×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
እግዚአብሔርን ማወቅ

የእግዚአብሔር ፍቅር ለፅንፈኛ ሙስሊሞች

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በሞሐድ ሳሌም

እኔ ምንም ነገር ሳያውቅ ዕድሜውን በሙሉ በመባዘን እነዳጠፋ ተራ ሰው ነኝ፤ የተወለድኩት በፓኪስታን ውስጥ እጅግ ባለጠጋ ከሆኑ ሙስሊም ከሆኑ ቤተሰቦች ነው። በተወለድኩ ከጥቂት ወራት በኋላ አባቴ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይዞኝ መጣ። ስድስት ዓመቴ እንደሆነኝ እናቴ በሞት ተለየችኝ። እያደግኩ ስመጣ፣ ማንም ሰው አንድ ነጥብ ላይ ሲደርስ አንዳንድ የሕይወት ጥያቄዎችን እንደሚጠይቅ ሁሉ እኔም በውስጤ ጥያቄ መጠየቅ ጀመርኩ። እዚህ ምድር ለምን መጣሁ? ለመሆኑ እግዚአብሔር በዕውነት አለ? ካለስ የት ነው የሚገኘው? ለምን አያናግረኝም? የሚሉት ጥያቄዎች ዘወትር ራሴ ለራሴ የምጠይቃቸው ጥያቄዎች ነበሩ።

ከአሥራ ሁለት ዓመቴ ጀምሮ ቁርዐንን አጥንቻለሁ። ከዛም እየጎለመስኩ ስሄድ ሌሎችንም የእስልምና መጻሕፍት አንብቤአለሁ። የነቢዩ መሐመድን የሕይወት ታሪክና፣ ሃዲስ፣ የመሳሰሉትን። እንደ አብዛኞቹ የሳዑዲ አረቢያ ሰዎች፣ ከእስልምና ዘርፎች አንዱ የሆነው የዋሃቢ ወይም አሃሊ ሃዲስ ዕምነት ተከታይ ነበርኩኝ። (ኦሳማ ቢን ላደንም የዚህ ዕምነት ተከታይ ነበር። ) የዚህ ዕምነት ተከታዮች እጅግ በጣም ፅንፈኞች ናቸው። እኔም ከእነርሱ አንዱ ነበርኩ።

የተማርኩት ወደ መንግሥተ ሰማይ ብቸኛ መግቢያ እስልምና ብቻ እንደሆነ ነው። « እንደዚህ ብታደርግ እነዚህንና እነዚያን በረከቶችቸ በሰማይ ቤት ታገኛለህ ፤ እንደዚያ ብታደርግ እነዚህንና እነዚያን በረከቶች በሰማይ ቤት ታገኛለህ።» እየተባልኩ ነው የኖርኩት። ስለዚህ እጅግ አክራሪ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ሆንኩ።

ከዕምነቴ አንጻር የማደርገው ነገር ሁሉ ትክክል እንደሆነ አምን ነበር። በሃዲስና በቁርዐን ላይ ስለተጻፈላቸው ነቢያት በዝርዝር አንብቤአለሁ። ከሌሎቹ ይልቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ብቻ ነበር ሕይወቴን የነካው። ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንደሚያምኑ ተረዳሁ። እንዴት ይህንን ነገር እንዳመኑ በጣም ደነቀኝ። ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የበለጠ ለማወቅ ፈለግሁ። ከኔ ጋር የሚማር አንድ ክርስቲያን ጓደኛ ነበረኝ። አንድ ቀን አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አገኝ እንደሆነ ጠየቅሁት። በጣም በመደነቅ ተመለከተኝና «አዝናለሁ ልሰጥህ አልችልም። » አለኝ። እኔም «ግድ የለህም በኔና ባንተ ይሁን ለማንም አላሳይም ብቻ አንድ አግኝልኝ » ብዬ አጥብቄ ለመንኩት። ሆኖም ቃሌን መጠበቅ አልቻልኩም ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በቤታችን ውስጥ እንደማነብ አባቴ አወቀ። ልክ አንዳወቀ እጅግ በጣም ተቆጣ ፤ ያለኝ ክርስቲያን ጓደኛ አንድ ብቻ እንደሆነም ያውቅ ነበር። እኔን ከአጎቴ ጋር ይዞኝ እዚያ ክርስቲያኑ ጓደኛዬ ቤት ወሰደኝና የማስጠንቀቂያውን መዐት አወረደበት። « ሁለተኛ ለዚህ ለሙስሊም ልጄ ክርስትናን እንደምትሰብክ ካወቅሁ፣ ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቃለሁ። ከዚያም ከዚህ አገር ለዘላለም እንደምትሰደድ ዕወቅ። » አለው። በጣም ደነገጥኩ ተጨነቅሁም። በጓደኛዬና በቤተሰቡ ላይ ይህን ማድረግ እንዳልነበረብኝ በማሰብ በጣም አዘንኩ።

