተኛ የባቢሎን ንጉሥ አልነበረም፤ በመዝገቦቹ ውስጥ አልተገኘም። | የባቢሎን ጽላቶች የዚህን ዋና ንጉስ እና የናቦኒደስ ልጅን አገዛዝ ይገልፃሉ። |
አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ “በጣም ብዙ ጊዜ” ስለተተረጎመ በመተርጎም ሂደት ውስጥ ተቀይጧል የሚል ሀሳብ አላቸው። ትርጉሞቹ ከሌሎች ትርጉሞች እየተሠሩ ቢሆን ያ እውነት ሊሆን ይችል ነበር። ግን ትርጉሞች በሺዎች በሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅጂዎች ላይ በመመርኮዝ በቀጥታ ከመጀመሪያው የግሪክ፣ የዕብራይስጥ እና የአረማይክ ምንጭ ጽሑፎች የተወሰዱ ናቸው።
የዛሬ ብሉይ ኪዳን ትክክለኛነት የተረጋገጠው እ.ኤ.አ. በ1947 በእስራኤል የዌስት ባንክን አካባቢ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች “የሙት ባሕር ጥቅልሎች” ሲያገኙ ነበር። “የሙት ባሕር ጥቅልሎች” እኛ ካሉን ከማንኛቸውም ጽሑፎች በ1000 ዓመት የሚበልጥ የብሉይ ኪዳን ጥቅል ይዟል። በእጃችን ያሉትን ጽሑፎች ከእነዚህ ከ1000 ዓመታት በፊት ከተጻፉት ጋር ስናወዳድር 99.5% ስምምነት ተገኝቷል። 0.5% ልዩነቶቹ የጽሁፉን ትርጉም የማይለውጡ ጥቃቅን የፊደል ልዩነቶች እና የአረፍተ ነገር አወቃቀር ናቸው።
አዲስ ኪዳንን በተመለከተ የሰው ልጅ እጅግ አስተማማኝ የጥንት ሰነድ ነው።
ሁሉም ጥንታዊ ጽሑፎች የተጻፉት በቆዳ ላይ ነው፣ ይህም ብዙ የመቆየት ሕይወት አይኖራቸውም። ስለዚህ ሰዎች መልእክቱን ጠብቆ ለማሰራጨት እና ለሌሎች ለማድረስ የመጀመሪያ ቅጂዎችን በእጅ ተቀድተዋል።
የፕላቶን “ሪፐብሊክ” ጽሑፍ የሚጠራጠሩ ሰዎች ጥቂት ናቸው። በ380 ዓ.ዓ አካባቢ በፕላቶ የተፃፈ ጥንታዊ ምርጥ ጽሑፍ ነው። እኛ ጋር ያሉት የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች በ900 ዓ.ም የተቀዱ ሲሆን እርሱ ከፃፈው የ1,300 ዓመት የጊዜ መዘግየት አለው። አሁን ሰባት ቅጅዎች ብቻ ናቸው ያሉት።
የቄሳር “ጋሊክ ጦርነቶች” የተጻፉት ከ100-44 ዓ.ዓ. አካባቢ ነው። ዛሬ ያሉን ቅጂዎች እርሱ ከጻፈ ከ1000 ዓመታት በኋላ የተቀዱ ናቸው። አሥር ቅጅዎች አሉን።
ወደ አዲስ ኪዳን ሲመጣ ከ50-100 ዓ.ም. መካከል የተጻፈ ሲሆን ከ5,000 በላይ ቅጂዎች አሉ። ሁሉም የመጀመሪያው ከተፃፈ ከ50-225 ዓመታት ውስጥ የተቀዱ ናቸው። በተጨማሪም፣ ወደ ቅዱሳን ጽሑፎች ሲመጣ፣ ጸሐፍት (መነኮሳት) የመጀመሪያዎቹን ጽሑፎች ሲገለበጡ በጥንቃቄ ነበር። ሥራቸውን በትክክል አንድ መሆኑን ለማረጋገጥ ደግመው ደጋግመው ይፈትሹ ነበር። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በመጀመሪያ የጻፉት ከማንኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ በተሻለ መንገድ ተጠብቆ ይገኛል። በቄሳር፣ በፕላቶ፣ በአርስቶትል እና በሆመር ጽሑፎች ላይ እርግጠኛ ከሆንነው በላይ ስለ ኢየሱስ ሕይወት እና ቃላት ስለምናነበው የበለጠ እርግጠኛ መሆን እንችላለን።
