×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
እግዚአብሔርን ማወቅ

ከጭፍን እምነት ያለፈ

ኢየሱስ አምላክ ነውን? ሁሉም ዋና ዋና ሃይማኖት ያከብረዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይ ብቻ ነበርን? ወይስ አምላክ? ለማመን እነዚህን ምክንያቶች ተመልከቱ…

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በፖል ኢ. ሊትል

ተነሳሽነቱን እርሱ ወስዶ ራሱን እስካልገለጠ ድረስ እግዚአብሔር መኖሩን እና ምን እንደሚመስል በትክክል ማወቅ ለእኛ የማይቻል ነው።

የእግዚአብሔር መኖር ፍንጭ ካለ ለማየት የታሪክን አድማስ መቃኘት አለብን። አንድ ግልጽ የሆነ ፍንጭ አለ። ከዛሬ 2000 ዓመታት በፊት ፍልስጤም ውስጥ ብዙም በማይታወቅ መንደር አንድ ሕፃን በረት ውስጥ ተወለደ። ዛሬም መላው ዓለም የኢየሱስን ልደት እያከበረ ነው፣ እናም በጥሩ ምክንያት። የእርሱ ሕይወት የታሪክን አቅጣጫ ቀየረ።

ሰዎች ኢየሱስን እንዴት ይመለከቱት ነበር

“ተራው ህዝብ በደስታ ይሰሙት ነበር” እና “እንደ አይሁድ ሃይማኖት መምህራናቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን አስተምሮአቸው ስለ ነበር ነው።”1

ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ስለራሱ አስደንጋጭ እና አስገራሚ ነገሮችን መናገር መጀመሩ ታወቀ። እርሱ ከሚያስደንቅ አስተማሪ ወይም ከነቢይ እጅግ የላቀ እንደሆነ ራሱን መለየት ጀመረ። እርሱ መለኮት መሆኑን በግልፅ መናገር ጀመረ። ማንነቱን የትምህርቱ ዋና ነጥብ አደረገው።

ለተከተሉት የሰጠው በጣም አስፈላጊው ጥያቄ “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” የሚል ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መለሰ።2 ኢየሱስ አልተደናገጠም፣ ጴጥሮስንም አልገሠጸውም። በተቃራኒው አበረታታው!

ኢየሱስ ደጋግሞ “አባቴ” ሲል ይጠቅሳል፣ ሰሚዎቹም የንግግሩ ሙሉ ተጽዕኖ አገኙ። “እንግዲህ አይሁድ፣ ኢየሱስ ሰንበትን ስለሻረ ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን አባቱ በማድረግ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል በማድረጉ፣ ሊገድሉት አጥብቀው ይፈልጉት ነበር።”3 ተብሎ ተነግሮናል። በሌላ ጊዜ ደግሞ “እኔ እና አባቴ (አብ) አንድ ነን።” የሃይማኖት ባለሥልጣኖቹ ወዲያውኑ ሊወግሩት ፈለጉ። ኢየሱስ ከተአምራቱ መካከል እርሱን ለመግደል የትኛው እንዳነሳሳቸው ጠየቃቸው። እነርሱ “የምንወግርህ፣ ተራ ሰው ሆነህ ሳለህ፣ ራስህን አምላክ በማድረግ፣ የስድብ ቃል ስለተናገርህ ነው እንጂ ከእነዚህ ስለ የትኛውም አይደለም” ብለው መለሱለት።”4

ኢየሱስ ስለራሱ የተናገረው

ኢየሱስ እግዚአብሔር ብቻ ያሉትን ኃይሎች እንዳሉት በግልጽ ተናግሯል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሽባ ለሆነ አንድ ሰው “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” አለው። የሃይማኖት መሪዎቹ ወዲያውኑ ተበሳጩ። “ይህ ሰው እንዴት እንዲህ ይላል? በአምላክ ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ እኮ ነው! ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማን ኀጢአትን ሊያሰተሰርይ ይችላል?” ብለው አሰቡ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “ሽባውን፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና፣ ‘ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?”