አባቴም ከአጎቴ ጋር ሆነው ከዚያ በኋላ ቀድሞ እንደማደርገው በቀን አምስት ጊዜ እንድጸልይ ፣ ከነዚህም ውስጥ አንዱን ጸሎት በእስላም መስጊድ በመገኘት እንድጸልይ ከባድ ማሳሰቢያ ከማስጠንቀቂያ ጋር ተነገረኝ። ስለዚህ በተሰጠኝ ማስጠንቀቂያ መሠረት የተለመደው ጸሎቴን ቀጠልኩ ፣ ወደ መስጊድም እየሄድኩ እጸልይ ነበር ። ብዙዉን ጊዜ ሰው በማይኖርበት ጊዜ ወደ መስጊድ እየሄድኩ « እባክህ እግዚአብሔር ሆይ ግለጽልኝ፤ » እያልኩ አለቅስ ነበር። « እግዚአብሔር ሆይ ! ኢየሱስ ማነው? አንተስ ማነህ ?» እያልኩ በልቅሶ እጠይቅ ነበር። ብዙዉን ጊዜ በመስጊድ በጸሎት ወቅት የመስጊዱ ኢማም በአረብኛ ሲናገር (በእስልምና አረብኛ ቋንቋ የአምልኮ ቋንቋ ነው፤ በጸሎት ወቅት መጠቀም የሚገባው ይህንን ቋንቋ ነው። ) ከልቤ አላዳምጠውም ነበር። አንድ ቀን መስጊድ ውስጥ በዙሃር ( በእኩለ ቀን ጸሎት ) ወቅት እየጸለይኩ እያለሁ ስለክርስቶስ ኢየሱስ አስብ ነበር። ለጸሎት በምንሰግድበት ወለል ላይ በስግደት ላይ እያለን፣ ወለሉ ላይ አንድ እጅግ በጣም መልከ መልካም ሰው አይ ነበር። አጋጥሞኝ የማላወቀው ልምምድ ስለነበረ በጣም ደነገጥኩ። በውሃ ላይ እንዳለ ምስል ነበር እያየሁ ያለሁት። ለራሴ በሚሰማኝ ድምጽ «ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።» የሚል ድምጽ ሰማሁ።« ይህ ጌታ ነው !» አለኝ።

ይህንን ካየሁ በኋላ የበለጠ መጨነቅ ጀመርሁ። እኔ በቁርዐን የማውቀው እግዚአብሔር አምላክ አንድ ብቻ እንደሆነ ነው። ክርስቲያኖች ደግሞ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው እርሱም እግዚአብሔር አምላክ ነው ብለው ያምናሉ። ይህ ደግሞ ይቅር የማይባል ታላቅ ኃጢዓት ነው። ለዚህ ምከንያት ብቻ ጸሎቴን አቋርጬ መውጣት አልፈለግኩም። ጸሎቴን ከጨረስኩ በኋላ ስለጉዳዩ ማሰብ ጀመርኩ። ስለ ክርስቶስ ለማወቅ ያለኝ ጉጉትና ርሃብ የበለጠ እያደገ መጣ።

