×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
ወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት

ሊፈርስ የተቃረበ ትዳር ተስፋ ይኖረው ይሆን?

ትዳር መፍረስ ለምን ያጋጥመዋል ፣ ደግሞስ መልካም ትዳር እንዴት ሊኖርህ ይችላል

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በዴኒስ ሬይኒ

አንድ ጊዜ አንዲት ሴት ስለ ትዳር ያላትን አስተያየት እንዲህ ብላ ነገረችኝ፤-

« ጥንድ በሆነ የርቀት ማሳያ መነጽር ምድረበዳውን ስቃኝ፣ ግንኙነትን አስመልክቶ በተለያየ ሁኔታና ደረጃ የሞቱ፣ ሊሞቱ የተቃረቡ፣ የተፋቱ ፣ የተለያዩ፣ ፣ የበሰበሱ ፣ አካላትን አያለሁ። ይህን ሁሉ ካየሁ በኋላ ለመሆኑ እኔስ ብሆን ይህን ጉዞ ለምን እጀምራለሁ? ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። »

ዛሬም ተማሪዎች የሚጠይቁት ጥያቄ ተመሳሳይ ነው። ምንም እንኳ ለዕድሜ ልክ የሚዘልቅ የፍቅር ጓደኝነት እጅግ በጣም ቢፈልጉትም ትዳርን ግን ይፈሩታል። በኒውስ ዊክ መጽሔት ላይ በአንድ መጣጥፍ ውስጥ አንዲት አዲስ ተጋቢ ሙሽራ እንዲህ አለች፣-«የወላጆቼ ትዳር ሲፈርስ አይቻለሁ፤ እኔ ራሴ ይህንን ትዳር እስከምን ድረስ ጠብቄ ማቆየት እንደምችል እርግጠኛ አይደለሁም፤ » አለች።

ከቤተሰቡ ትዳር መበላሸት የራሱን ድርሻ በኮሮጆው ውስጥ ይዞ ያልወጣ ትውልድ አይኖርም። በየአመቱ ብዙ ልጆች የወላጆቻቸው ትዳር መፍረስ ሰለባ ናቸው።

በዚህ ገጠመኝ ውስጥ ያለፉ ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች የደረሰባቸውን ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ፤

ማርታ፡- አንድ ከሰዓት በኋላ ከትምህርት ቤት ስትመለስ አባቷን የልብስ ሻንጣውን ይዞ በራቸው ላይ ታገኘዋለች። ቤተሰቡን ትቶ እየሄደ ነበር። « የኔ ማር ተመልሼ መጥቼ አይሻለሁ» ብሏት ግንባሯ ላይ ስሟት ሄደ። ከዛን ጊዜ በኋላ ዳግመኛ አላየችውም።

ርብቃ፡- ወላጆቿ አሁንም አንድ ላይ ናቸው፤ ሆኖም መላ ትኩረታቸው በሥራቸውና በሚያገኙት ትቅም ላይ ብቻ ነው። አባትና እናቷ በምትማርበት ትምህርት ቤት የወላጆች ቀን ላይ እጅግ በጣም የተወሰኑ ጊዜያት ብቻ ነው ሊገኙ የቻሉት። አሁን ደግሞ እርሷ ኮሌጅ ገብታለች። ከሁለት አንዱንም በአካል ቀርባ ያነጋገረችው እጅግ በጣም ለተመጠነ ጊዜ ነው።

ፊሊጶስ፡- መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ውስጥ በነበረበት ጊዜ አንድ ሌሊት እናትና አባቱ ከመኝታ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ሲጨቃጨቁ ይሰማል። ወዲያውኑ የዕቃ መንጓጓትና መሰባበር ይሰማል። ከዚያም ጩኸት ይከተላል። የዚህን ጊዜ ፊሊጶስ በማዕድ ቤት ውስጥ እናቱ በስለት ተወግታ ቆስላ ስትደማ ያገኛታል። ወዲያዉኑ ወደ ፖሊስ ደውሎ ፖሊሶች መጥተው አባትየውን በቁጥጥር ሥር አውለው ይወስዱታል። ፊሊጶስ እናትየውና ሁለት ታናናሽ እህቶቹ ወደ መጠለያ ተወስደው መኖር ጀመሩ። ከዛን ጊዜ አንስቶ አባትየው የት እንደሚኖር የሚያውቀው ነገር የለም።