ኢየሱስም ቀጠለ፣ “ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣ 11“ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።” ሁሉም እየተደነቁ ሰውየው ወዲያውኑ ተፈወሰ።

በተጨማሪም ኢየሱስ ይህን የመሰሉ ንግግሮችን ተናግሯል: - “እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።”5 እና “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።”6 ብዙ ጊዜም በእርሱ የሚያምን ቢኖር ኢየሱስ የዘላለም ሕይወትን እንደሚሰጣቸው ተናግሯል። “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።”7 “እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም።”8

እነዚህን የመሰሉ ንግግሮችን በመናገሩ የኢየሱስ ሕይወት በአደጋ ላይ በነበረበት ወሳኝ ወቅት፣ ሊቀ ካህናቱ ጥያቄውን በቀጥታ አቀረቡለት:- “አንተ የተባረከው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ?”

ኢየሱስም “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ።

ሊቀ ካህናቱ ፍርዱን ሰጠ፡ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? ስድቡን ሰምታችኋል።”9

ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት በጣም ቅርብ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ሰው ለእርሱ ያለውን አመለካከት ለእግዚአብሔር ካለው አመለካከት ጋር አመሳስሎታል። ስለዚህ እርሱን ማወቅ እግዚአብሔርን ማወቅ ነበር።10

እርሱን ማየት እግዚአብሔርን ማየት ነበር።11 በእርሱ ማመን በእግዚአብሔር ማመን ነበር።12 እርሱን መቀበል እግዚአብሔርን መቀበል ነበር።13 እርሱን መጥላት እግዚአብሔርን መጥላት ነበር።14 እርሱን ማክበር እግዚአብሔርን ማክበር ነበር።15

ሊሆኑ የሚችሉ ማብራሪያዎች

የክርስቶስን ንግግሮች ስንመለከት አራት አማራጮች ብቻ አሉ። እርሱ ውሸታም ነበር፣ የአእምሮ ህመምተኛ ነበር፣ አፈ-ታሪክ ብቻ ነበር ወይም እውነት ነበር።

ጥያቄው እውነቱን እየተናገረ ነበር?

ምናልባት ኢየሱስ አምላክ ነኝ ሲል እየዋሸ ይሆናል። ምናልባት እርሱ አምላክ አለመሆኑን ያውቅ ይሆናል፣ ግን ሆን ብሎ ሰሚዎቹን በማታለል ለትምህርቱ ሥልጣን ለመስጠት ይሆናል። ግን በዚህ አስተሳሰብ አንድ ችግር አለ። የእርሱን አምላክነት የሚክዱ ሰዎች እንኳን ኢየሱስ ታላቅ የሥነ ምግባር መምህር እንደሆነ ይስማማሉ። በትምህርቱ እጅግ ወሳኝ በሆነው - በማንነቱ ላይ - ሆን ተብሎ ሐሰተኛ ከሆነ ኢየሱስ ታላቅ የሥነ ምግባር አስተማሪ ሊሆን እንደማይችል ለመገንዘብ አያቅታቸውም።

ሌላው አማራጭ ደግሞ ኢየሱስ ሃቀኛ ነበር ግን በራሱ ተታልሏል። ዛሬ አምላክ ነው ብሎ ለሚያስብ ሰው ስም አለን። የአእምሮ ህመምተኛ። ነገር ግን የክርስቶስን ሕይወት ስንመለከት በአእምሮ ህመምተኛ ሰው ውስጥ የምናገኛቸው ባህሪያት እንደነበሩት ምንም ማስረጃ አናገኝም። ይልቁንም በጫና ውስጥ ትልቁን መረጋጋት እናገኝበታለን።

ሦስተኛው አማራጭ በሦስተኛው እና በአራተኛው መቶ ክፍለዘመን ቀናተኛ ተከታዮቹ እርሱ ቢሰማ እንኳን ሊደነግጥባቸው የሚችላቸውን ያልተናገራቸውን ቃላት እንደተናገራቸው አድርገው ተናግረው ይሆናል። ቢመለስ ወዲያውኑ ይገስጻቸው ነበር።

ሆኖም ይህ እውነት አይመስልም። ዘመናዊ የአርኪዎሎጂ ጥናት አራት የክርስቶስ የሕይወት ታሪኮች የተጻፉት ኢየሱስን ባዩ፣ በሰሙትና በተከተሉት ሰዎች የሕይወት ዘመን ውስጥ መሆኑን ያረጋግጣል። እነዚህ የወንጌል ዘገባዎች የኢየሱስ ምስክሮች በነበሩ ሰዎች የተረጋገጡ እውነታዎችን እና ንግግሮችን ይዘዋል።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ታዋቂ የአርኪዎሎጂ ባለሙያ ዊሊያም ኤፍ አልብራይት እንደተናገረው ወንጌላት የተጻፈው ከ70 ዓ.ም. በኋላ እንደሆነ ለማመን ምንም ምክንያት የለም። የወንጌላት የመጀመሪያ ጽሑፍ የተጻፈው በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዮሐንስ ስለነበር ነው ብዙ የተሰራጩት እና ተጽዕኖ ያገኙት።