አባቴ ማንበቤን ካወቀ ጊዜ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ በእጄ የለም። አንድ ቀን ከጓደኛዬ ጋር በሱቆች አካባቢ ስናልፍ አንድ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥበት ሱቅ አየሁ። እኔም ያኔውኑ ገባሁና ያሆ ዶት ኮም ድረገጽ ላይ እየተመለከትኩ እያለሁ በድንገት አንድ ሃሳብ መጣብኝ፤ ፈልግ በሚለው ባዶ ቦታ ላይ «ኢየሱስ ማነው ? » የሚለውን ጥያቄ ተየብኩ። በሰጠሁት ርዕስ ላይ ሊያስረዱኝ የሚችሉ የበርካታ ድረገጾች ዝርዝር በኮምፒውተር ምሥል ማሳያ ገበታው ላይ መጡልኝ። እዚህ ባለሁበት ሁኔታ ስለኢየሱስ ክርስቶስ መረጃ መፈለጌ አስደነቀኝ። ከከፈትኩት ድረገጽ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ከምጠብቀው በላይ መረጃዎችን አገኘሁ። በብሉይ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ የተነገሩትን ትንቢቶችና በአዲስ ኪዳን ላይ አፈጻጸማቸውን ሁሉ በሚገባ ከመረጃው አገኘሁ።

በመሠረቱ እጅግ በጣም ነው የተደነቅሁት። ክርስቶስን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ እንዴት መቀበል እንዳለብኝ ፈጽሞ አላወቅኩም ነበር። ለማንኛውም በአጋጣሚም ቢሆን በኢንተርኔት ቤቷ ውስጥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በቂ መረጃ የሚሰጠውን ድረገጽ እንኳን አገኘሁት ብዬ ተደሰትኩ። ወደዚች ኢንተርኔት ቤተ ጎራ ማለት አበዛሁ፡፡ አንዳንዶቹ የክርስቲያን ድረገጾች እናንተም ምክንያቱ እንደሚገባችሁ እርግጠኛ ነኝ በይፋ ተደርሶባቸው ተዘግተዋል። አንድ ቀን እንደለመድኩት ወደ ኢንተርኔት አገልግሎት ወደማገኝበት ሱቅ በመሄድ የደህንነት ጸሎት እንዴት መጸለይ እንደሚገባኝ በመጠየቂያ ክፍት ቦታ ጥያቄዬን አቀረብኩ። ባገኘሁት መረጃ መሠረት የደህንነት ጸሎቴን ጸለይኩ ። ከዛም በጥልቀት ማሰብ ጀመርኩ። ለመሆኑ ትልቅ ኃጢዓት ፈጽሜ ይሆን? እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። ለመሆኑ ምናልባት ይህን ጸሎት በመጸለዬ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳልገባ እከለከል ይሆን.? እያልኩ መጨነቅም ጀመርኩ።

እንደልማዴ ለጸሎት ወደ መስጊድ በምሄድበት ሰዓት ሁሌ ባለፈው አይቼ የተደነቅሁትን ያንን የጌታ ኢየሱስን ምስል ማየቴን አላቋረጥኩም። አንድ ቀን ወደገበያ ቦታ በአንድ አቋራጭ መንገድ ብቻዬን እየሄድኩ ነበር። ቦታው አብዛኛውን ጊዜ ሰው የማይበዛበት ጭር ያለ ቦታ ነበር። እየሄድኩኝ እያለ አስብና አምላኬንም እጠይቅ ነበር። « እግዚአብሔር ሆይ ለመዳን አሁን ያደረግሁት ክርስቲያን መሆኔ ትክክል ነው ወይ? ወይስ እስላም እንደሆንኩ መቀጠል ነበረብኝ? » እያልኩ ከእግዚአብሔር ጋር ከልብ የሆነውን ጥያቄዬንና ጭንቀቴን ገለጽሁ፤ እየሄድኩ እያለሁ በመሐል አንድ ድምጽ ሰማሁ። «ልጄ ሆይ አሁን የወሰንከው ውሳኔ ትክክል ነው። በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ነህ።» አለኝ። አሁን ደግሞ የበለጠ መደነቅ ሆነልኝ። እንዲህ አይነት ልምምድ ፈጽሞ ለእኔ አዲስ ነበር።