የተሻለ ትዳር ሊኖርህ ወይም ሊኖርሽ ይችላል

ማርታ፣ ርብቃና ፊሊጶስ ያለፉበትን ሕይወት ያሳለፉ ሰዎች አጋጥመውህ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም አንተ የነሱን ዓይነት ወይም የባሰ ሕይወት ውስጥ አልፈህ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ያንተ ቤተሰብ በግጭትና ባለመጣጣም ዕረፍትና እርካታ በማጣት የተናጠ ሊሆን ይችላል። ከዚህም የተነሳ አንተም ወደፊት የትዳር ሕይወት ውስጥ ለመግባትም ሆነ ላለመግባት መወሰን ያቅትሃል፤ ምክንያቱም ወደ ትዳር ሕይወት ብትገባም በነውጥ የተሞላ ቤተሰብ እንዳይኖርህና በልጆችህም ላይ መሳቀቅ እንዳይፈጠር ትሰጋለህ። ከምትወድህ ጋር አብረህ ሕይወትህን ማቆራኘትና መኖር የሚለው ሃሳብ ሊመችህ ይችላል። ወደ ዕውነታው ስትመጣ ግን ትዳር ለአንተ የማስፈራሪያ የቆመ ምስል ሆኖ ይታይሃል። በዚህ ጊዜ ቆም ብለህ « ለመሆኑ ቤተሰቦቼ በኔ ላይ ካደረሱብኝ በደል አንጻር ያንን ሁሉ ጥሼ በማለፍ ተቋቁሜ ሰላም የሰፈነበት፣ ጤነኛና ደስተኛ ቤተሰብ መመስረት እችላለሁኝ ወይ? » ብለህ ራስህን ትጠይቃለህ።

መልሱ በግልጽ አዎ ትችላለህ የሚል ነው።

ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ በአደጋ ላይ የሚገኙ ትዳሮችን እንዳይፈርሱ የምክር አገልግሎት በሚሰጥ ድርጅት ውስጥ ስሰራ በሺህ የሚቆጠሩ ተስፋ የሌላቸውና በአደጋ ላይ የነበሩ ትዳሮች እንደገና ተንሰራርተው ሲቋቋሙ አይቻለሁ። እግዚአብሔር አምላክ በትዳር ጓደኝነት ሰበብ ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች መውጫና መጽናኛ የሚሆን የራሱ መንገድ አለው።

ችግር ቢኖርበት እንኩዋን ትዳር ይፈለጋል

ይህ ሁሉ ችግርና ሰቆቃ በትዳር ላይ እየታየበትና እየተነገረበት እያለ አሁንም ሰዎች ለምን የትዳር ሕይወት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ያሳያሉ? ምንም እንኳ ያን ያሀል ጫና የበዛበትና የትንቅንቅ ሕይወት ቢመስልም አሁንም ትዳር በጣም የሚፈለግ ከመሆኑ የተነሳ ትዳርን መሞከር የማይሻ የለም። ሉዊስ ሃሪስ በቅርቡ ባደረገው አሰሳ 96% የሚሆኑ የኮሌጅ ተማሪዎች ማግባት ይፈልጋሉ ወይም ተጋብተዋል። 97% የሚሆኑት « በጣም የተቀራረበ የቤተሰብ ህብረትና አንድነት የደስታ ምንጭ አንደሆነ ፤ » አጥብቀው ይስማሙበታል።መልካምና እስከመጨረሻ ድረስ የሚዘልቅ ትዳር የማግኘት ተስፋን ሰንቆ ሁሉም ሰው ትዳርን የመሞከር ፈቃደኝነት ይታይበታል። እና ለምንድነው ትዳር ይህን ያህል የተፈለገው?

ዕውነቱ ይህ ነው። ይኸውም ማንም ሰው ብቸኛ ሊሆን አይፈልግም.። ምንም እንኳ በራሳችን ጉዳይ ላይ ትኩረት የመስጠት፣ የማሰብ እንዲሁም የማድረግ ዝንባሌ ቢኖረንም፣ ዞሮ ዞሮ እኛን ቀርቦ የሚወደንና የሚያስብልን ሰው አጥብቀን መፈለጋችን አይቀርም። ራሳችንን ስንጠየቅ « እኔ ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ ፤ » እያልን ራሳችን በራሳችን መኖር እንደምንሻ ፍላጎት ብናሳይም ፣ ሆኖም ከሌላው ጋር በፍቅር ተጣምሮ የመኖር ጠንካራ ፍላጎት ይኖረናል።

እንደዚሁም ጾታዊ መሳሳብ ለፍቅር ጓደኝነት አስፈላጊ ቢሆንም ከአንድ ሰው ጋር የምንፈጥረው ግንኙነት ወሲብን በመፈለግ ብቻ መሆን አይኖርበትም።

ትዳር ለምን ይፈርሳል ?

