×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
የህይወት ጥያቄዎች

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ቋት

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ፡ ሦስት ሰዎች በሕይወታቸውን ስኬት፥ ተቀባይነትና ዓላማ እንዴት እንዳገኙ ያካፈሉት ምሥክርነት ነው።

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

ከዚህም የሚበልጥ ነገር መኖር አለበት ብላችሁ ያሰባችሁበት ጊዜ የለም? እንደው በቀላሉ ከሕይወት ባሻገር (ከመኖር በላይ) አንድ ነገር መኖር እንዳለበት አስባችሁ አታውቁም ? የሚከተሉት መሰናዶዎች የሕይወትን ተጨባጭ ገጽታና በዚያም ውስጥ የእግዚአብሐሔር ሚና ምን እንደሆነ በሚገባ ያስገነዝቡናል።

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ቋት ፡ ስኬት (በ ጆን ጂ. )

ምናልባት ሰምታችሁ ይሆናል። አንድ ተራራን መውጣት የሕይወት ግቡ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ስለነበረው ሰው ማለቴ ነው። ይህ ሰው እንዳሰበው ተራራውን ወጥቶ ጫፍ ከደረሰ በኋላ ውስጡ እጅግ በቅሬታ ተሞላ። ከዚህ በኋላ የትም መሄድ አይችልም። ያሰበው ቦታ ደርሷል። ተራራ መውጣት ብቻ በራሱ ለሕይወት ግብ መሆን አይችልምና ውስጡ በቅሬታ ተሞላ። የጎደለ ነገር አሁንም አለ። የውስጡ ክፍተት አልተሞላም። ባዶነቱ እንዳለ ነው። ልክ እንደዚሁ ዝነኛው የእግር ኳስ ተጫዋች እንደሆነው ማለት ነው። የሕይወቱ ግብ በእግር ኳስ ሻምፒዮን ሆኖ ዋንጫውን ማንሳት ነበር። አልቀረም በቂ ትጋትና ጥረትን ስላደረገ፣ ሻምፒዮናነቱንም ተጎናጸፈ ፥ የናፈቀውንም ዋንጫ አቀፈ። ግን ከዚያስ ? ምን ይሁን? ባዶነቱ ግን እንዳለ ነው። ባዶውን የሕይወት ቋት እንዴት ብሎ የእግር ኳስ ዋንጫ ይሞላዋል?

የኔም የኮሌጅ ሕይወት በብዙው እንደዚሁ ዓይነት ነበር። በተለይ በመጨረሻው የመመረቂያዬ ዓመት ላይ ፣ ሰዎች ስኬት ማለት ይህ ነው ብለው የነገሩኝን ሁሉ አግኝቻለሁ። ከሌሎች ኮሌጆች ጋር አንድነትና ወንድማማችነትን መመስረት ፥ እንደዚሁም በተለይ ለወጣትነት ሕይወት የደስታ ምንጭ ናቸው ተብለው የሚታሰቡትን አንዳንድ ልምዶች ውስጥም ዘልቄ ገብቼ ሞክሬአለሁ። ግብዣን ከጓደኞቼ ጋር መደገስና መጨፈር፣ በትምህርቴ ጥሩ ውጤትን ማስመዝገብ፣ አይኔ አረፈባቸው ከምላቸው ቆነጃጅት ልጃገረዶች ጋር ጊዜን ማሳለፍ፥ እነዚህ ሁሉ የውስጤን ባዶ ቋት ለመሙላት የወሰድኳቸው እርምጃዎች ነበሩ።

በኮሌጅ በነበርኩበት ጊዜ የውስጤን ክፍተት ለመሙላት ያደረግኳቸው ነገሮች ሁሉ ከኮሌጅ ሕይወቴ ጋር አብረው አለፉ። አሁንም ግን የውስጤ ባዶነት ኦናነቱ ሰፍቶ ይታየኛል። እውነትም ከኮሌጅ ተመርቄ የሕይወቴ ግብ ነው ብዬ ያሰብኩት የተራራ ጫፍ ላይ ስደርስ ፥ በእርግጥ ያሰብኩበት ደርሻለሁ፤ ከዚያስ ምን ይሁን? ወዴትስ ልሂድ ?የሚለው የውስጥ ጥያቄዬን ግን ከቶም መመለስ ስላልቻልኩ ሕይወቴ በቅሬታ የተሞላ ሆነ። ጩኸቱ ሁሉ ታዲያ ወዴት ልድረስ! የሚል ሆነ። አንድ ነገር እንደጎደለኝ ታውቆኛል። ግብ ብዬ ለሕይወቴ የለየኋቸው ነገሮች ከጥቅማቸው ባሻገር የሕይወትን ባዶ ቋት እንደማይሞሉ የገባኝ ከዚያ በኋላ ነው።