ሆኖም በማልፍባቸው ነገሮችና በገጠሙኝ ሁኔታዎች ሁሉ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ አግኝቼ ማንበብ ስጀምር ብዙ ነገር ማወቅ ጀመርኩ። ከነዚህም ውስጥ ለምሣሌ፡-

« ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ ፡- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ ። » ኢሣይያስ 30,21

በተጨማሪም እንዲህ ይላል።

« ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣቸሁ ዘንድ የዘላለም ሃሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። እናንተም ትጠሩኛላችሁ ሄዳችሁም ወደእኔ ትጸልያላችሁ ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። እናንተም ትሹኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁ ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ ። » ኤርምያስ 29፥11-13

እግዚአብሔር አምላክ ለእኔ ፍጹም ታማኝ ነበር !

ከዚህ በፊት በቁርዐን ላይ እንደተማርኩት የመጀመሪያዎቹ አባትና እናታችን የሆኑት አዳምና ሔዋን በኃጢዓት ከመውደቃቸው በፊት በገነት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አውቃለሁ። (ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ተመሳሳይ ነው።) ሆኖም በቁርዐን እንደተማርኩት ከሆነ አዳምና ሄዋን ኃጢዓታቸው ይቅር እንደተባለላቸው ነው የሚናገረው። ስለዚህ ለሙስሊም ጓደኞቼ ፡- « አዳምና ሄዋን ኃጢዓታቸው ይቅር ከተባለላቸው ለምን ከገነት ተባረሩ? ይህ ማለት አዳምና ሄዋን ኃጢዓታቸው ይቅር አልተባለላቸውም ማለት ነው? » ብዬ መጠየቅ ጀመርኩ።

ቁርዐኑ በሚያረጋግጠው መሠረት ቶራ (አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት) ዛቡር (የዳዊት መዝሙር መጽሐፍ) እና ኢንጅል (ወንጌላት) የእግዚአብሔር ቃል ናቸው። እና ለምን ተለወጡ? ብዙዎች የእስልምና ሊቃውንት እንደሚሉት ከላይ የተጠቀሱት መጻሕፍት ከተለወጡ ማን ለወጣቸው? ብዬ ጠየቅሁ። እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ተለውጧል ብለው ምክንያት ስለሚሰጡ በዚህም ምክንያታቸው የበለጠ ደስተኞች ናቸው። ያም ሆነ ይህ ዕውነትን ለማወቅ ትሁት መሆንና ስለምናምነው ነገር ሁሉ ዕውነቱን መረዳትን መፈለግ ነበረብን። እኔ መጽሐፍ ቅዱሴን እያነበብኩ እግዚአብሔርን ምሪት ባልጠይቅና እርሱ በቀየሰልኝ ጎዳና ባልሄድ ዛሬ ምን እሆን ነበር? የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እግዚአብሔር መልስን እንደሚሰጥ ማንም አይሰጥም። ያ ተጨባጭ ሐቅ ነው!

ቁርዐን በሱራ አል- ባቃራ 2፥ 106 ላይ ራዕይና መገለጥ እንደሚጠፋና እንደሚወድም ወይም እንደሚረሳ ይናገራል። ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ አቋምና ሁኔታ ጋር በተቃራኒ የሚገኝ ነገር ነው።

በቶራ (በኦሪት ) መጽሐፍ በዘኁልቊ 23፥19 ላይ እንዲህ ተጽፏል። « ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። » ይላል።

እነደዚሁም በዛቡር (በመዝሙር) መጽሐፍ 31፥5 ላይ ፡-

« በእጅህ ነፍሴን እሰጣለሁ፤ የእውነት አምላክ አቤቱ ተቤዥተኸኛል። »

በኢንጅል (በወንጌል) ላይም ይህ ተጽፏል። (የዮሐንስ ወንጌል 17፥17)

« በእውነትህ ቀድሳቸው ፤ ቃልህ እውነት ነው ። »

በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ስለተሳሳተ ማስተካከያ የሰጠበትና ሙከራውን እንደገና ለማድረግ እንደ ሰው የሆነበት ቦታ አላነበብኩም።