እጅግ ብዙ ሰዎች በትዳር ውስጥ ለዘላለም አብረው ለመኖር ፍላጎት እያላቸው ሳለ መጨረሻቸው ወደ ፍችና ወደ ቁጣ እንዲሁም ርካታ ማጣት ውስጥ የሚገቡት ለምንድነው? ብዙዎች ስሜታቸውን መሠረት አድርገው ጠንካራ ጽኑዕ የሆነ የጋብቻ አንድነትን ለማግኘት ይጥራሉ። የብዙዎች የፍቅር ጓደኝነት በፍቅርና መቀባበል ይጀምርና አንዱ ወገን የሚጠበቀበትን እስከፈፀመ ድረሽ ብቻ ይዘልቃል። ነገሮች ሰላም ሆነው ስሜትም እንደሞቀ ሲቀጥል ባልና ሚስት አንድነታቸውን በደስታ ያጣጥሙታል። በአንዱ ወገን በኩል የሚያሳዝንና የሚያስቀይም ነገር የመፍጠሩ ሥጋትን የሚጨነቁበትን የሚያስባቸው ነገር አይሆንም። ነገር ግን ስሜት ሲቀዘቅዝ አንዱ ሌላውን ፍጽምናን ያጣውን ሰው የመውደድ አቅም ጨርሶ አይኖረውም። በዚህ ወቅት ፍላጎት አይጣጣምም፤ ይህም እርስ በርስ መጎዳዳትን ያስከትላል። አንዱ ከሌላው ራሱን ለመከላከል የራሱን ምሽግ መቆፈር ይጀምራል። አዎንታዊ የሆነ መግባባትና ንግግር ያሽቆለቁላል። ለግጭት ምክንያት የሚሆን እርስ በርስ አለመገባባትና አለመረዳት የተራራ ያህል እየገዘፈ ይሄዳል። ይህን ለቁጣና ለጭካኔ ማለፊያ ነዳጅ ሆኖ ያገለግላል። እርቅና ይቅርታ መሐል ገብቶ ይህን ዙርያ ጥምዝዝ የሆነ ችግር መፍትሄ ካልሆነው በሁለቱ መካከል የሚገኘው ፍቅር አደጋ ውስጥ ይወድቃል።

ይህ ዓይነቱ ግንኙነት ለጊዜው ማለትም ራስ ወዳድነትን የሚያጭሩ ነገሮች እስከሚከሰቱ ጊዜ ድረስ ራሱን ደብቆ የሚቆይ ግንኙነት ነው። ሆኖም ዛሬም ባይሆን ነገ ዘግይቶ ዕውነታው ፈጥጦ መውጣቱ አይቀርም። የተጣመሩት ባልና ሚስቶች አንድ የተሻለ አመለካከት ቢኖራቸውም፣ በጊዜ ሂደት የሚታየው ተግባር የሚያሳየው ግን ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉና በራሳቸው የሚኖሩ ሰዎች ሁልጊዜ ፍላጎታቸው አንድ ዓይነት ሆኖ መፍትሄ ያገኛሉ ማለት አይደለም።

ስለዚህ የተሻለና መልካም ትዳርን እነዴት ማግኘት ይቻላል?

በፍቅር ጓደኝነት ስኬታማ ለመሆን የሁለቱን ጋደኛሞች ሥራን ይጠይቃል። ሁለቱም ተጣማሪዎች የየግላቸውን ፍላጎትና ምኞት መካድ ይኖርባቸዋል። ራስ ወዳድነትን ራስን መስዋዕት አድርጎ በማቅረብ መተካት ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ከትዳር ጓደኛሞች አንዱ አንድን ነገር በቅንነት አጥጋቢ በሆነ ምክንያትም ሲያደርግ ያንን በትዕግስት ከመቀበል ይልቅ ግልፍተኝነት ይከተላል። ምክንያቱም ተፈጥሮአችን ውስጥ ያለው ራስ ወዳድነት አንጂ ራስም መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ አይደለም።

ይህ ለምን ሆነ?

የምንኖረው ፍጹም ሰዎች በሚኖሩባት ዓለም ውስጥ ቢሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር አምላክ ገና ጋብቻን ሲመሰርት እንደነበረው ጊዜ የጋብቻቸው ጣዕመ ዝማሬ አስደናቂ ሕብር በኖረው ነበር። ነገር ግን እየኖርን ያለነው ፍጹም በሆነው ዓለም ውስጥ አይደለም። ዕውነቱን ለመናገር እያንዳንዳችን በዚህ በራስ ወዳድነትና በኃጢዓት ዝንባሌ የተበከልን ነን። ኃጢዓት ማለት ምን ማለት ነው? እኛ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛውን ነገር ከማድረግ ይልቅ ትክክል ያልሆነውን ማድረግ ይቀናናል። ራስወዳድ ፣ ጎጂዎች፣ ጨካኝና መራሮች ፣ ትዕቢተኞችና ምህረት የለሾች የመሳሰሉት እንሆናለን። ስለዚህ ባልና ሚስቶች ከዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ራሳቸውን ለማውጣት ቢታገሉ አይደንቅም።

እኔ ብቻ የምፈልገው ይሁን የሚል ዝንባሌ፣ አብሮ በጋራ የመኖርን መንፈስ ይሰብራል። ይህ አሉታዊ ዑደት ይጀምርና ግንኙነቱ ደፍርሶ ትዳርም እስከሚፍረከረክ ድረስ ያለርህራሄ ይቀጥላል።

ኮምጨጭ ብለን አንጋፈጠው። ትዳሩ የመጽናት ዕድሉን እንዳያጣ ሌላውን እንድንወድ የሚያስችለንን፣ በውስጣችን ሰርጾ መግባት ያለበት እርዳታ ያስፈልገናል።