እርግጥ ነው ነፍሴ በዚህ ዓይነት ውስጥ እንዳለችና እንደምትባዝን ማንም አያውቅብኝም። ከላይ ከላይ ለሚመለከተኝ ሁሉ ፍጹም ደስተኛና የሞላለት፣ እንዲሁም የተሳካለት መስዬ ለመታየት አልተቸገርኩም። አስገራሚና ትልቁ ያየሁት የሕይወት ምጸት ፣ ብዙዎች ከኔ ጋር ሕብረት ያላቸው እኔን መሰል ወጣቶች፥ ከላይ ከላይ በሚያዩት ሕይወቴ ብቻ ተማርከው እኔን መምሰል በመፈለግ ስህተት ውስጥ ሲገቡ ማየቴ ነው። የውስጥ ማንነቴን ገና አልተረዱትም። የውስጤን ባዶነት የሚያሳየውን ገበናዬን እንዴት ይወቁት? ምን እየተሰማኝ እንዳለ ቢያውቁት ኖሮ ምን እንደሚፈጠር አሁን መገመት ይቸግረኛል።

በዚህ በኮሌጅ ተማሪዎች ሕብረት ውስጥ አንድ በጣም የምናሾፍብቸውና የምንቀልድባቸው ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቡድን ነበር፤ «መጽሐፍ ቅዱስ አጣቢዎች» እላቸዋለሁ ። ምንም እንኳ በነዚህ ወጣቶች ላይ የማሾፍና የማፌዝ ብሆንም ፥ ከዛም ባለፈ የምኮንናቸውና የምወቅሳቸው ብሆንም ፥ ልክ እንደኔ ሕይወታቸው ውስጥ ያልሞላ ባዶ ቋት አላቸው ብዬ ለመቀበል ግን እቸገር ነበር። ምክንያቱም እነዚህ ልጆች እኔ ያጣሁት፣ ግን ሕይወቴ አጥብቃ የምትፈልገው ርካታን እንዳገኙ እርግጠኛ ልሆን ችያለሁ። የሕይወት ትርጉም በሚገባ የገባቸው ይመስላል።

ትምህርቴን እንደጨረስኩ ባለው ቀጣዩ የበጋ ወራት በአንድ ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ውስጥ እንድካፈል ተጋበዝኩ። ብቻ በተለያየ ምክንያት ለመቅረት የሚያስገድደኝ ነገር ስላልነበር እንደው ጊዜ ለማሳለፍ ሄድኩ። ሆኖም አንድ የማልክደው ነገር፥ ከሌላው ጊዜ ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገር ይበልጥ ክፍት እንደሆንኩ ይታወቀኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምረው ሰው ማስተማር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ውስጤ እጅግ በአድናቆት እየተሞላ ነበር። «ስሙ ሕይወታችሁን በሚያልፈውና ቁሳዊ በሆነው ነገር ለመሙላት የምትፈልጉ. . . » እያለ ሲናገር የበለጠ ከመደነቅም ወደ መደንገጥም መግባት ጀመርኩ። የምሳለቅበትን መጽሐፍ ቅዱስ ከልቤ ማድነቅ ጀመርኩ። ያለሁበትን የጊዜውን የሕይወቴን ባዶነት ሲነካካው ይታወቀኝ ነበር።