አዲስ ኪዳንን ከሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች ጋር ለማነፃፀር ይህንን ይጫኑ
የአዲስ ኪዳንን ከሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች ጋር ንፅፅር…
አዲስ ኪዳን ከሌሎች ጥንታዊ ጽሑፎች ጋር እንዴት እንደሚነፃፀር እነሆ*:
ጸሐፊ | መጽሐፍ | የተጻፈበት ቀን |
የመጀመሪያው ቅጂ |
የጊዜ ልዩነት | የቅጂዎች ቁጥር |
ሆመር | ኢሊያድ | 800 ዓ.ዓ. | 400 ዓ.ዓ. | 400 አመታት | 643 |
ሄሮዶቱስ | ታሪክ | 480-425 ዓ.ዓ. | ዓ.ም. 900 | 1,350 አመታት | 8 |
ቱሲዲደስ | ታሪክ | 460-400 ዓ.ዓ. | ዓ.ም. 900 | 1,300 አመታት | 8 |
ፕላቶ | 400 ዓ.ዓ. | ዓ.ም. 900 | 1,300 አመታት | 7 | |
ዴሞስተንስ | 300 ዓ.ዓ. | ዓ.ም. 1100 | 1,400 አመታት | 200 | |
ቄሳር | ጋሊክ ጦርነቶች | 100-44 ዓ.ዓ. | ዓ.ም. 900 | 1,000 አመታት | 10 |
ታሲተስ | አናልስ | ዓ.ም. 100 | ዓ.ም. 1100 | 1,000 አመታት | 20 |
ፕሊኒ ሴኩንዶስ |
ተፈጥሯዊ ታሪክ |
ዓ.ም. 61-113 | ዓ.ም. 850 | 750 አመታት | 7 |
አዲስ ኪዳን | ዓ.ም. 50-100 | ዓ.ም. 114 (ክፍሎች) ዓ.ም. 200 (መጽሐፍት) ዓ.ም. 325 (ሙሉ አዲስ ኪዳን) |
+50 አመታት 100 አመታት 225 አመታት |
5366 |
*McDowell, Josh. The New Evidence that Demands a Verdict (Thomas Nelson Publishers, 1999), p. 55.
ከአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች መካከል አራቱ እያንዳንዳቸው በኢየሱስ ሕይወት ላይ የራሳቸውን የሕይወት ታሪክ ጽፈዋል። እነዚህ አራቱ ወንጌላት ይባላሉ፣ የአዲስ ኪዳን የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት። የታሪክ ጸሐፊዎች የሕይወት ታሪክ አስተማማኝ መሆኑን ለመለየት ሲሞክሩ “ስለ ዚህ ሰው ተመሳሳይ ዝርዝሮችን የሚያመለክቱ ሌሎች ምንጮች ምን ያህል ናቸው?” ብለው ይጠይቃሉ።
ይህ እንዲህ ነው የሚሰራው። የፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ. ኬኔዲን የሕይወት ታሪክን እየሰበሰባችሁ እንደሆነ አስቡ። ቤተሰቡን፣ ፕሬዚዳንታዊ ቆይታውን፣ ሰውን ጨረቃ ላይ ሲያወጣ ግቡን እና የኩባን ሚሳይል ቀውስን አያያዙ የሚገልጹ ብዙ የሕይወት ታሪኮችን ያታገኛላችሁ። ኢየሱስን አስመልክቶ ስለ ህይወቱ ተመሳሳይ እውነታዎችን የሚዘግቡ በርካታ የሕይወት ታሪኮችን እናገኛለን? አዎን። ስለ ኢየሱስ እውነታዎች እና በእያንዳንዱ የሕይወት ታሪክ ውስጥ የት እንደሚያገኙ እነሆ።
ማቴዎስ | ማርቆስ | ሉቃስ | ዮሐንስ | |