በቁርዐን ውስጥ በነቢያት ሁሉ የእግዚአብሔር ራዕይ በተገለጠባቸው መጻሕፍት ማለትም ቶራ - የኦሪት መጻሕፍት ፣ ዛቡር - የመዝሙር መጽሐፍ ፣ ኢንጂል - የወንጌላት መጻሕፍት የዳንኤል መጽሐፍንም ጨምሮ ልናምንባቸው እንደሚገባ ያስረዳና በነዚህ የማያምን ግን ሙስሊም እንዳልሆነ ይናገራል። ሙስሊም በነበርኩ ጊዜ ሁልጊዜ ከመተኛቴ በፊት ይህን ጸሎት እጸልይ ነበር። በሱራ አልባቃራ በምዕራፍ 285 ላይ ይነበባል። ቁርዐን ለማንበብ ካልሰነፍን፣ የማይለወጠውን የእግዚአብሔር ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይገባናል።

መጽሐፍ ቅዱስን ከምድረገጽ ለማጥፋት ያልተደረገ ሙከራና ጥረት የለም። በዘመናት መካከል ብዙ ተግዳሮቶችን አልፎ እዚህ ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት አልተቻለም። ይህም የሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር አምላክ ቃል ስለሆነ እግዚአብሔር እራሱ ከጥፋት እንደጠበቀው እንረዳለን። ስለዚህ እኔም ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ እግዚአብሔር መገለጥ ለመቀበል ለማይፈልጉ መረጃ አቅርባችሁ አረጋግጡልኝ እላለሁ፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች መጽሐፍ ቅዱስን ተገቢውን ጊዜ ሰጥተው አጥንተውታል፤ በመጨረሻም የደረሱበት ድምዳሜ ግልፅ መሆኑና የተፃፈውንም በሌሎች ማስረጃዎች አረጋግጠዋል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጡት ትንቢቶች ዛሬ በዘመናችን ሁሉ እየተፈጸሙ እንደሆነ እያየን ነው። ይህ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል እውነተኝነትና የጸሐፊውን ማንነት በሚገባ የሚያረጋግጥ ነው። የዓለም ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ ዛሬ ነገና ወደፊትም ምን እንደሚሆን በሚገባ ያውቃል። እርሱ የወደፊቱን እንደ ጥንቆላ መገመት ሳይሆን ምን እንደሚሆን ያውቀዋል።

በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስና በመሐመድ መካከል ያለውን ልዩነትንም ማወቅ እጅግ አስገራሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡-

« በመጀመሪያ ቃል ነበረ ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። » (ኢንጂል) ዮሐንስ ወንጌል 1፥1

ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን አስደሳች ዜና ተባለ፣ የእግዚአብሔር ቃል፣ ከአላህ ጋር የነበረ፣ ተብሎ ስለተጠራ ሲሆን፣ መሐመድ ግን እንደዚህ አልተባለም ። ተባለ እንዴ?

ሱራ ማርያም ምዕራፍ 21 ላይ እንዲህ ተጽፏል፡- « እኔ የጌታ መልዕክተኛ ብቻ ነኝ፤ ኃጢዓት የሌለበትን ልጅ እሰጣችኋለሁ። »

ለምን ኃጢዓት የሌለበትን ልጅ ?

ሳሃይ አል ቡካሪ ሃዲስ ፥ ሃዲስ 4፥506 አቡ ሃሪያ ነቢዩ መሐመድ ያለውን እንዲህ ብሎ ነው የተረከው፤- « ከማርያም ልጅ ከኢየሱስ በቀር ፣ ማንኛውም የሰው ልጅ ልክ ሲወለድ ሰይጣን በሁለት ጣቱ ሁለቱንም ጎኑ ላይ ይነካዋል፤ ኢየሱስን ግን ለመንካት ሞክሮ አልቻለም። እሱን እነካዋላሁ ብሎ የእንግዴ ልጁን ሽፋን ነካው » ብሎ ነው የገለጸው።