ሆኖም እግዚአብሔር አምላክ በሚያስደንቅ ሁኔታ እየተናገረኝ የልቤን በር በጨዋነት ሲያንኳኳ እየታወቀኝ፥ በጊዜው ግን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኜ አልተገኘሁም። ይልቅስ ብሶብኝ ማሰብ የጀመርኩት፣ እኔ ስለወጥ ጓደኞቼ በኔ መለወጥና እንግዳ ሕይወት ሲሳለቁብኝ እያታየኝ ይህንን ሁኔታ በማውጣትና በማወረድ ብዙ ጊዜ ፈጀሁ። ፍርሃትም አደረብኝ። ጭንቀትም ውስጥ ገባሁ። በጉዳዩ ላይ አጠንክሬ ባሰብኩበት መጠን በዕውነት እግዚአብሔር አምላክም ረዳኝ። ከእርሱ ጋር ግንኙነትን ለመፍጠር መወሰን ተክክለኛ ውሳኔና እርምጃ መሆኑን አበክሮ ለውስጤ ተናገረኝ። ከዚያ በትግሌ መቀጠል አልቻልኩም። በእርግጥ ለሕይወቴ እንደሚያስፈልገኝ በማመን ራሴን በትህትና ዝቅ አድርጌ ለእርሱ አስገዝቼ በእውነት እግዚአብሔር አምላክ ወደ ሕይወቴ እንዲገባና ባዶ የነበረውን ቋት እንዲሞላልኝ ጋበዝኩት።

ከዚያ በኋላ የሆነውን ለመግለጽ በጣም እቸገራለሁ። በቀላሉ በአጭር ቃል እንዲህ ብዬ ብቻ ብገልጸው እወዳለሁ፤ እግዚአብሔር አምላኬን «ተገናኘሁ» ። ልክ አምላኬን እግዚአብሔርን እንዳገኘሁት የሕይወቴ ባዶ ክፍተት በድንቅ እንደሞላና እኔም በእውነተኛ እርካታ ውስጥ እንደምገኝ ተረዳሁ። ከዚያ በፊት ያልተለማመድኩት የውስጥ ሙላት ሕይወቴን ሲገዛ ተሰማኝ። የሕይወቴ ባዶ የነበረው ቋት በእርሱ ቸርነት ተሞላ። ከዛን ጊዜ አንስቶ ሙሉነት የሕይወቴ አካል ሆነ። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን።

ከዚያ በኋላ የተረዳሁት ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር ይህ ያለፍኩበት ጎዳና የኔ ብቻ ልምምድ እንዳልሆነ ነው። ጌታ ኢየሱስ ማንኛውም ሰው እንዲያልፍበት የሰጠው ስጦታ ነው። እንዲህ አለ፡- (አሁንም ይላል) « የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደእኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ ሚያምንም ሁልጊዜ አይጠማም። »ዮሐ. 6፥32-35 ጌታ ኢየሱስ ከርሱ ጋር እንድንገናኝ ይጋብዘናል።

ሕይወት የራሷ ውጣ ውረድ አላት። በትገልም የተሞላችም ናት። ግን የሕይወትን ትርጉም ማወቅና የሚያረካትን መምረጥ ብቻ ሰላምና ደስታን ይሰጣል። ይህንንም ያወቅሁት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቄ ነው።

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ባዶ ቋት ፡ ተቀባይነትን ማግኘት (በ ሮበርት ሲ. )

በልጅነቴ ዘ ዊዛርድ ኦፍ ኦዝ የሚል የቴሌቭዥን ፊልም እያየሁ ነው ያደግኩት። በልጅነቴ የምወደው ፊልም ነበር። የማታውቁት ከሆነ ታሪኩን ቀንጭቤ ላውጋችሁ። ዶሮቲ የተባለችው ገጸባህርይ የምትኖርበትን የካንሳስን ከተማ ትለቅና በቀላሉ አንድ ተንኮለኛ የሆነ ጠንቋይን የገደለችበትና ዝነኛ የሆነችበት ምድር ኦዝ የተባለ ቦታ ታርፋለች። በዚህ የተነሳ ከዖዝ ከተማ የጎረፈላት ክብርና ዝና የውስጧን ፍላጎት ሊያረካ አልቻለም ነበር። ከዛ ይልቅ የውስጥ ፍላጎቷ አስደናቂውን የዖዝ ከተማ ጠንቋይ ማየት ነበር። ስለዚህ ከሦስት ጓደኞቿ ጋር ሆና ያንን አስገራሚና አስደናቂ ፍጡር ለማየት እርሱን ፍለጋ ጉዞ ትጀምራለች።

ከዛ በኋላ ዶሮቲና ጓደኞቿ ምን አጋጠማቸው መሰላችሁ ፣ ከመልካምና እንግዳ ተቀባይ ጠንቋይ ይልቅ፥ ቁጡ፥ አስፈሪና አስጨናቂ ጠንቋይ ሆኖ አገኙት። ራሳቸውን በሚገባ ለርሱ አገልጋይነት ብቁ ለማድረግና አስማተኛዋን መጥረጊያ ለመሸለም በጣም ከባድ የሆኑ ሥራዎችን በማሰራት ያሰቃያቸው ነበር። እናም. . . .