ኢየሱስ ውሸታም፣ ወይም የአእምሮ ሕመምተኛ፣ ወይም ከታሪካዊ እውነታ ውጭ የተፈጠረ አፈ-ታሪክም አልነበረም። ብቸኛው ሌላኛው አማራጭ ኢየሱስ እኔ አምላክ ነኝ ሲል በእውነት እውነተኝነት እየነበረ መሆኑ ነው ።

ኢየሱስ አምላክ የመሆኑ ማረጋገጫ ምንድነው?

ማንኛውም ሰው እንደዚህ ነኝ ብሎ መናገር ይችላል። እግዚአብሔር ነኝ የሚሉ ሌሎች ነበሩ። እኔ አምላክ ነኝ ማለት እችላለሁ። አንተም/አንቺም አምላክ ነኝ ማለት ትችላላችሁ፣ ግን ሁላችንም መመለስ ያለብን ጥያቄ “ንግግራችንን ለማረጋገጥ ምን ማረጋገጫዎችን እናመጣለን?” የሚል ነው። በእኔ ሁኔታ የእኔን ንግግር ስህተት ለማግኘት አምስት ደቂቃ አይፈጅባችሁም። የእናንተንም ስህተት ለማግኘት ብዙ ተጨማሪ ጊዜ አይወስድ ይሆናል።

ወደ ናዝሬቱ ኢየሱስ ሲመጣ ግን እንዲህ ቀላል አይደለም። ንግግሮቹን ለመደገፍ ማረጋገጫ ነበረው። እንዲህ አለ፣ “እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ።”16

የኢየሱስ ሕይወት

ከንግግሮቹ ጋር የተጣጣመ ሥነ ምግባራዊ ባህሪ ነበረው። የሕይወቱ ጥራት ታላቅ ስለነበር “ከእናንተ ስለ ኀጢአት በማስረጃ ሊከሰኝ የሚችል አለን?”17 ብሎ ጠላቶቹን መጠየቅ ችሏል። ኃጢአቶቹን ሊጠቁሙ ለሚፈልጉ ሰዎች ቢናገርም በባህሪው ውስጥ ጉድለት ስላልነበረ ዝምታ ነበር መልሳቸው።

ኢየሱስ በሰይጣን መፈተኑን እናነባለን፣ ግን በእርሱ በኩል የኃጢአት ኑዛዜን በፍፁም አንሰማም። ተከታዮቹን እንዲያደርጉ ቢነግራቸውም እርሱ ግን ይቅርታን በፍፁም አልጠየቀም።

ይህ በኢየሱስ በኩል ምንም ዓይነት የሞራል ውድቀት ስሜት አለመኖሩ በዘመናት ሁሉ ከቅዱሳንን እና ከጻድቃን ተሞክሮ የሚለይ መሆኑ እጅግ የሚያስገርም ነው። ወንዶችና ሴቶች ወደ እግዚአብሔር ሲቀርቡ፣ በራሳቸው ውድቀት፣ ብልሹነት እና ጉድለቶች የበለጠ ይጨነቃሉ። አንድ ሰው ወደ ታላቅ ብርሃን በጣም በቀረበ ቁጥር፣ መታጠብ እንደሚያስፈልገው በበለጠ ይገነዘባል።

በተጨማሪም ከልጅነታቸው ጀምሮ የኃጢአትን ሁሉን አቀፋዊነት እንዲያምኑ የተማሩት ዮሐንስ፣ ጳውሎስና ጴጥሮስ ሁሉም ስለ ክርስቶስ ኃጢአት የለሽነት መናገራቸው አስደናቂ ነው። “እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።”18

ኢየሱስን ለሞት የፈረደበት ጲላጦስ እንኳን “ምን ክፉ ነገር አድርጎአል?” ሲል ጠየቀ። ጲላጦስ ሕዝቡን ካዳመጠ በኋላ “እኔ ከዚህ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ ከእንግዲህ ኀላፊነቱ የራሳችሁ ነው” ሲል ደመደመ። ሕዝቡ ያለማቋረጥ ኢየሱስን እንዲሰቀል ጠየቁት (ስለስድብ፣ አምላክ ነኝ ስላለ)። የክርስቶስን ስቅለት የረዳው ሮማዊው መቶ አለቃ “ይህስ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” ብሏል።19