ኢየሱስ ከድንግል ተወለደ | 1:18-25 | - | 1:27፣ 34 | - |
በቤተልሔም ተወለደ | 2:1 | - | 2:4 | - |
በናዝሬት ኖረ | 2:23 | 1:9፣ 24 | 2:51፣ 4:16 | 1:45፣ 46 |
ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ ተጠመቀ | 3:1-15 | 1:4-9 | 3:1-22 | - |
የፈውስ ተአምራትን አደረገ | 4:24፣ ወዘተ | 1:34፣ ወዘተ | 4:40፣ ወዘተ | 9:7 |
በውኃ ላይ ተራመደ | 14:25 | 6:48 | - | 6:19 |
አምስት ሺህ ሰዎችን በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ መገበ |
14:7 | 6:38 | 9:13 | 6:9 |
ኢየሱስ ተራ ሰዎችን አስተማረ | 5:1 | 4:25፣ 7:28 | 9:11 | 18:20 |
ከማህበረሰቡ ከተገለሉ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳለፈ | 9:10፣ 21:31 | 2:15፣ 16 | 5:29፣ 7:29 | 8:3 |
ከሃይማኖት ልሂቃኑ ጋር ተከራከረ | 15:7 | 7:6 | 12:56 | 8:1 - 58 |
የሃይማኖት ልሂቃን እርሱን ለመግደል አሴሩ | 12:14 | 3:6 | 19:47 | 11:45 - 57 |
ኢየሱስን ለሮማውያን አሳልፈው ሰጡት | 27:1፣ 2 | 15:1 | 23:1 | 18:28 |
ኢየሱስ ተገረፈ | 27:26 | 15:15 | - | 19:1 |
ተሰቀለ | 27:26 - 50 | 15:22 - 37 | 23:33 - 46 | 19:16 - 30 |
በመቃብር ተቀበረ | 27:57 - 61 | 15:43 - 47 | 23:50 - 55 | 19:38 - 42 |
ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ለተከታዮቹ ታየ | 28:1 - 20 | 16:1 - 20 | 24:1 - 53 | 20:1 - 31 |
ከወንጌላት መካከል ሁለቱ የኢየሱስ የሕይወት ታሪኮች የተጻፉት ኢየሱስን በግል በሚያውቁ እና ከሦስት ዓመት በላይ አብረውት በተጓዙ በማቴዎስ እና በዮሐንስ ነው። ሌሎቹ ሁለቱ መጻሕፍት የተጻፉት የሐዋርያት የቅርብ ባልደረቦች በሆኑት በማርቆስና በሉቃስ ነው። እነዚህ ጸሐፊዎች ለሚያቀርቧቸው እውነታዎች ቀጥተኛ መረጃ ነበራቸው። በሚጽፉበት ጊዜ፣ ኢየሱስ ሲናገር የሰሙ፣ ሰዎችን ሲፈውስ እና ተአምራት ሲያደርግ የተመለከቱ በሕይወት ያሉ ሰዎች ነበሩ።
ስለዚህ የጥንቷ ቤተክርስቲያን አራቱን ወንጌላት በቀላሉ የተቀበለችው በኢየሱስ ሕይወት ላይ ቀድሞውኑም ከነበረው የታወቀ እውነት ጋር ስለተስማሙ ነው።
እያንዳንዱ የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስ እና የዮሐንስ ወንጌላት እንደ የዜና ዘገባዎች የጊዜውን ክስተቶች በእውነተኛ ክትትል፣ እያንዳንዳቸው ከራሳቸው አመለካከት ጽፈውት ይነበባል። መግለጫዎቹ ለእያንዳንዱ ጸሐፊ ልዩ ቢሆኑም፣ ግን እውነታዎቹ የሚስማሙ ናቸው።
ከወንጌላት በአንዱ ከተጻፈው በጥቂቱ ለማየት ይህንን ይጫኑ
ከወንጌላት በአንዱ ከተጻፈው በጥቂቱ...