ሳሃይ አል ቡካሪ ሃዲስ ፥ ሃዲስ 4፥641 ሰይድ ቢን አልሙሰያብ ነቢዩ መሐመድ ያለውን እንዲህ ብሎ ነው የተረከው፤-« የአላህ ሃዋሪያ እንዲህ ሲል ሰማሁት፥ ከአዳም ልጆች መካከል ሰይጣን ያልነካው ማንም የለም፤ ከማርያም ልጅ በቀር ገና ሲወለድ ጮሆ ያላለቀሰ ሕጻን የለምና። »

ስለዚህ መሐመድ ገና ሲወለድ ሰይጣን ነክቶት ዕድሜውን በሙሉ የኃጢዓት ሕይወት ሲመራ ፡ ለምን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ብቻ ያለኃጢዓት ሆነ? በቁርዐን ላይ በብዙ ቦታ መሐመድ ደጋግሞ ኃጢዓቱን እንደተናዘዘና ንስሐ እንደገባ ይገልጻል። ማንኛውም የእስልምና ዕምነት ተከታይ ሆኖ ቁርዐንን ያነበበ ሁሉ ይህንን በሚገባ ይገነዘባል።

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ወቅት እግዚአብሔር ብቻ ሊሰራቸው የሚችለውን ተዓምራቶች እንደሰራ ተዘርዝሮ ተገልጿል። ታዲያ እግዚአብሔር አምላክ ሙታንን ማስነሳትን፣ ከበሽታ መፈወስን ፣ የመሳሰሉትን ታላላቅ ታምራቶችን እርሱ ብቻ እንዲፈጽማቸው ለምን አደረገ?

ለምን መሐመድ እነዚያን አይነት ታምራቶችን አልፈጸመም? በዘመኑ ብዙ ሰዎች ተዓምራትን እንዲያደርግ ቢጠይቁት ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም። ግን በቁርዐን ላይ አንድ ተዓምር ብቻ አድርጓል ተብሎ ተገልጾለታል፤- ጨረቃን ለሁለት መክፈል። ይህ ተዓምር ድንቅ ነው ከተባለ፣ ለሰው ልጅ ይህ መሆኑ ምን ጥቅም ይሰጠዋል ?

ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ፣ መላዕክት ከድንግል ማርያም መወለዱንና ኃጢዓት የሌለበት መሆኑን ይህንን የተከበረ ልደት ለማብሰር ተላኩ። በእስልምና ተከታዮች ዘንድ እንደ ታላቅና የመጨረሻው ነቢይ የሚታየው መሐመድ ግን ይህን እድል አላገኘም። ለመሐመድ ለምን እንዲህ አልተባለለትም?

እግዚአብሔር አምላክ ድንግሊቱ እንድተወልድ ማድረግ ከቻለ የተወለደውን ልጄ ማለቱ ምኑ ነው ከባድ?

ቁርዐን ፡- መገለጥና ምህረት እንዳለም ይገልጻል፤ ራዕይና መገለጥ ከመሐመድም በኋላ ለሚመጣው ትውልድም ነው ፤ ግን ለምን? መገለጥና ራዕይ በዚያ መልክ እንዲሆን ለምን ተፈለገ? ምን ዓይነት ምህረት ነው ለዚህች ዓለም ያስፈለገው? ቁርዐን ለዚህ ሁሉ ምላሽ የለውም። ሙስሊሞች ለዚህች ዓለም የተላከውን ምህረትና መገለጥ ለማወቅ ኢንጂልን (ወንጌልን) ማንበብ አለባቸው ።

በኢንጂል (በወንጌል) በማርቆስ ወንጌል 10 ፥ 46-47 ውስጥ አንድ ማየት የተሳነው ሰው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ጮኸ፡-

« ወደ ኢያሪኮም መጡ ፤ ከደቀመዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ፣ የጠሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጠሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደሆነ በሰማ ጊዜ የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ ማረኝ ! እያለ ይጮህ ጀመር። »

እንደዚሁም በአዲስ ኪዳን ፡-

« ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምህረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። » የይሁዳ መልዕክት 1፥21

« ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሳቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ እድፈትም ለሌለበት ለማያልፍም ርስት እንደ ምህረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። » 1ኛ ጴጥሮስ 1፥3