ከብዙ ሥቃይና መረበሽ በኋላ ዶሮቲና ጓደኞቿ በዖዝ ጠንቋይ ፊት እንደገና መቆም ቻሉ። በዚህ ጊዜ አስማታዊዋ መጥረጊያ ተሰጥቷቸዋል ። የቀረው ጠንቋዩን ማየት ብቻ ነው። የዶሮቲ ውሻ ቶቶ ሮጣ ከፊት ለፊታቸው የነበረውን መጋረጃ ስትከፍተው በፊታቸው ተኮፍሶ ያገኙት አንድ በትንሹም በትልቁም የሚነጫነጭና የሚጮህ ሽማግሌ ጠንቋይ ሰው ብቻ ነው። ምንም አዲስ ነገር አልነበረም።

በዛ አስተሳሰብ አድጌ ገና ከልጅነቴ ጀምሮ እግዚአብሔር ለእኔ ልክ እንደ ዖዝ ጠንቆይ ሆኖ ብቻ ነበር የሚታየኝ። ዝም ብሎ ነገር ነበር የሚመስለኝ። ተናዳጅ፥ ቁጠኛና ጯሂ አድርጌ ነበር እግዚአብሔርን የማስበው። ስለ እኔ የሚያውቀውም ነገር እጅግ በጣም የተወሰነና ትንሽ እንደሆነ አድርጌ ነበር የማስበው። በሕጻንነቴ ቤተ ክርስቲያን ከቤተሰቦቼ ጋር ስሄድ ያየኋቸው ምስሎች እርሱን በሩቅ ያለ ደሞም የማይደረስበት አድርገው ነው በዛ የልጅነት አዕምሮዬ የቀረፁብኝ ።እርሱ የሚያየው በመልካም አኗኗር የሚኖሩትን ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ በእርሱ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት በመጀመርያ ለእግዚአብሔር ጠቃሚ እነደሆንኩ ማረጋገጥ ያለብኝ ይመስለኝ ነበር፡፡ ባጭሩ እግኢአብሔር ለኔ ድንቅ ብዬ የምጠራው አልነበረም፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደገባሁ በመጀመሪያው ዓመት ላይ ይህ ሁሉ አስተሳሰቤ ተለወጠ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋርዶብኝ የነበረው መጋረጃ ተገለጠ። ሁልጊዜ እግዚአብሔርን እንደማይጨበጥ ጉም አድርጌ እንዳላሰብኩ፡ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን አሳየኝ። እርሱ እግዚአብሄር ቁጡ ረእንዳልነበር አስረዳኝ። በአጠቃላይ ስለአግዚአብሔር የነበረኝ ግምትና ሃስብ ፈ.ፅሞ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይገናኝና የተቃረነ ነበር። እርሱ የፍቅርና የርህራሄ አምላክ እንደሆነ አወቅሁ። ፍፁም ህይወት መኖር እንደማልችል ያውቃል ለካ፡፡ ለዚህም ነው እሱ ፍፁም የሆነው ጌታዬና አምላኬ ስለኔ በፍፁምነት ኖረልኝ።

እኔ እንደገባኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የኔ አምሳያ ሳይሆን በቀጥታ የኔ ምትክ ነው። የርሱን ሰቆቃና ሥቃይ እንድመስል አይጠበቅብኝም ፤ ግን በሱ ስቃይ የደህንነት ዕድልን በማግኘት መጠቀም እንደሚኖርብኝ ተገንዝቤአለሁ። እንደተገነዘብኩት እርሱ በሙሉ ፈቃደኝነት ባለፈበት የመስቀል ሞት እኔ መቀበል የሚገባኝን ፍርድ ስለኔ እርሱ ተቀበለልኝ። እግዚአብሔር ለእኔ ያለውን ፍቅር ሊገልጽልኝ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ተጓዘ። በዚያ በመስቀሉ ሥር ነው እርሱ እኔን በሚገባ የሚያውቀኝ መሆኑን የተረዳሁት። በመሥቀሉ ሥር ነው የተቀበለኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል፡- « እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢዓት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢዓት አደረገው። » 2ኛ ቆሮ 5፥21