ወንጌላት እንደ ተጨባጭ እውነታ፣ "እንደዚህ ነበር" በሚል መልክ ቀርበዋል። ኢየሱስ ተአምር ስለማድረጉ የሚገልጹት ዘገባዎች እንኳን ያለ ስሜታዊነት ወይም ምስጢራዊት የተጻፉ ናቸው። አንዱ ዓይነተኛ ምሳሌ በሉቃስ ምዕራፍ 8 ላይ ኢየሱስ አንዲትን ልጅ ከሞት ያስነሳበት ዘገባ ነው። በገለጻው ውስጥ ዝርዝሮቹን እና ግልፅነቱን ልብ በሉ:
ሕዝቡ ሁሉ መምጣቱን ይጠባበቁ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ በደስታ ተቀበሉት። በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵራብ አለቃ መጥቶ፣ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ለመነው፤
ይህን ልመና ያቀረበው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ አንዲት ልጅ ስለ ነበረችው ነው፤ እርሷ በሞት አፋፍ ላይ ነበረች። ወደዚያው እያመራ ሳለ፣ ሕዝቡ በመጋፋት እጅግ ያጨናንቀው ነበር። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ ሊፈውሳትም የቻለ ማንም አልነበረም።
እርሷም ከበስተ ኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ይፈስ የነበረው ደሟም ወዲያው ቆመ።
ኢየሱስም፣ “የነካኝ ማነው?” አለ። ሁሉም መንካታቸውን በካዱ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከቦህ በግፊያ እያስ ጨነቀህ ነው” አለው። ኢየሱስ ግን፣ “አንድ ሰው ነክቶኛል፤ ኀይል ከእኔ እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አለ።
ሴትዮዋም ሳትታወቅ መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ፣ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ ፈውሶሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።
ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ፣ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታድክመው” አለው። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፣ “አይዞህ አትፍራ፤ እመን ብቻ፤ ልጅህ ትድናለች” አለው።
ወደ ኢያኢሮስ ቤት ሲገባም ከጴጥሮስ፣ ከዮሐንስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከልጅቱ አባትና እናት በቀር ማንም አብሮት እንዲገባ አልፈቀደም። በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ሁሉ እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን፣ “አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹም መሞቷን ስላወቁ ሣቁበት።
የልጅቷም መንፈስ ተመለሰ፤ ወዲያውም ተነሥታ ቆመች፤ ኢየሱስም የሚበላ ነገር እንዲሰጧት አዘዛቸው። ወላጆቿም ተደነቁ፤ እርሱ ግን የሆነውን ነገር ለማንም እንዳያወሩ አዘዛቸው።
ልክ እንደሌሎች የኢየሱስ ፈውሶች ዘገባ፣ ይህም የእውነተኛነት ቀለበት አለው። ልብ ወለድ ቢሆን ኖሮ በተለየ መልኩ የሚፃፉ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ፣ በልብ ወለድ ጽሁፍ ውስጥ አንድ ነገር እየሆነ በሌላ ነገር መቋረጥ አይኖርም። ልብ ወለድ ቢሆን በሐዘን ውስጥ የነበሩ ሰዎች በኢየሱስ ንግግር ባልሳቁ ነበር፤ ምናልባት ይቆጡ ወይም ይጎዱ ይሆናል እንጂ አይስቁም። ልብ ወለድ ጽሑፍ ቢሆን፣ ኢየሱስ ወላጆቿን ስለዚህ ጉዳይ ዝም እንዲሉ ያዝዝ ነበር? ፈውሱ ትልቅ ነጥብ ያመጣል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ። እውነተኛ ሕይወት ግን ሁልጊዜ ለስላሳ አይደለም። መሰናክሎች አሉ። ሰዎች ያልተለመደ ምላሽ ይሰጣሉ። ኢየሱስ ይህንን ወላጆቿ እንዳያስተላልፉ ያልፈለገበት የራሱ ምክንያቶች አሉት።