የእኛ ራስ ወዳድነትና የሃጢዓተኝነት ባህርይ ባል ከሚስቱ ወይንም ሚስት ከባሏ ብቻ አይደለም የሚለየው። የረድኤታችን ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔርም ይለየናል። እግዚአብሔር አምላክ እንደ ጋብቻ ጀማሪና ቀራጺ የፍቅር ጓደኝነትም እንዴት እንደሚዘልቅና እስከመጨረሻ ድረስ መጓዝ እንደሚችል የሚያውቀው እርሱ ራሱ ብቻ ነው። እርሱ በቅድሚያ ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንዲኖረን ይፈልጋል። ከዛም ከእርሱ መመሪያን እንድናገኝ ይፈልጋል።

እግዚአብሔር አምላክ ረድኤቱን የሚልክልን በየዕለቱ ለሚያጋጥሙን ተግዳሮቶችና ችግሮች ብቻ አይደለም ፤ ከዚህ በፊት ለደረሱብንና ለሰበሰብናቸው ጉዳቶችና ስብራቶች አንዲሁም ቁስሎች ጭምር ነው ፈውስን የሚሰጠን። ለምሣሌ በጉርምስናችን ወቅት በተሳሳተ ምርጫ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ከገባንበት ስህተትና ጥፋት ነጻ በማውጣት ያነጻናል። አግዚአብሔር አምላክ በርሱ ልጅነታችን ልናገኘው የሚገባውን ጥቅምና መብት እንድንጠቀምበት አጥብቆ ይፈልጋል። አንዱም መብታችን በትዳራችን ውስጥ የእርሱን መለኮታዊ ረድኤት መጠየቅና ማግኘት ነው።

ይህንን ዕውነታ በሁለት ባልና ሚስቶች ሁኔታ ውስጥ በምሣሌ ማሳየት እፈልጋለሁ። በመጀመሪያም ሁኔታ፣ ባልና ሚስቶቹ ( ሰላማዊትና ሰለሞን ብያቸዋለሁ ) በሕይወታቸው ውስጥ ታዳጊ የሆነው የእግዚአብሔር አምላክ ረድኤትን ዋጋ አልሰጡትም። በሁለተኛው ሁኔታቸው ደግሞ ሰላማዊትና ሰለሞን ከራሳቸው ግንኙነት በተጨማሪ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ግንኙነት አላቸው።

ሁኔታ አንድ ፡ ትዳር ለምን እንደሚፈርስ ማሳየት

ቅዳሜ ጥዋት ነው ሰለሞን ከጓደኞቹ ጋር ጎልፍ መጫወት ይፈልጋል። ከመኝታው ተነስቶ ለባለቤቱ ለሰላማዊት እንደሚሄድና እስከ አሥር ሰዓት ድረስ እንደማይመለስ ይነግራታል። ሰላማዊትም ተቀብላ በጣም እየተነጫነጨች « ዛሬ ሽርሽር እንደምንሄድ ተነጋግረን ነበር አሁን ታዲያ ምን ተገኘ ይህን ሃሳብ ሚያስለውጥ ?» ትለዋለች።

እርሱም በጣም በጩኸት መልሶ « በፍጹም እንሄዳለን አላልኩሽም። ለማንኛውም እኔ ጎልፍ ከተጫወትኩ ሁለት ሳምንት አልፎኛል፤ ዛሬ ቀኑ ብራና ደስ የሚል ቀን ነው፤ ስለዚህ ሄጃለሁ፤ » ብሎ በሩን ወደ ኋላ በጣም ዘግቶ ሄደ።

ሰላማዊት በጣም ተጎዳች፤ ባለችበት ትንሽ ካለቃቀሰች በኋላ በንዴት እየተወራጨች አጠገቧ ያለውን ትራስን ሌሎችንም እቃዎች እያነሳች መወርወር በክፍሉ ውስጥ ጀመረች። « ቆይ አሳይሃለሁ ! እኔ አይደለሁም !» እያለች የዛቻውን መዐት ለብቻዋ ታወርደው ጀመር ። ጓደኛዋን ደውላ ጠርታ አብረው ወጡና ምሣ ተገባበዙና አንዳንድ ነገሮችን ገበያ ወጥተው ገዙ። ሰላማዊት ገበያ ሄዳ ብር 1000 የሚያወጣ ልብስ ገዛች። በተጨማሪም ሰለሞንም ሲያይ የበለጠ እንዲናደድ ብላ ሌሎች ውድ የሆኑ ልብሶችንም ሸመተች። ይኼኔ የዱቤ ካርዳቸው ዕዳ ሰማይ ደረሰ።

ሰለሞንም የጎልፍ ጨዋታውን ጨርሶ ከጓደኞቹ ጋር የሚጠጣ ምና ምን ለመውሰድ ወደ ጎልፍ ክለቡ ቡና ቤት ጎራ አለ። አንዱ መጠጥ ሁለተኛውን እያስከተለ መጠጣቱ ቀጠለ። ሰለሞን በመጠጥ መሀል የቡና ቤቷ አስተናጋጅ እንዴት ቆንጆ እንደሆነች አስተዋለ። ይህች ቆንጆ አስተናጋጅ ሦስተኛውን መጠጥ እያቀረበችለት እያለ ጠጋ ብሎ በጆሮዋ አንድ ነገር ሹክ አላት። ሴቲቱ ያላትን ነገር እንዳልተቀበለች ብታስመስልም ፈቃዷን ግን በፈገግታዋና በሁኔታዋ ለመግለጽ አልተቸገረችም። በሚቀጥለው ሌላ መጠጥ ይዛ ስትመለስ፣ ባቀረበችለት መጠጥ ስር ባለው አፍ ማበሻ ለስላሳ ወረቀት ላይ የስልክ ቁጥሯ መጻፉን አየ። ሰለሞን ወዲያውኑ ወረቀቱን አንስቶ ወደኪሱ ከተተ።