ትክክለኛ ተቀባይነትን ከመጋረጃ በስተጀርባ ተቀምጦ አገኘሁት። እኔም ዛሬ ራሳችሁ መጋረጃውን ገልጣችሁ እግዚአብሔርን እንድታገኙትና ያዘጋጀላችሁን ይቅርታና ተቀባይነትን በትህትና እንድትቀበሉ አደፋፍራችኋለሁ።

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ባዶ ቋት ፡ ዓላማ (በ ማርሊን አ )

ሁልጊዜ ሕይወት ትርጉም ሊኖራት ይገባል ብዬ ነበር የማስበው። በየዕለቱ በምንሰራችቸው በሁሉም ነገር ላይ ማለቴ ላይሆን ይችላል። ልብስን ማጠብ የመሳሰሉትን የግድ ትርጉም እንስጣቸው ማለቴ አልነበረም ወይም ሁልጊዜ ኮምጨጭ ያለ ህይወት እንኑር ማለቴ አልነበረም ። ብቻ ምን አለፋችሁ ሁላችንም ብንሆን ብዙ መልካምና ደስ የሚል ጊዜን ማሳለፍ እንፈልጋለን።

ሕይወት ግን ደስታን ከመፈለግ ያለፈ ነገር ውስጧ አለ። ምክንያቱም ደስታ የምንለዉ ነገር ብዙም ዘላቂ አይደለም፡፡ ዛሬ እዚህ ነው ስንለው ነገ ደግሞ ወደሌላ ቦታ ይሄዳል። ራቪ ዘካርያስ የተባለ ጸሐፊ ይህንን አባባሌን በጥሩ ሁኔታ ሲገልጸው እንዲህ አለ።- « ሕይወት በሰፊው ትርጉም ካጣች፥ ያች ሕይወት የሚቀሰቅሳት ፥ ትርጉም አለው ብላ የምትከተለው ቁምነገርና ለማንነቷ ዝርዝር መግለጫ ያጣች ናት ማለት ነው። » አለ።

ለብዙ ዓመታት የዶስቶቭስኪን፥ የሳርተርን፥ የኒቼን፥ የሶቅራጥስንንና የሌሎችንም የብዙ ፈላስፎችን ሥራዎች ለሕይወቴ ትርጉምና ዓላማ ያገኙልኛል በሚል ጥማት ላጠናቸው ሞክሬአለሁ። በየጥቂት ሳምንታት አዳዲስ የፍልስፍና ሃሳቦችን በሕይወቴ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ሕይወቴ ተለውጦ እንደሆነ በመከታተል ሙከራ አደርግ ነበር። እነዚህ በየጊዜው በሕይወቴ የምሞክራቸው የፍልስፍና ሃሳቦች በቀጥታ ከተጨባጩ ዓለም ጋር ሲገናኙ ሃሳብ ብቻ እንጂ ከቶም ትርጉም የሌላቸው መሆናቸውን ስመለከት በጣም እበሳጭ ነበር። ሆኖም ሙከራዬን አላቋርጥም ነበር።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆነው የታይም መጽሔት ላይ ጸሐፊ የነበረው ዶክተር ዴቪድ አይክማን ፥ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ እንደ ጨረር የፈነጠቀው ነገር ነበር። ይህ ሰው ሁለት የድህረ ምረቃ ድግሪዎች አሉት፤ በቻይናና በሩሲያ ታሪክና በኮሙኒዝም ጉዳይ ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረገ አንቱ የተባለ ባለሙያ ነው፤ ከሰላሣ በሚበልጡ አገሮች በመዘዋወር ሠርቷል። ስድስት አለም አቀፍ ቋንቋዎችን አንደ አፍ መፍቻው አቀላጥፎ ይናገራል። ሕይወትን በተመለከተ ያለው አስተሳሰብ ያለ ነበር። በልዩ ትርጉም ነው ሕይወትን የሚመለከተው። ይህ ሰው ሕይወትን አስመልክቶ እንዲህ አለ፡- « እያንዳንዳችን ዓላማ አለን፤ እዚህም ለመገኘታችን ምክንያት አለን። ያንን ማንም ሊነግራችሁ አይችልም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ብቻ ታገኙታላችሁ።» አለ። በዶር አይክማን በንግግሩ ከጌታ ከኢየሱስ ጋር መጀመር ነው መፍትሄው አለ።