የኢየሱስ ተአምራት - በሽተኞችን ፈውሷል

ኢየሱስ ኃይሉን እና ርህራሄውን ሁልጊዜ አሳይቷል። አንካሶችን እንዲራመድ፣ ዓይነ ስውራን እንዲያዩ አደርጓል፣ በበሽታም የያዙትን ፈውሷል።

ለምሳሌ፣ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረ አንድ ሰው ከቤተመቅደስ ውጭ የተቀመጠ የታወቀ ለማኝ እንደሆነ በሁሉም ዘንድ ይታወቅ ነበር። ኢየሱስ ከፈወሰው በኋላ የሃይማኖት ባለሥልጣኖቹ ለማኙን ስለ ኢየሱስ ጠየቁት። ሰውየው መለሰ "አንድ የማውቀው ነገር ቢኖር ዕውር ነበርኩ አሁን ግን አያለሁ!" እነዚህ የሃይማኖት ባለሥልጣናት ይህንን ፈዋሽ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንዴት እንዳላወቁት ሊረዳ አልቻለም። “ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም።”20 ለእርሱ ማስረጃው ግልጽ ነበር።

ተፈጥሮን መቆጣጠር ይችል ነበር

በተጨማሪም ኢየሱስ በተፈጥሮ በራሱ ላይ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል አሳይቷል። በገሊላ ባሕር ላይ ኃይለኛውን ነፋስ እና የሚናወጠውን ማዕበል እንዲረጋጋ አዘዘ። በጀልባው ውስጥ የነበሩት በጣም ደንግጠው “ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።21 በሠርግ ላይ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠ። በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሳ ጀምሮ 5,000 ሰዎችን መገበ። በሐዘን ላይ ያለችን መበለት ልጅ ከሞት በማስነሳት አንድያ ልጅዋን መልሶ ሰጣት።

የኢየሱስ ወዳጅ አልዓዛር ሞቶ ከተቀበረ አራት ቀናት ሆኖት ነበር። ኢየሱስ ግን “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” አለው። እናም በአስደናቂ ሁኔታ ከሞት አስነሳው፣ ብዙዎችም ተመለከቱ። ጠላቶቹ ይህንን ተአምር አለመክዳቸው በጣም ወሳኝ ነው። ይልቁንም ኢየሱስን ለመግደል ወሰኑ። “እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል።”22

ኢየሱስ እንደተናገረው አምላክ ነውን?

የኢየሱስ አምላክነት ከሁሉ የላቀው ማስረጃው ከሙታን መነሳቱ ነው። ኢየሱስ በሕይወቱ ሂደት አምስት ጊዜ እንደሚሞት፣ በምን መንገድ እንደሚገደል፣ ከተቀበረ ከሶስት ቀናት በኋላ ከሙታን እንደሚነሳ በግልፅ ተንብዮአል።

በእርግጥ ይህ ታላቁ ፈተና ነበር። ለማጣራት የቀለለ ንግግር ነበር። ይሆናል ወይም አይሆንም። እርሱ የገለጸውን ማንነቱን ያረጋግጣል ወይም ያጠፋዋል። እናም ለእናንተ እና ለእኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፣ የኢየሱስ ከሙታን መነሳት እንደነዚህ ያሉትን ንግግሮች ያረጋግጣል ወይም አስቂኝ ያደርጋቸዋል፡

"መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።"23 "እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም።"24 በእርሱ ለሚያምኑ፥ "እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ..."25

ስለዚህ በራሱ ቃል ይህንን ማረጋገጫ ሰጥቷል፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል”26

ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው?