የወንጌላት ትክክለኛነት ከሁሉ የተሻለው ፈተና ለራሳችሁ ማንበብ ነው። የእውነተኛ ክስተቶች ዘገባ ይመስላል ወይንስ ተረት? እውነት ከሆነ እግዚአብሔር ራሱን ገልጦልናል ማለት ነው። ኢየሱስ መጥቷል፣ ኖራል፣ አስተምሯል፣ አነቃቅቷል እንዲሁም ቃላቱን ዛሬ ለሚያነቡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወትን አምጥቷል። ኢየሱስ በወንጌላት የተናገረውን ብዙዎች እውነተኛ ሆኖ አግኝተዋል - “እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።” (ዮሐንስ 10፥10)።
ከኢየሱስ ሞት እና ትንሣኤ በኋላ በነበሩት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ስለ ኢየሱስ የተጻፉ የሕይወት ታሪኮች አያስፈልጉም ነበር። በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ ሁሉ የኢየሱስ ምስክሮች ነበሩ፣ አገልግሎቱንም ጠንቅቀው ያውቃሉ።6
ሆኖም፣ የኢየሱስ ዜና ከኢየሩሳሌም ባሻገር ሲሰራጭ እና የአይን እማኞች በቀላሉ ተደራሽ በማይሆኑበት ጊዜ፣ ስለ ኢየሱስ ሕይወት እና አገልግሎት ለሌሎች ለማስተማር የጽሑፍ ዘገባዎች ያስፈልጉ ነበር።
ስለ ኢየሱስ የበለጠ ማወቅ ከፈለጉ፣ ይህ ጽሑፍ የሕይወቱን ማጠቃለያ ይሰጥዎታል - ከጭፍን እምነት ያለፈ።
የጥንቷ ቤተክርስቲያን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን እንደተፃፈች ወዲያውኑ ተቀበለች። ጸሐፊዎቹ የኢየሱስ ወይም የቅርብ ተከታዮቻቸው ወዳጆች፣ ኢየሱስ የጥንት ቤተክርስቲያንን መሪነት በአደራ የሰጣቸው ሰዎች እንደሆኑ ቀደም ሲል ተጠቅሷል። የወንጌል ጸሐፊዎች ማቴዎስ እና ዮሐንስ ከኢየሱስ የቅርብ ተከታዮች መካከል ነበሩ። ማርቆስ እና ሉቃስ ደግሞ የሐዋርያትን ዘገባ በማግኘት የቅርብ ባልደረቦች ነበሩ።
ሌሎቹ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም የኢየሱስ ህይወት ቀጥተኛ መረጃ ነበራቸው - ያዕቆብ እና ይሁዳ በመጀመሪያ በእርሱ የማያምኑ የነበሩ የኢየሱስ ግማሽ ወንድሞች ነበሩ። ጴጥሮስ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ነበር። ጳውሎስ ክርስትናን በመቃወም እና የሃይማኖት ገዥ መደብ አባል በመሆን ጀምሮ ግን ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ በማመን የኢየሱስ ቀናተኛ ተከታይ ሆነ።
በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ዘገባዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የዓይን ምስክሮች በራሳቸው ካዩዋቸው ጋር አንድ ነበሩ።
ሌሎች መጻሕፍት ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ሲጻፉ ለቤተ ክርስቲያን ሐሰተኛነታቸውን ለመለየት አስቸጋሪ አልነበረም። ለምሳሌ፣ የይሁዳ ወንጌል የተፃፈው ይሁዳ ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ በ130-170 ዓ.ም በግኖስቲክ ኑፋቄ ነው። የቶማስ ወንጌል በ140 ዓ.ም አካባቢ የተጻፈ የሐዋርያትን ስም በተሳሳተ መንገድ የተሸከመ የሐሰተኛ መጻሕፍት ሌላ ምሳሌ ነው። እነዚህ እና ሌሎች የግኖስቲክ ወንጌሎች ከታወቁት የኢየሱስ እና የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች ጋር የሚጋጩ ሲሆኑ ብዙ ጊዜ ብዙ ታሪካዊ እና መልክዓ ምድራዊ ስህተቶች ተገኝተውባቸዋል።7
በ367 ዓ.ም አታናሲዩስ 27ቱን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በይፋ ዘረዘረ (እኛ ዛሬ የምንጠቀመውን ዝርዝር)። ብዙም ሳይቆይ ጀሮም እና አውገስቲን ይህን ተመሳሳይ ዝርዝር አሰራጭተዋል። እነዚህ ዝርዝሮች ግን ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች አስፈላጊ አልነበሩም። በአጠቃላይ መላው ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተመሳሳይ የመጻሕፍት ዝርዝር ዕውቅና ሰጥተው ይጠቀሙበት ነበር።