ዶር አይክማን በተጨማሪም እንዲህ አለ።« የጌታ የኢየሱስን ቃላት ስሰማ (ከመጽሐፍ ቅዱስ ማለቱ ነው።) በቀጥታ ለልቤ የሚነገረኝ ይመስለኛል። እንዲህ ይለኛል፤ እኔ የሕይወት መንገድ ነኝ፤ ብትከተለኝና የምልህን ብቻ ብታደርግ ሕይወትህ ይለወጣል። የሚለኝ ይመስለኛል።» አለ። ይህ ሰው በመቀጠልም ከክርስቶስ ጋር ግንኙነትን ለመፍጠር ክርስቶስን ወደ ሕይወት በመጋበዝ የመጀመሪያውን እርምጃ ስለመውሰድ ተናገረ። በመጨረሻም ዶር አይክማን፡- ማንኛችሁም ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰውን የመጀመሪያውን እርምጃ ብትወስዱ አስደናቂና ትርጉም ያለው ሕይወት እንደሚኖራችሁ በድፍረት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።» ሲል ደመደመ።

ልክ እንደ ዶ/ር አይክማን እኔም የመጣሁት እግዚአብሔርን ሲክድ ከነበረ ሕይወት ነው። ልክ እንደርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለራሱ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተናገራቸው ንግግሮች ሁሉ ለኔ ልዩ ትርጉም የሚሰጡኝ ነበሩ። ጌታ ኢየሱስ ሕይወትን አስመልክቶ በተናገራቸው ንግግሮች እንደማንኛውም ሰብዐዊ ፈላስፋ ከቶም ወደ ሌሎች ሰዎችን መፍትሄ አድርጎ አልጠቆመም። እርሱ ግን መፍትሔ አድርጎ የሚያቀርበው እርሱን ራሱን ነው። ጌታ ኢየሱስ ኃጢዓታችንን ይቅር እንደሚል፥ በጭንቀትና በሁከት መሐል እርሱ ሰላም እንደሚሆን፥ ወደ ነጻነት ሕይወት እንደማመራን ተናግሯል።

እኔም በእርግጥ የእግዚአብሔር መኖር ዕውነት ከሆነ እርሱን ማወቅ አለብኝ፤ ብዬ ወሰንኩ። ሆኖም አሁንም ሕይወቴ ከጥርጥር በሽታ ነጻ አልነበረም። ክርስቲያኖችን ባገኘኋቸው ቁጥር እከራከራቸው እንደነበር አውቃለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ አምላክ እንደሆነ ማረጋገጫ እንዲሰጡኝ እፈልግ ነበር። አንድ ቀን ግን ከልቤ ሆኜ በትህትናና በቅንነት ስመለከት የእግዚአብሔርን ሕልውናና የክርስቶስ ኢየሱስ መለኮትነት በሚገባ ተገለጠልኝ። በድንገት በርካታ ተጠየቅ የሞላባቸው ምክንያቶችና ታሪካዊ ጭብጦች ሲገለጡልኝ እጅግ በጣም ደነገጥኩ። አሁን ውሳኔን መወሰን ነበረብኝ። እግዚአብሔርን ወደ ሕይወቴ ገብቶ በኔ ላይ እሱ በሚፈልገው መንገድ ተጽዕኖ እንዲያደርግብኝና እርሱ የሚፈልገውን ዓይነት ሰው እንደሆን መፍቀድና ያለፈውን የሕይወቴን ምዕራፍ መዝጋት ወይስ እንዳለ መቀጠል? መወሰን ነበረብኝ።

ጌታ ኢየሱስን ለማመን የሚያስችሉኝን ተጨባጭ የሆኑትን አዕምሮአዊ ምክንያቶችን ከላልሼ ተመለከትኩና ወደ ሕይወቴ ይገባ ዘንድ በትህትና ጠየቅኩት። ከዚያ ቅጽበት ጀምሮ ለሕይወቴ ትርጉም ፍለጋ መባዘኔን በታላቅ መፍትሄና ግኝት ደመደምኩ።

ከእግዚአብሔር አምላክ ጋር ግንኙነት መፍጠር መቻሌን ሳስብ በጣም እደነቃለሁ። አነጋግረዋለሁ፤ በለውጦችና በሁኔታዎች መካከልም እርሱ ንግግሬን እንደሚሰማኝ ምልክቶችን ያሳየኝ ነበር። ላልመውና ላስበው ከምችለው በላይ በሙያዬም እንድበለጽግ የሚያስችለኝን ጎዳና እርሱ በችሮታው መራኝ። ጥያቄዎችን በየጊዜው እጠይቀዋለሁ ፣ እርሱም ተገቢውንና ትክክለኛውን ምላሽ ከቃሉ ይሰጠኛል።