የኢየሱስ ክርስቶስ ምህረትና ይቅርታ እርሱ ለኖረበት ዘመን ወይም እርሱ ለኖረበት አካባቢ ብቻ አልነበረም። እግዚአብሔር ለሁሉም የሰው ልጅ ከመሐመድ በፊትና በኋላም ላሉት ሁሉ የምህረት መንገድና ምንጭ አድርጎታል።

የእግዚአብሔር ቃል በሚገባ እንደሚነግረን እኛ ሁላችን ኃጢዓተኞች በመሆናችን በዚህም የተነሳ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር መለየታችንን በሚገባ እናውቃለን። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅና እንደገና ግንኙነታችንን ለመጀመር ብቸኛው እግዚአብሔር ያዘጋጀው መንገድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢዓት የሌለበት ሆኖ ሳለ ስለ እኛ ኃጢዓት ሆነ። ኃጢዓታችን በሙሉ በእርሱ ላይ ተጫነ።

ኃጢዓታችን በሙሉ በእርሱ ላይ ስለተጫነ። ኃጢዓት የሌለበት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢዓት ሆነ። በኢንጂል (በወንጌል) በማቴዎስ 1፥21-22 እንዲህ ተብሎ ተጽፏል። « እርሱ ሕዝቡን ከኃጢዓታቸው ያድናቸዋልና ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትለዋለህ፤ በነቢይ ከጌታ ዘንድ ፡- እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ፤ ልጅም ትወልዳለች። ስሙንም አማኑኤል ይሉታል። »

ለብዙ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ፡- «ኃጢዓትህ ተሰረየችልህ » እያለ በመናገር እርሱ የሰዎችን ኃጢዓት ይቅር ለማለት እንደመጣ አሳይቷል።

እንደዚሁም በአዲስ ኪዳን ውስጥ፡-

« እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢዓት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢዓት አደረገው። » 2ኛ ቆሮንቶስ. 5፥21

ብዙ ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚገኘውን ምህረትና ደህንነት በማግኘት ሕይወታቸው ተለውጧል። ከእነዚህም አንዱ እኔ ነኝ። ብዙዎች ተዓምርን፣ስልጣንን፤ ዕውነትን ትክክለኛ ባልሆነ ቦታ ለማግኘት ሲባዝኑ ይገኛሉ፤ እኔም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አግኝቴ እስከማርፍ ድረስ ሳደርግ የነበረው ነገር ልክ እንደነዚህ ሰዎች ነበር። ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ አንድ ብቻ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን እውነት አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ አለ፡-

« እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር፤ ከአሁን ጀምሮ ታውቁታላችሁ፡ አይታችሁትማል። » ዮሐንስ. 14፥6

መሐመድና ሙስሊም ተከታዮቹ በየቀኑ ብዙ ጊዜ በሚያስገርም ሁኔታ ስለደህንነታቸው ምሪት እንዲያገኙ ይጸልያሉ። በጣም የሚደንቀው ነገር ታላቁና የመጨረሻው ነቢይ ተብሎለት የሚነገርለት መሐመድ እንኳ ዕድሜ ልኩን እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ይህንን ምሪት በመጠየቅ እንደጸለየ ነው ያለፈው። - ሱራ አል ፈትህያ 3

ለመሆኑ መሐመድ በትክክለኛው መንገድ ላይ ነበርን? እስልምና በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ ነውን? ዛሬ ሙስሊሞች ወንዶችና ሴቶችን አንድ ነገር አሳስባቸዋለሁ፤ ለመሆኑ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት አሁን የያዙት ጎዳና በእርግጥ ትክክለኛ መንገድ ነው ብለው ያስባሉ? ብዙ ጊዜ በቁርዐን ላይ እንደምናገኘው መንግሥተ ሰማያት የእግዚአብሔር ህልውና የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ ተመልክተናል።

በሱራ አል ኑር 14 ላይ የተጻፈው እንዲህ ተብሎ ነው።

« የአላህ ምህረትና ጸጋን ካላገኘህ በዚህ ምድርና በወዲያኛው ኣለም ቅጣት ገሃነም ውስጥ ዕድል ፈንታህ ይሆናል። »

ሱራ ጣዉብ 111

« አላህ ለአማኞቹ ለመልካም ሥራቸው ለነርሱና ለነርሱ ለሆኑት ሰዎች የገነትን አትክልት ቦታ ገዛላቸው። »

ከዚህ ምን እንረዳለን?