ቤተክርስቲያን ከግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገሮች ባሻገር እያደገች በመምጣቷ እና ቅዱሳት መጻሕፍትን መተርጎም አስፈላጊ በመሆኑ የተከፈሉ ኑፋቄዎች በራሳቸው ተፎካካሪ የቅዱሳት መጻሕፍት ብቅ ማለታቸውን ሲቀጥሉ ትክክለኛ ዝርዝር ማውጣቱ ይበልጥ አስፈላጊ ሆነ።
በሚገባ የተጠበቁ የመጀመሪያዎቹን ጽሑፎች ቅጅዎች ብቻ ሳይሆን የአይሁድም ሆነ የሮማውያን ታሪክ ጸሐፊዎች ምስክርነትም አለን።
የናዝሬቱ ኢየሱስ ብዙ ተአምራትን እንዳደረገ፣ በሮማውያን እንደተገደለ እና ከሙታን እንደተነሳ ወንጌላት ይዘግባሉ። በርካታ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ እና ስለ ተከታዮቻቸው የሚገልጸውን ዘገባ ይደግፋሉ-
የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮማ ታሪክ ጸሐፊ ቆርኔሌዎስ ታኪተስ (ከ55-120 ዓ.ም) ከጥንት እጅግ ትክክለኛ ታሪክ ጸሐፊዎች መካከል አንዱ ተደርጎ ይቆጠራል።8 ከጽሁፎቹ ውስጥ በአንዱ … የሮም ንጉስ ኔሮ ክርስቲያኖች በተባሉት ላይ ታላቅ ስቃይ እንዳደረሰ... ክርስቶስ በጥብርያዎስ የግዛት ዘመን በአንዱ አውራጃችን በጴንጤናዊው ጲላጦስ እጅ ከፍተኛ ቅጣት እንደደረሰበት ይዘግባል .... "9
ፍላቪየስ ጆሴፈስ (ከ38-100 ዓ.ም) የተባለው የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ በአይሁድ ጥንታዊ ቅርሶች መጽሐፉ ውስጥ ስለ ኢየሱስ ጽፏል። ከጆሴፈስ “ኢየሱስ ጠቢብ የነበረ፣ አስገራሚ ነገሮችን ያከናወነ፣ ብዙዎችን ያስተማረ፣ ከአይሁዶችና ከግሪክ ሰዎች መካከል ተከታዮችን ያሸነፈ፣ መሲሕ ነው ተብሎ የታመነ፣ በአይሁድ መሪዎች የተከሰሰ፣ በጲላጦስ የተሰቀለ፣ እና ከሞት እንደተነሳ የታመነ ሰው እንደነበረ እንረዳለን።"10
ሱቶኒየስ፣ ታናሹ ፕሊኒ እና ታሉስ እንዲሁ ከአዲስ ኪዳን ዘገባዎች ጋር የሚስማማ ስለ ክርስቲያናዊ አምልኮ እና ስደት ጽፈዋል።
በእርግጠኝነት ለኢየሱስ የማያደላው የአይሁድ ታልሙድ እንኳ በሕይወቱ ውስጥ ስለተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ይስማማል። ከታልሙድ “ኢየሱስ ከትዳር ውጭ እንደተፀነሰ፣ ደቀ መዛሙርት እንደሰበሰበ፣ ስለራሱ የስህተት ቃላትን እንደተናገረ እና ተዓምራትን እንዳደረገ፣ ነገር ግን እነዚህ ተአምራት የአስማት እና የእግዚአብሔር አይደሉም እንደተባሉ እንማራለን።”11
ጥንታዊ የታሪክ ጸሐፊዎች በፖለቲካ እና በወታደራዊ መሪዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን፣ ከሩቅ የሮማ ግዛት አውራጃዎች በሚገኙ ረቢዎች ላይ አለማተኮራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ በጣም አስደናቂ ነው። ሆኖም የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎች (አይሁዶች፣ ግሪኮች እና ሮማውያን) ምንም እንኳን ራሳቸው አማኞች ባይሆኑም በአዲስ ኪዳን ውስጥ የቀረቡትን ዋና ዋና ክስተቶች ያረጋግጣሉ።
አዎን። እምነት በእውነት ዋጋ እንዲኖረው በእውነታዎች ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ምክንያቱም ይህ ነው። ወደ ለንደን በረራ እየወሰዳችሁ ከሆነ አውሮፕላኑ ነዳጅ የተሞላ እና ሜካኒካል አስተማማኝነት ያለው፣ አብራሪው የሰለጠነ እና በአውሮፕላኑ ውስጥ ምንም አሸባሪዎች እንደሌሉ እምነት ይኖራችኋል። እምነታችሁ ወደ አውሮፕላኑ አስገብቷችኋል። ነገር ግን ወደ ለንደን የሚያደርሳችሁ እምነታችሁ ሳይሆን የአውሮፕላኑ፣ የአውሮፕላን አብራሪው፣ ወዘተ አስተማማኝነት ነው። ባለፉት በረራዎቻችሁ መልካም ተሞክሮ ላይ መተማመን ትችላላችሁ። ያንን አውሮፕላን ወደ ለንደን ለማድረስ ግን አዎንታዊ ተሞክሯችሁ በቂ አይሆንም። ዋናው ነገር የእምነታችሁ ማረፊያ ነው - እምነት የሚጣልበት ነው?