እነዚህ ነገሮች በአንድ ግልጽ ባልሆነና ማዕበላማ በሆነ ጀምበር ውስጥ የተከናወኑ አይደሉም። ከእግዚአብሔር ጋር በሁለት ወገን በተደረገ ግንኙነት የተፈጸመ ኹነት ነው። ይህ አካሄድ እኔ በጣም የረካሁበትና እጅግ የምደሰትበት ሁኔታ ነበር። ይህ ሁሉ የሆነው እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ አይደለም ። ጌታ ኢየሱስን ወደ ሕይወቱ በመጋበዝ ያስገባና በዕውነት እርሱን የማወቅ መሻት ላለውና ለሚከተለው ሁሉ የሚሆን ነው።

እግዚአብሔርን በመከተል ታላቅና ጥልቅ ደስታ አለ። ከሌሎች ነገሮች በተለየ ሁኔታ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅና መከተል ወደ ትክክለኛው የሕይወት ዓላማ ያመጣል።

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ባዶ ቋት: ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ

ትክክለኛ ሕይወት ማለት፣ በእርካታ፣ ተቀባይነትን በማግኘትና በዓላማ የተሞላ ሕይወት ነው። ይህንንም የምናገኘው ከጌታ ኢየሱስ ጋር ግንኙነትን በመፍጠር ነው። በታሪክ ማንም ሥጋ የለበሰ ሰው ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እንዳለው የኖረና ይህንንም በሕይወቱ ያረጋገጠ ማንም የለም። እርሱ ኃጢዓትን ይቅር የሚል አምላክ እንደሆነ ተናገረ፤ እግዚአብሔር አብን ለማወቅ ብቸኛው መንገድ እርሱ እንደሆነ ተናገረ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን የተናገራቸውን ሁሉ ዕውነት መሆናቸውን ከሞት በድል በመነሳት ለዓለም ሁሉ አረጋገጠ። በእርግጥም እርሱ በዚህች ምድር ላይ ከተመላለሱት ሰዎች ሁሉ እጅግ የተለየ ነበር። ከመምህርም በላይ . . . ።

መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ ሰው የሆነ አምላክ እንደሆነ አስረግጦ ይነግረናል። « ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና ዕውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን። »ዮሐ.1፥14 ጌታ ኢየሲስ ራሱ የእግዚአብሔር ፡-« የክብሩ መንጸባረቅና የባህርዩ ምሣሌ. . . » ነው። ዕብራ.1፥3 በአጭሩ ጌታ ኢየሱስ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል በትክክል የገለጸልን አምላክ ነው። ስለዚህ ከርሱ ጋር እንዴት ግንኙነትን እንመስርት?

ወገኖች! ከጌታ ጋር ግንኙነት መመስረት የምንችለው መልካምና የተሻሉ ሰዎች ለመሆን በመሞከር አይደለም ። እንደምንም በራሳችን ተፍጨርጭረን ኖረን የአግዚአብሔርን ማረጋገጫ በማግኘትም ከርሱ ጋር ግንኙነትን መመስረት አንችልም። ከአንድ ሰው ጋር ግንኙነት ለመመስረት እሱ የሚፈልገውን ዓይነት ሰው ለመሆን ጥራችሁ የሰውየውን ማረጋገጫ ለማግኘት ሞክራችሁ ታውቃላችሁ?

እግዚአብሔር አምላክ ግን እኛን ወደ እርሱ ለማቅረብ መንገዱን ለማሳየት ዕውነተኛና ፍጹም ፍቅሩን ሰጥቶናል። ሆኖም አንደ ችግር አለ፤ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የሰመረ ግንኙነት እንዳይኖር የከለከለ ነገር አለ። ኃጢዓታችን ነው። ( እኔነታችን ፥ በቁጣና በክፉ ቃላቶቻችን ይገለጻል። ትዕግሥት ማጣታችን፥ እጅግ ራስ ወዳድነታችን፥ ንፉግነታችንና የመሳሰሉት ) ምናልባት ጸሎታችሁ የማይሰማበት ምክንያቱ ግራ ገብቷችሁ ከሆነ ምክንያቱ ይኸው ነው። ኃጢዓታችን ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር አምላካችን ለይቶናል።