ንግግር ርካሽ ነው። ማንኛውም ሰው እንደዚህ ነኝ ማለት ይችላል። ግን ወደ ናዝሬቱ ኢየሱስ ሲመጣ ... የእርሱን ንግግር ለመደገፍ ማረጋገጫ ነበረው።

ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ የተናገረንን ሁሉ መፈፀም ይችላል። ይህ ማለት እርሱ በእውነት ኃጢአትን ይቅር ማለት ይችላል፣ የዘላለምን ሕይወት ይሰጠናል እና አሁን በዚህ ሕይወት ይመራናል ማለት ነው። እንደ እግዚአብሔር፣ አሁን እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል አውቀናል እናም እርሱን እንድናውቀው እና በግላዊ መንገድ ለእኛ ያለውን ፍቅር እንድናውቅ ለሚጠራን ጥሪ ምላሽ መስጠት እንችላለን።

በሌላ በኩል፣ ክርስቶስ ከሙታን ካልተነሳ ክርስትና ተጨባጭ ትክክለኛነት ወይም እውነታ የለውም። ሙሉ በሙሉ ሐሰት ነው። ኢየሱስ የሞተ ሰው ብቻ ይሆን ነበር። ወደ አንበሶች እየዘመሩ የሄዱት ሰማዕታትና ይህን መልእክት ለሌሎች ሲያደርሱ ሕይወታቸውን የሰጡ የዘመኑ ሚስዮናውያን ደካማ ሞኞች ነበሩ ማለት ነው።

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አረጋግጧል?

ለኢየሱስ ትንሣኤ ማስረጃ እንመልከት።

እርሱ ያደረጋቸውን ተአምራት ሁሉ በመመልከት፣ ኢየሱስ በቀላሉ የመስቀል ሞትን ማስቀረት ይችል ነበር፣ ግን መሞትን መረጠ።

ከመታሰሩ በፊት ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር “ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”27

በተያዘበት ጊዜም እንኳ የኢየሱስ ጓደኛ ጴጥሮስ እርሱን ለመከላከል ሞከረ። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስን፣ “በል ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ። ካስፈለገ አባቴን ብለምነው ከዐሥራ ሁለት ክፍለ ሰራዊት የሚበልጡ መላእክት የማይሰድልኝ ይመስልሃል?”28 አለው። እንዲህ ዓይነት ኃይል በሰማይና በምድር ነበረው። ኢየሱስ በፈቃደኝነት እስከ ሞት ድረስ ሄደ።

የኢየሱስ ስቅለት እና መቀበር

የኢየሱስ ሞት የሮማ መንግሥት ለብዙ መቶ ዓመታት ሲጠቀምበት በነበረው የተለመደ የማሰቃየት እና የሞት መንገድ በአደባባይ በመስቀል ላይ ነበር። በኢየሱስ ላይ የመጣው ክስ ስድብ (አምላክ ነኝ ማለቱ) ነበር። ኢየሱስ ለኃጢአታችን ለመክፈል ነው ብሏል።

ኢየሱስ የብረት ወይም የአጥንት ቁርጥራጮች ጫፉ ላይ ባሉት ባለብዙ ገመድ ጅራፍ ነበር የተገረፈው። ረዥም እሾህ ያለበት አክሊል በራሱ ላይ ተመታ። ከኢየሩሳሌም ውጭ ወደሚገደልበት ኮረብታ እንዲራመድ አስገደዱት። እጅ እና እግሮቹን በምስማር እየቸነከሩ በእንጨት መስቀል ላይ አንጠለጠሉት። በዚያ ተንጠልጥሎ በመጨረሻ ሞተ። መሞቱን ለማረጋገጥ በጦር ጎኑን ወጉት።

የኢየሱስ አካል በእርጥብ ቅመማ ቅመም በተሸፈነ ማድረቂያ በፍታ ተጠቅልሎ ከመስቀል ላይ ወረደ። አስከሬኑ በከባድ ዓለት መቃብር ውስጥ ተቀበረ፣ የመግቢያውን ደህንነት ለማስጠበቅ በጣም ትልቅ ድንጋይ ተንከባሎበት ነበር።

ኢየሱስ በሦስት ቀናት ውስጥ ከሞት እንደሚነሳ መናገሩን ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር። ስለዚህም በመቃብሩ በር ላይ የሰለጠኑ የሮማ ወታደሮችን ዘብ አስቀመጡ። የመንግሥት ንብረት መሆኑን የሚገልፅ የሮማን ማኅተም ከመቃብሩ ውጭ ላይም አኖሩ።

ከሶስት ቀናት በኋላ መቃብሩ ባዶ ነበር

ይህ ሁሉ ቢሆንም ከሶስት ቀናት በኋላ መቃብሩን ያተመው ድንጋዩ ከመቃብሩ ጥቂት ርቆ በሚገኝ ስፍራ ላይ ተገኘ። አስከሬኑ አልተገኘም። በመቃብሩ ውስጥ ስጋው የሌለበት የመቃብር ጨርቆች ብቻ ነበር የተገኙት።