አዲስ ኪዳን ትክክለኛና አስተማማኝ የኢየሱስ መልእክት ነው? አዎን። አዲስ ኪዳንን ማመን እንችላለን፣ ምክንያቱም እጅግ በጣም ተጨባጭ የሆነ ድጋፍ አለው። ይህ ጽሁፍ የሚከተሉትን ነጥቦች ነክቷል - የታሪክ ምሁራን ስምምነት፣ የአርኪዎሎጂ ተመራማሪዎች ስምምነት፣ አራቱ የወንጌል ታሪኮች የተስማሙ ናቸው፣ የዋናው ጽሁፍ ቅጅዎችን ማቆየቱ አስደናቂ ነው፣ በትርጉሞቹ የላቀ ትክክለኛነት አለ። ይህ ሁሉ ዛሬ የምናነበው ጽሑፍ የመጀመሪያዎቹ ፀሐፊዎች በትክክሉኛው ህይወት በትክክሉኛው ቦታ የፃፉትን እና የተለማመዱትን እንደሆነ ለማመን ጠንካራ መሠረት ይሰጠናል።
ከጸሐፊዎቹ አንዱ የሆነው ዮሐንስ በጥሩ ሁኔታ ጠቅለል አድርጎ ያቀርበዋል፣ "ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፉ ሌሎች አያሌ ታምራዊ ምልክቶችን በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል።"12
በኢሜል ወደ እርስዎ ለሚመጣው የዮሐንስ ወንጌል ነፃ ጥናት እንድትመዘገቡ እንጋብዞታለን። ይህንን ይጫኑ
► | ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር |
► | ጥያቄ አለኝ |
የግርጌ ማስታወሻ: (1) Strobel, Lee. The Case for Christ (Zondervan Publishing House, 1998), p. 132. (2) The renowned Jewish archaeologist, Nelson Glueck, wrote: "It may be stated categorically that no archaeological discovery has ever controverted a biblical reference." Nelson Glueck, Rivers in the Desert: History of Negev. Jewish Publication Society of America, Philadelphia, 1969, P. 176. (3) Strobel, p. 143-144. (4) Geisler, Norman L. Baker Encyclopedia of Christian Apologetics (Grand Rapids: Baker, 1998). (5) McDowell, Josh. Evidence That Demands a Verdict (1972), p. 19. (6) ሐ.ሥራ 2:22, 3:13, 4:13, 5:30, 5:42, 6:14, ወዘተ. (7) Bruce, F.F. The Books and the Parchments: How We Got Our English Bible (Fleming H. Revell Co., 1950), p. 113. (8) McDowell, Josh. The New Evidence that Demands a Verdict (Thomas Nelson Publishers, 1999), p. 55. (9) Tacitus, A. 15.44. (10) Wilkins, Michael J. & Moreland, J.P. Jesus Under Fire (Zondervan Publishing House, 1995), p. 40. (11) Ibid. (12) ዮሐንስ 20:30-31