ሰለሞን ቤቱ ትንሽ ፍርሃት ፍርሃት እያለው በአሥራ አንድ ሰዓት ደረሰ። ሰላማዊት ደግሞ የቴሌቪዥኑን ድምጽ ከመጠን በላይ ከፍታ ቁጭ ብላ ታያለች። የዚህን ጊዜ ዞር ሲል አዲስ የተገዙ ዕቃዎች ጥቅልል ተከምሮ ያያል። በንዴት ጦፎ ቴሌቪዥኑን ዘጋና ወደ ተከመረው ዕቃ ማመልከት ጀመረ። ሰላማዊትም ቃልህን ጠብቅ ብላ እየተመናቀረች ወደ መኝታ ቤት ገብታ በሩን አላትማ ዘጋችው። ባሉበት ሆነው ሲጨቃጨቁ አመሹና በመጨረሻም ሰለሞን እዛው ሳሎን ውስጥ ተኝቶ አደረ።

ሁኔታ ሁለት ፡ መልካምና የተሻለ ትዳር እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ለማሳየት

ቅዳሜ ጥዋት ነው ሰለሞን ከጓደኞቹ ጋር ጎልፍ መጫወት ይፈልጋል። ከመኝታው ተነስቶ ለባለቤቱ ለሰላማዊት እንደሚሄድና እስከ አሥር ሰዓት ድረስ እንደማይመለስ ይነግራታል። ሰላማዊትም ተቀብላ በጣም ተደንቃ « ዛሬ ሽርሽር እንደምንሄድ ተነጋግረን ነበርኮ ረሳኸው እንዴ ?» ትለዋለች።

እርሱም በጣም በቅሬታ መልሶ « እባክሽ ይቅርታ ሽርሽሩን ነገ ማድረግ አንችልም ? እኔ ጎልፍ ከተጫወትኩ ሁለት ሳምንት አልፎኛል፤ ዛሬ ቀኑ ብራና ደስ የሚል ቀን ነው፤ ስለዚህ ልሂድ ፤ » ብሎ በሩን ወደ ኋላ ዘግቶ ሄደ።

ሰላማዊት በጣም ተጎዳች፤ ባለችበት ትንሽ ካለቃቀሰች በኋላ በንዴት እየተወራጨች አጠገቧ ያለውን ትራስን ሌሎችንም እቃዎች እያነሳች መወርወር በክፍሉ ውስጥ ጀመረች። « ቆይ አሳይሃለሁ ! እኔ አይደለሁም !» እያለች የዛቻውን መዐት ለብቻዋ ታወርደው ጀመር ። ልክ እሷ እንደተናደደው እርሱም እንዲናደድ እየተመኘች።

ሰላማዊት በእግሯ ትንሽ ለመጓዝ ፈለገች፤ በመናፈሻው በኩል እያለፈች እያለ፣ ንዴቷና ብስጭቷ እየቀነሰላት መጣ። ወደቤቷም ስትመለስ ለመጸለይ ቻለች። « ጌታ ኢየሱስ ሆይ ሰለሞን ራስ ወዳድ ነው ብዬ ተናድጄበት ነበር። እባክህ ጌታ ሆይ እኔም ራስ ወዳድ እንዳልሆንና ቁጣዬ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆንብኝ እርዳኝ። »

ጓደኛዋን ደውላ ጠርታ አብረው ወጡና ምሣ ተገባበዙና አንዳንድ ነገሮችን ገበያ ወጥተው ገዙ። ሰላማዊት ገበያ ሄዳ አዲስ ልብስ ገዛች።

ሰለሞንም የጎልፍ ጨዋታውን ጨርሶ ከጓደኞቹ ጋር የሚባላ ሳንድዊችና የሚጠጣ ምና ምን ለመውሰድ ወደ ጎልፍ ክለቡ ጎራ አሉ። ሰለሞንም ከባንኮኒው በስተጀርባ ያለችው ልጅ ቆንጆ እንደሆነች አስተዋለ ። ሆኖም የወንድምነት ሰላምታውን በፈገግታ ለግሷት ከጓደኞቹ ጋር ወደ ምግብ ጠረቤዛው ሄዱ። በመሐል ሰለሞን ማለዳ ከቤት ሲወጣ ሰላማዊት ጨቅጫቃና ነዝናዛ ሆና ከዚህ ከሚወደው የጎልፍ ጫወታው ልታስቀረው እንደነበር አስቦ ነበር። አሁን ደግሞ ሲወጣ ያሳያት ሁኔታና ሥርዐተ አልበኝነት ምን ያህል እንደጎዳት እያሰበ ከልቡ ተጸጸተ። ደስታው ፍጹም አልነበረም።