የኢየሱስ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ተከታዮች መቃብሩ ባዶ እንደነበረና አስከሬኑም እንደጠፋ መስማማታቸውን ማወቅ ወሳኝ ነው።

በመጀመሪያ የተሰራጨው ማብራሪያ ደቀ መዛሙርቱ ጠባቂዎቹ በተኙበት ጊዜ ሬሳውን መስረቃቸው ነበር። ይህ ትንሽ ትርጉም ይሰጣል። ይህ ሙሉ በሙሉ የሰለጠኑ የሮማውያን ወታደሮች ጥበቃ ነበር እናም በስራ ላይ መተኛት በሞት ያቀጣ ነበር።

በተጨማሪም፣ ኢየሱስ ሕያው እንደሆነ፣ ከሞት እንደተነሳ በማወጃቸው እያንዳንዳቸው ደቀ መዛሙርት ተሰቃይተው ይገደሉ ነበር (በተናጠል እና በተለያዩ አካባቢዎች)። ሐሰት ቢሆን እንኳን ወንዶችና ሴቶች እውነት ነው ብለው ስላመኑት ነገር ይሞታሉ። ነገር ግን ውሸት እንደሆነ ለሚያውቁት ነገር አይሞቱም። አንድ ሰው እውነቱን ከተናገረ ሊሞት ሲል ነው።

ምናልባት ባለሥልጣኖቹ አስከሬኑን ወስደውት ሊሆን ይችል ይሆናል? ይህም ደግሞ ደካማ ሀሳብ ነው። ሰዎች በእርሱ እንዳያምኑ ነበር ኢየሱስን የሰቀሉት። የክርስቶስን አካል ቢኖራቸው ኖሮ በኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ላይ ሊያሳዩት ይችሉ ነበር። በአንድ ጊዜ ክርስትናን በተሳካ ሁኔታ ያጠፉ ነበር። ይህን አለማድረጋቸው የኢየሱስ ስጋ እንዳልነበራቸው ግልፅ ምስክርነት ይሰጣል።

ሌላው አማራጭ ሴቶቹ (የኢየሱስን ባዶ መቃብር መጀመሪያ ላይ የተመለከቱት) ተረብሸው እና በሀዘን ተሸንፈው ማለዳ መንገዳቸውን ስተው ወደ የተሳሳተ መቃብር ሄደ ነው። በጭንቀታቸው መቃብሩ ባዶ ስለነበረ ክርስቶስ እንደተነሳ አሰቡ። ግን ዳግሞ ሴቶቹ ወደ የተሳሳተ መቃብር ከሄዱ ለምን የካህናት አለቆች እና ሌሎች የእምነት ጠላቶች ወደ ትክክለኛው መቃብር ሄደው አስከሬኑን አላመጡም?

ሐሰት ቢሆን እንኳን ወንዶችና ሴቶች እውነት ነው ብለው ስላመኑት ነገር ይሞታሉ። ነገር ግን ውሸት እንደሆነ ለሚያውቁት ነገር አይሞቱም።

አንድ ሌላ አማራጭ ደግሞ አንዳንዶች “ራስን የመሳት ሀሳብ” ብለው የሚጠሩት ነው። በዚህ አመለካከት ክርስቶስ በእውነት አልሞተም። በስህተት እንደሞተ ሪፖርት ተደርጎ ነበር፣ እውነቱ በድካም፣ በህመም እና በደም መፍሰስ ራሱን ስቶ ነገር ግን በመቃብሩ ቅዝቃዜ ውስጥ እንደገና ነቃ። (መሞቱን በሕክምናው ለማረጋገጥ ጎኑን በጦር እንደወጉት መዘንጋት የለበትም።)

ነገር ግን ክርስቶስ ከነሕይወቱ እንደተቀበረ እና ራሱን ስቶ እንደነበር ለአፍታ እናስብ። ያለ ምግብ እና ውሃ ወይም ያለ ምንም ዓይነት ትኩረት እርጥበታማ በሆነ መቃብር ውስጥ ለሦስት ቀናት በሕይወት ይቆያል ብሎ ማመን ይቻላልን? ከተቀበረበት ልብስ ራሱን ለማውጣት፣ ከመቃብሩ በር ላይ ከባዱን ድንጋይ ለማንከባለል፣ ሮማውያኑን ወታደሮች ለማሸነፍ እና በምስማር በተወጉት እግሮች ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ለመጓዝ የሚያስችል ጥንካሬ ነበረው? ይህም እንዲሁ ትንሽ ትርጉም ይሰጣል።