« እናንተ የምታምኑ የሚጠበቅባችሁን ተግባር አከናውኑ፤ ወደ እርሱ ሊያቀርባችሁ የሚችለውን መፍትሄ ሁሉ እሹ፧ » ሱራ ዐአል ማይዳ 350

እኔ ሁልጊዜ መንፈሳዊ ርሃብንና ጥማትን እግዚአብሔር አምላክ በውስጣችን ያስቀምጥ ዘንድ ለደህንነት የሚያበቃንነን መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ እንዲረዳን እጸልያለሁ። ለሙስሊም ወንድሞቼና እህቶቼ ምን ማለት እንደሆነ ለማሳወቅና ትርጉሙም በትክክል ምን ማለት እንደሆነ ለማሳየት ብዙ የቁርዐን ጥቅሶችን በመጥቀስ ለማሳየትም ሞክሬአለሁ።

እኔ መንግሥተ ሰማይ በእኛ መልካም ሥራ የምንገዛት ቦታ ነች ብዬ አላምንም። መንገሥተ ሰማይን የምናገኘው በእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት ብቻ ነው። ስለዚህ ሁሌ ይህ እውነት እንዲገለጽልን የሚሻ ርሃብና ጥማት በውስጣችን አድሮ ለደህንነት የሚያበቃንን እውነት ተገንዝበን ለደህንነት እንድንበቃ ጸሎቴ ነው። ደህንነትን ለማግኘት የተወሳሰበና የከበደ ነገር የለም። በቀላሉ በትሁት ልብ ወደእርሱ ቅረቡ፤ የምህረት ፊቱንም እሹ፤ ማንነታችሁን በእርሱ የምህረትና የጸጋ ክንድ ላይ አሳርፉ።

በክርስቶስ አዲስ ክርስቲያኖች እንሆናለን። እውነቱ ከብዙ ጊዜ በፊት ነው የተጻፈው፣ ሆኖም ዛሬም አዲስ ነው። የፈጠረን እግዚአብሔር አምላካችን አስተሳሰባችንንና ሐሊናችንን እንዴት መለወጥ እንዳለበት ስለሚያውቅ በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ የመዳን መንገድን አዘጋጅቶልን በውስጣችን ያለውን ባዶ ቦታ እንዲሞላው ፈለገ። ስለዚህ ወንድሞችና እህቶች የእርሱን አስደናቂ ፍቅር ለመቀበል ልባችሁን በትህትና ክፈቱለት። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወችሁ እንዲገባ ፍቀዱለትና ቀጥሎ የሚሆነውን ተመልከቱ። በሕይወታችሁ ታላላቅ ነገሮች ሲከናወኑ የማየት ዕድልን ታገኛላችሁ። እኔ በችግርና በመከራ ውስጥ ስሆን ማንም ሊያደርግልኝ በማይችለው መንገድ ቀርቦኝ ሲጽናናኝና ሲያበረታታኝ አይቼዋለሁ። እርሱ ለዘላለም ሕያው እንደሆነና እስከዘላለም እንደሚወደኝ በሚገባ አስገንዝቦኛል። አንድያ ልጁን ልኮ ስለእኛ ኃጢዓት እንዲሞትና እኛም ደህንነትን እንድናገኝ ስላደረገ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁም። ከእርሱ ጋር ግንኙነት ለመጀመር ከፈለጋችሁ እንዴት መጀመር እንደምትችሉ ለማወቅ እግዚአብሔርን በግል ማወቅ የሚለውን ጽኁፍ ማየት ትችላላችሁ።

 ጥያቄ አለኝ
 ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነትን እንዴት እንደምትጀምር

ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More