ከዛም ድምጹን ከፍ አድርጎ « እሺ ወንድሞች ወደ ቤት መሄዴ ነው፤ ከሰላማዊት ጋር ጊዜ ማጥፋት እፈልጋለሁ። » አላቸው። ሁለቱ ጓደኞቹ አሾፉበትና ሃሳቡን ሊያስቀይሩት ሞከሩ ። ሆኖም ሰለሞን ከውሳኔው ንቅንቅ አላለም ።

ሰላማዊት ሰባት ሰዓት ላይ ቤት ስትገባ፣ ሰለሞን ቤት ገብቶ በማዕድ ቤት ጠረቤዛ አጠገብ ተቀምጦ ስታየው በጣም ገረማት። ከጎኑ ለሽርሽር የተዘጋጀ ቅርጫት በምግብና በመጠጥ ተሞልቶ ተቀምጦ አየች።

ጉዳቷ በድምጿ ውስጥ እየታወቀ «ሰለሞን ለምን በጊዜ መጣህ?» ብላ ጠየቀችው፤

ሰለሞንም «ማለዳ ስላሳየሁሽ የማይገባ ሁኔታ አዝናለሁ፤ እኔ ጎልፍ መጫወት መፈለጌን እንጂ ስለአንቺ ፍላጎት ግድ አልነበረኝም፤ ራስ ወዳድ የሆንኩ ይመስለኛል፤ ይቅር ትይኛለሽ? »

ሰላማዊት ከንፈሯን በቁጭት ነከሰች። አሁንም ጉዳቷ አልለቀቃትም። ሰለሞን ግን ዕውነትም የተጸጸተ ይመስላል። በጊዜ ጨዋታውን አቋርጦ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነበር። ሰላማዊትም « እሺ ይቅር ብዬሃለሁ ። » አለችው።

ሲሳሳሙ ሰለሞን « ቀኑን እንደገና መጀመር እንችላለን? እየመጣሁ እያለ አሁንም ሽርሽር ለመሄድ ገዜ እንዳለኝ ገምቼ የሚያስፈለገውን በፍ አዘጋጅቼአለሁ። እንሂድ? » ብሎ ጠየቃት።

ሰላማዊትም እንደፎከረችው ሰለሞንም ልታናድድ ብትፈልግም ልቧ ሊጨክን አልቻለም። ስለዚህ በፈገግታ ተሞልታ ፈቃደኝነቷን ራሷን በማነቃነቅ ገለጸችለት።

ለሰለሞንና ለሰላማዊት ቀኑ ተለወጠ። ቁጣና ንዴት ከሁለቱም ውስጥ ተጠርጎ ጸድቷል። ግንኙነታቸው ልክ ከመሬት እንደፈለቀ ምንጭ ታድሷል። በሁለቱም ሕይወት ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥራ ለይ ነበር። በቅድሚያ ራስን መስዋዕት አድርጎ ለመኖር ብርታትን ሰጣቸው። ምክንያቱም በየጊዜው ይህን ዓይነት ገጠመኝ ውስጥ ሲታለፍ ይቅር ለማለትና ይቅርታንም ለመጠየቅ ጌታ ካልረዳ ስለማይቻል ነው።

እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው ሁለቱ ሁኔታዎች በሁለት ሰዎች መካከል የሚኖረውን ውስብስብ ግንኙነት በደብዛዛውም ቢሆን ያሳያል። ሆኖም በአንድ ትዳር እንዲሁም በእያንዳንዳቸው በባልና ሚስት ሕይወት ውስጥ ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ ሁኔታዎች እንደሚለወጡ ያየነው ምሣሌ በሚገባ ያስገነዝባል። የክርስቲያን ትዳር እንዲያው በቀላሉ የመርህና የሕጎች ክምችት አይደለም፤ የክርስትና ትዳር በራሱ ሕይወት ነው። በየጊዜው ከእግዚአብሔር ጋር መስተጋብር በመፍጠር ከእርሱም መመሪያንና ኃይልን በመቀበል እንዲኖሩ ተደረጎ የተቀረጸ ሕይወት ነው።

ትዳርህ ሊፈርስ አይገባምና - የእግዚአብሔርን ቃል ስማ

የእግዚአብሔር ቃል የትዳር መፍረስን አስከፊነትና ከዚያ ይልቅ ለሌኛው ወገን በትህትና ዝቅ ብሎ የራስን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ፣ በኛና በትዳር ጓደኞቻችን መካከል ዕውነተኝነት እንዲኖር በተጨማሪም ከዝሙት ኃጢዓት በመጠበቅ ሌሎቸንም ጉዳዮች አንስቶ በግልጽ ያስተምራል። ሆኖም እንፈጽመው ዘንድ የታዘዝነውን ሁሉ አንዳችም ሳናስቀር እንፈጽመዋለን ማለት አይደለም። እንዴት ማድረግ እንደሚገባን ከእግዚአብሔር አምላክ መመሪያን ማግኘት ይኖርብናል። (ለምሣሌ ለትዳር ጓደኛ ከውሸት ይልቅ ዕውነትን መናገር በጣም ጠቃሚ ነው።) ነገር ግን በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አምላክ በግንኙነት ውስጥ የእርሱን ማህተም ለማኖር ምን ያህል ጥበበኛና አዋቂ እንደሆነ መረዳታቸው ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ነው።