ሆኖም፣ የኢየሱስን አምላክነት ለተከታዮቹ ያሳመነው ባዶው መቃብር ብቻ አይደለም።

ባዶ መቃብር ብቻ አይደለም

ያ ብቻ ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሳ፣ ሕያው እንደሆነ እና እግዚአብሔርም እንደሆነ አላሳመናቸውም። ያሳመናቸው ኢየሱስ በአካል፣ በሥጋ የተገለጠባቸው እና ከእነርሱ ጋር የበላባቸው እና ያናገራቸው ጊዜያት ናቸው። የተለያዩ ስፍራዎች፣ የተለያዩ ጊዜያት፣ ለተለያዩ ዓይነት ሰዎች። ከወንጌል ጸሐፊዎች መካከል አንዱ የሆነው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ብሏል “ከሕማማቱም በኋላ ራሱ ቀርቦ ሕያው መሆኑን፣ ለእነዚሁ በብዙ ማስረጃ እያረጋገጠላቸው አርባ ቀንም ዐልፎ ዐልፎ እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው።”29

እነዚህን እንደቅዠት መቁጠር ትርጉም አይሰጥም። አንደኛው ምክንያት የተለያዩ አካባቢዎች፣ ጊዜያት እና ሰዎች መሆናቸው ነው። ግን ደግሞ፣ ቅዠቶች እንዲከሰቱ አንድ ሰው በእውነት የሌለ ነገርን እንደሆን በጣም ማመን መፈለግ አለበት።

ለምሳሌ፣ ልጇን በሞት ያጣች እናት በየቀኑ ከሰዓት 9፡30 ላይ ከትምህርት ቤት እንደሚመለስ ታስታውስ ይሆናል። እርሱን እስክታገኘው ድረስ እና ከእርሱ ጋር እስክታወራ ድረስ ሁልጊዜ ከሰዓት በኋላ በሩ ላይ ሆና ትጠብቅ ይሆናል። ከእውነታው ተራርቃለች።

አንድ ሰው የኢየሱስን ትንሣኤ በተመለከተ በደቀ መዛሙርት ላይ የሆነው ይህ ነው ብሎ ያስብ ይሆናል። ሆኖም ግን ተቃራኒው ነው የሆነው። ኢየሱስ ከሙታን እንደተነሣ ከፈቃዳቸው በላይ እንዲያምኑ ተደርገዋል።

ኢየሱስ አምላክ ነውን?

አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ በአካል እንደገና ሕያው ስለመሆኑ ዘገባዎችን ይሰጣሉ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲሆን ቶማስ አልነበረም። ለቶማስ ሲነግሩት እንዲሁ አላመነም ነበር። በግልጽ “በምስማር የተቸነከሩትን የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፣ ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረግሁ፣ በጐኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም” አለ።

ከአንድ ሳምንት በኋላ፣ ኢየሱስ ቶማስ ባለበት እንደገና ወደ እነርሱ መጣ። ኢየሱስ ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህን ዘርጋና በጐኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤ እመን” አለው። ቶማስም መለሰ: - "ጌታዬ፤ አምላኬም!"

ኢየሱስ “አንተ ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ግን ብፁዓን ናቸው”30 አለው።

ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ይሰጥሃል

ክርስቶስ ለሕይወታችሁ ዓላማ እና አቅጣጫን ይሰጣል። “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም”31 ብሏል።

ብዙዎች ስለ የሕይወት ዓላማ አጠቃላይ እና በተለይም ደግሞ ስለራሳቸው ሕይወት በጨለማ ውስጥ ናቸው። የብርሃን ማብሪያ በመፈለግ በሕይወት ክፍል ውስጥ እየተንከራተቱ ነው። በጨለማ እና በማይታወቅ ክፍል ውስጥ ሆኖ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ይህንን የግራ መጋባት ስሜት ያውቃል። መብራቱ ሲበራ ግን የደህንነት ስሜት ይመጣል። አንድ ሰው ከጨለማ ወደ ሕይወት ብርሃን ወደ ክርስቶስ ሲወጣም እንዲሁ ነው።