ስለዚህ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን ምን አደረገ? ሰው የሆነው አምላክ ጌታ ኢየሱስ የሰውን ልጅ ኃጢዓት በሙሉ በትከሻው ተሸክሞ በሙሉ ፈቃደኝነት አኛን ተክቶ በመስቀል ላይ ሞተ። እርሱ ይህን ደረገው እኛ ፍጹም ይቅርታን እንድናገኝና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንድንጎናጸፍ ነው።

ቸግራችንን ይበልጥ ግልጽ እንዲያደርግልን አንድ ምሣሌ እናቅርብ፤ አንድ የኮሌጅ ተማሪ ጥፋት አጠፋችና ዳኛ ፊት ቀረበች። ዳኛው ተማሪዋን ሰላሣ ቀን እስራት ወይንም የአንድ ሺህ ብር ቅጣት ወሰኑባት። ተማሪዋ መታሰርም ሆነ የገንዘብ ቅጣቱንም መክፈል አትችልም። ዳኛው ይህንን በሚገባ ያውቁ ስለነበር፤ ካባቸውን አወለቁና ቅጣቱ ወደሚከፈልበት ቦታ ሄዱና ቅጣቱን ለመክፈል የገንዘብ ቼክ ላይ ፈርመው ቅጣቱን ከፈሉላት። ግን ለምን? እንደዳኛነታቸው ጥፋት ስለተፈጸመ ሕጉ የደነገገውን ቅጣት መወሰን ነበረባቸው ፤ ፍትህ ነውና ። ሆኖም ተማሪዋ የእርሳቸው ልጅ ስለነበረች እንድትታሰር ስላልፈለጉ፣ በቀጥታ የተወሰነውን የቅጣት ገንዘብ ስለርሷ ሆነው ከፈሉ።

ይህ እንግዲህ ልክ ጌታ ኢየሱስ ለእያንዳንዳችን ዕዳችንን ለመክፈል በመስቀል ሞት የከፈለውን ቅጣት ማለት ነው። በታላቅ ሰቆቃና ሥቃይ ነው ያለፈው። ተደበደበ፥ ተወገረ፥ ተገረፈ፥ ስለእኛ ተሰቀለ። አሁን እኛን ስለከፈለው መስዋዕት ምላሽ እየጠየቀን ይገኛል። ምላሻችን ምንድነው? ምላሻችን እርሱን ወደ ሕይወታችን በዕምነት መጋበዝ ሊሆን ይገባል።

ሊሞላ ያልቻለው የሕይወት ባዶ ቋት: እግዚአብሑርን ማወቅ

እግዚአብሔር እርሱን እናቀውቀው ዘንድ ይፈልጋል። ፍቅሩን፥ ደስታውንና ሰላሙን እንድንለማመድ ይሻል። ወደ ሕይወታችን ስንጋብዘው ይቅርታውን እንቀበላለን። ግንኙነትን ከእርሱ ጋር እንጀምራለን። እስከ ለዘላለም በሚዘልቅ ግንኙነት እንተሳሰራለን። ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፡- «እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ፥ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፈትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። » ራዕይ.3፥20

ይህ ሁሉ እንግዲህ የልብ/የልብሽ መሻት ከሆነ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ጸሎት እንድትጸልይ/ዪ እመክርሃለሁ/ እመክርሻለሁ። (ቃላቶቹ ብቻ ሳይሆን ልብህን/ሽን ለርሱ እንድታቀርብ/ቢ አጥብቄ እመክርሃለሁ። /እመክርሻለሁ።)

« የተወደድክና የተከበርክ አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፣ ኃጢዓት በመስራት አንተን በድያለሁ። በመስቀል ላይ በመሞት ኃጢዓቴን ሁሉ ስለወሰድክልኝ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። ምህረትህን መቀበል እፈልጋለሁ። ካንተ ጋር የጠበቀና የሰመረ ግንኙነት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። የሕይወቴ ጌታና አዳኝ ሆነህ ወደ ሕይወቴ ትገባ ዘንድ እጠይቅሃለሁ። ካንተ ብቻ የሚገኝ ትክክለኛውን ሕይወት ስጠኝ። በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ሥም ፤ አሜን! »

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More