ለምሣሌ እግዚአብሔር አሁንም ጋብቻ በሥጋ ከመገናኘት በፊት እንዲመጣ አጥብቆ ይናገራል። ሆኖም በተለይ በምዕራባውያን ባህል 64 በመቶ የሚሆኑት የኮሌጅ ተማሪዎች « ከጋብቻ በፊት አብሮ በመኖር መጀመር ጥሩ ሙከራ ወይም ሃሳብ ነው ።» ብለው ያምናሉ። ከእነዚህ ተማሪዎች ብዙዎቹ የወላጆቻቸውን የትዳር ገጠመኝ ተመልክተዋል። ይኸውም የወላጆቻቸው ሲፈርስ አይተዋልና የሙከራ ጋብቻ ጥሩ ሃሳብ እንደሆነ አድርገው ነው የሚቀበሉት።

ስሎነም እግዚአብሔር አምላክ ከወሲብ ልምምድ በፊት ለምን ጋብቻን እንዲሆን አደረገ? ምክንይቱ ይህ ነው። ይኸውም ስኬታማ መቀራረብ እንዲኖረን ስለሚፈልግ ነው። ሁለት ሰዎች ግንኙነታቸው ወይም ፍቅራቸው እንከን እንዳይገባበት ስጋት ውስጥ ሳይገቡ እንዴት መቀጠል ይችላሉ? በዚህ በኩል የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፤ የጋብቻ ፍች ቁጥር የሚበዛው እነዚያ ከጋብቻ በፊት አብረው መኖር በጀመሩት ባለትዳሮች መካከል እንደሆነ ነው። የእግዚአብሔር ዕውቀት ስህተት የለበትም። እርሱ ሁልጊዜ ልክ ነው። የእግዚአብሔር አመራር ሁልጊዜ የሚመጣው እርሱ ለእኛ ከሚያደርግልን ጥንቃቄና ክብካቤ አንጻር ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ወደተሻለ የጋብቻ ሕይወት ይመራሃል።

ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ከቶም ምክርን ብቻ የሚለግስ የጋብቻ አማካሪያችን እንዲሆን አይሻም፤ እኛ እርሱን እንድናውቀው፣ ከእርሱም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረንና እንድንታመንበት ይሻል። ሌላውን ከመውደዳችን በፊት የእርሱን በምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ላይ ላይ ያልተመሰረተውን ፍቅር መለማመድ እንደሚኖርብን ያስገነዝበናል።

በእርሱ ፍቅር እኛ ስንነካ እኛን ወክሎ እግዚአብሔር እራሱ አንድ የሚያስገርም ነገር በሕይወታችን ይፈጻማል፤ ራስወዳድነታችን ከሌሎች ጋር የበለጠ ለመቀራረብ ችግር እንደፈጠረብን ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል። በተለይም ቅዱስና ፍጹም ከሆነው ከእግዚአብሔር ከአምላካችን አንደለየን ደጋግመን ተመልክተናል። ምንም ዓይነት መልካም ሥራን ብንሠራና ምንም ጥረት ብናደርግ በእግዚአብሔር ዓይን ኃጢዓታችንን ይቅር ሊያሰኙልን አይችሉም። ለበደላችን ወይም ለኃጢዓታችን ተገቢው የሆነው ዋጋ ሞት ብቻ ነው። ይህም ማለትየምድር ህይወታችንም ካበቃ በኋላ ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው። ስለዚህ ይህንን ለመለወጥ በራሳችን ልናደርገው የምነችለው ነገር አይኖርም። እርሱ ፍጽምናን ይጠይቃል ። በቀላሉ የምንወጣው አይደለም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍርድ አስደናቂ ከሆነው ፍቅሩ ጋር ሆኖ እርሱ ራሱ መፍትሄውን ለገሰን።

ሰው የሆነው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢዓታችንን ዋጋ የሆነውን የሞት ቅጣት ራሱ በሕይወቱ ከፍሎ እኛን አዳነን። ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም በላይ የእግዚአብሔርን መንገድ በማስተማር ትርጉም ያለው ሕይወትን ይሰጠናል። በቅድሚያ ግን የእርሱ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ወደ ምድር የመምጣቱ ዓላማ በእኛ ፈንታ ስለኃጢዓታችን ሊሞትልን እንደሆነ ይገልጽልናል። የኔን የናንተን የሁላችንንም የዓለም ኃጢዓት አንድም ሳይቀር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ዕዳውን ከፈለ። ስለዚህ ምህረትን ከእርሱ እናገኛለን። ይቅር ተብለናል። ሞቶ ተቀብሮም ከሦስት ቀን በኋላ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ። የዓይን ምሥክሮችን ጨምሮ ብዙዎች በርሱ ሕይወታቸው የጠለወጠ ሁሉ ይህን ድንቅ ምሥክርነት በሁሉም ቦታ ይናገራሉ።