ካርል ጉስታቭ ጁንግ እንዲህ ብሎ ነበር “የዘመናችን ማዕከላዊ ስፍራ ባዶነት ነው።” ልምምዶች፣ ግንኙነቶች፣ ገንዘብ፣ ስኬት፣ ዝና በስተመጨረሻ የምንፈልገውን ደስታ ያስገኛሉ ብለን እናስባለን። ግን ሁል ጊዜ ባዶነት ይቀራል። ሙሉ በሙሉ አያረኩንም። እኛ ለእግዚአብሄር ተፈጥረናል እናም በእርሱም ብቻ እርካታችንን እናገኛለን።

ኢየሱስ እንዲህ አለ፡ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም።”32

አሁን ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መጀመር ትችላላችሁ። በምድር ላይ በሕይወት እና ከሞት በኋላም በዘላለም ውስጥ እግዚአብሔርን በግል ማወቅ ትችላላችሁ። እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠን ተስፋ ይህ ነው፡

"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤"333

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ኃጢያታችንን በራሱ ላይ ወሰደ። ኃጢያታችን ከእንግዲህ በእኛና በእርሱ መካከል ገደብ እንዳይሆን፣ ስለ ኃጢያታችን ቅጣትን መረጠ። እርሱ ለኃጢአታችሁ ሙሉ በሙሉ ስለከፈለ፣ ሙሉ ይቅርታን እና ከእርሱ ጋር ግንኙነት ይሰጣችኋል።

ያንን ግንኙነት እንዴት መጀመር እንደሚችሉ እነሆ፡

ኢየሱስ እንዲህ አለ፡ "እነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።"34

አሁን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወታችሁ መጋበዝ ትችላላችሁ። ዋናው ቃላቱ አይደሉም። በጣም አስፈላጊው ነገር ለእናንተ ስላደረገላችሁ እና አሁን ስለሚሰጣችሁ ለእርሱ ምላሽ መስጠትታችሁ ነው። እንዲህ ያለ ነገር ልትሉት ትችላላችሁ፣ “ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ አምናለሁ። ስለ ኃጢአቶቼ በመስቀል ላይ ስለሞትክልኝ አመሰግናለሁ። ይቅር እንድትለኝ እና አሁን ወደ ህይወቴ እንድትገባ እጠይቃለሁ። ወደ ህይወቴ ስለመጣህ እና ከአንተ ጋር ግንኙነት ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ። አመሰግንሃለሁ።

ኢየሱስን በሕይወታችሁ ከጋበዛችሁ እርሱን በተሻለ ለማወቅ እንድታድጉ ልንረዳችሁ እንወዳለን። ልንረዳችሁ በምንችልበት በማንኛውም መንገድ ከዚህ በታች ካሉት አገናኞች አንዱን በመንካት ያግኙን።

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ማቴዎስ 7፥29 (2) ማቴዎስ 16፥15-16 (3) ዮሐንስ 5፥18 (4) ዮሐንስ 10፥33 (5) ዮሐንስ 10፥10 (6) ዮሐንስ 8፥12 (7) ዮሐንስ 5፥24 (8) ዮሐንስ 10፥28 (9) ማርቆስ 14፥61-64 (10) ዮሐንስ 8፥19፤ 14፥7 (11) 12፥45፤ 14፥9 (12) 12፥44፤ 14፥1 (13) ማርቆስ 9፥37 (14) ዮሐንስ 15፥23 (15) ዮሐንስ 5፥23 (16) ዮሐንስ 10፥38 (17) ዮሐንስ 8፥46 (18) 1ኛ ጴጥሮስ 2፥22 (19) ማቴዎስ 27፥54 (20) ዮሐንስ 9፥25፣ 32 (21) ማርቆስ 4፥41 (22) ዮሐንስ 11፥48 (23) ዮሐንስ 14፥6 (24) ዮሐንስ 8፥2 (25) ዮሐንስ 10፥28 (26) ማርቆስ 9 ፥31 (27) ዮሐንስ 10፥18 (28) ማቴዎስ 26፥52፣53 (29) ሐ.ሥራ 1፥3 (30) ዮሐንስ 20፥24-29 (31) ዮሐንስ 8፥12 (32) ዮሐንስ 6፥35 (33) ዮሐንስ 3፥16 (34) ራእይ 3፥20


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More