ጋብቻ በነጻምርጫ እንደሚወሰን ሁሉ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር የሚኖርህን ግንኙነት በነጻነት እንድትወስን ፈቅዶልሃል

እግዚአብሔርን ለመቀበል እኛ ልናደርገው የሚገባን ልዩ ነገር የለም። ከእርሱ ለሚኖረን ግንኙነት እርሱ ራሱ በፈቃደኝነት በነጻ የሰጠን ስጦታ ነው። ይህ በእኛ ምርጫ የሚወሰን ነው። የምህረት ስጦታውን ተቀብለን ከእርሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ ከፈለግን እንችላለን። ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤- «እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።»1 እርሱ ወደ ሕይወታችን ሊመጣ ይፈልጋል። አሁንም ቢሆን የእያንዳንዳችንን ውሳኔና ምርጫ ያከብራል። ጋብቻ እንግዲህ አስፈላጊነቱ ታምኖ በውሳኔ የሚከወን ከሆነ ይሄ ምርጫ ደግሞ የበለጠ በውሳኔ ሊጸና ይገባዋል።

ወገኔ ሆይ ! ለመሆኑ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ጋር ዘላለማዊ ግንኙነት እንዲኖርህና በሕይወትህ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ፈቃደኛ ነህን? በእርሱ መለኮታዊ ጥበብባ ዕውቀት ልትመራና ድጋፍና ብርታት እንዲሆንህ ትሻለህ?

ውሳኔህ አዎ ከሆነ አሁኑኑ ወደ ሕይወትህ ልትጋብዘው ትችላለህ። ያልተጋቡ ሙሽሮች በቅዱስ ጋብቻ ለመጣመር በጉባኤ ቀርበው ሲጠየቁ ፈቃዳቸውን አዎ አገባለሁ ብለው እንደሚያታኑ ሁሉ አንተም ጌታ ኢየሱስን ወደ ሕይወትህ ለማስገባት ያለህን ፈቃደኝነት አዎ እቀበለዋለሁ በማለት ፈቃደኝነትህን በዚህ ምሥክርነት ማጽናት ትችላለህ። ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- « እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። »2 « ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤»3 ስለሚል ልጁ መሆን ትፈልጋለህ?

እግዚአብሔር ለአንተ ያለውን ፍቅር ለማወቅና ወደ ልብህ እንዲገባ መጠየቅ ትፈልጋለህ? ይህ አንተ ራስህን ለእርሱ በምትገልጽበት ሁኔታ ይወሰናል። የሚከተለው ጸሎት እንዴት እንደምትጸልይ ሃሳብ ይሰጥሃል። « ጌታ ኢየሱስ ሆይ ታስፈልገኛለህ፤ ስለእኔ ኃጢዓት ስትል በመስቀል ላይ ስለሞትክልኝ አመሠግንሃለሁ። የሕይወቴን በር ከፍቼልህ አዳኜ አድርጌ እቀበልሃለሁ። ኃጢዓቴን ይቅር ብለህ የዘላለም ሕይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሕይወቴን ተቆጣጠርና አንተ የምትፈልገው ሰው ዓይነት አድርገኝ። አሜን። »

በቅንነትና በዕውነት ይህንን ጸሎት ጸልየህ ከሆነ ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር ግንኙነት ጀመርህ ማለት ነው። ይህ ከሆነ በኋላ በጋብቻህ ላይ ምን ዓይነት ውጤት ታያለህ? አዎ አሁን ለምን ትዳርህ እንደፈረሰ አውቀሃል። እግዚአብሔርን ምሪት መጠየቅ እንዳነብህም ተረድተሃል። መለኮታዊ ጥበብና የትዳር ጓደኛህን በዕውነተኛ ፍቅር የምትወድበትንም ኃይል እርሱ እንዲሰጥህ መጠየቅ ትችላለህ። ከዚህ በኋላ ፍቅርን የተሞላ ትዳር ሎኖርህ ይችላል። እንደማናቸውም ባልና ሚስቶች ስህተት ልትሰሩ ትችላላችሁ፤ አንዳንድ ጊዜም ትዳራችሁን ለማቆም በጭንቀት ስትደክሙ ትገኛላችሁ። ሆኖም በእግዚአብሔር ላይ እስከተደገፋችሁ ጊዜ ድረስ እርሱ ብርታት ራዕይና የትዳር ጓደኞቻችሁን ከራስ ወዳድነት ውጭ የምትወደዱበትን እንዲሁም የይቅርታን ልብን የምትለማመዱበትን ኃይል ይሰጣችኋል። ትዳራችሁም ለዘላለም ይዘልቃል።

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ዮሐ 14፥6 (2) ራዕይ 3፥20 (3) ዮሐ 1፥12


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More