×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
ወሲብ እና የፍቅር ግንኙነት

የፖርኖግራፊ ዘጠኙ ዉሸቶች

ከፖርኖግራፊ ሱስ ነጻ ውጡ፤ ዘጠኝ የፖርኖግራፊ ቅጥፈቶችን በማወቅ እንዴት ነጻ መውጣት እንደምትችሉ

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በጄኒ ማኮኔል

ፖርኖግራፊ እንደአጉል ሱስ. . . . . . ወሲብ ከተገቢው ዐውድ ውጭ ሲሆን

ቅዝቃዜ በተሞላ ምሽት በእሳት ማንደጃ ቺሚኒ (ለእሳት መሞቂያ ተብሎ ለዚሁ ዓላማ የሚሰናዳ ነገር ነው።) ውስጥ እጅግ ፈካ ያለ ፍምን እንደማግኘት የሚያስመኝ ምንም ነገር የለም። አሥር ጊዜ እየቆሰቆሳችሁና ማገዶ እየጨመራችሁ ከእሳቱ የሚወጣውን ሙቀት በማጣጣም መደሰትና መዝናናት ምን ዓይነት ውብ ነገር ነው ያሰኛል።- ክፉ ነገር የለውም ሰላም ነው። ልክ እንደዚሁ እስቲ አንድ ነገር አስቡ ፥ ከእሳት መሞቂያው ቼሚኒ ውስጥ አንድ የእሳት ፍም ወስዳችሁ በእንግዳ ማረፊያ ሳሎን ውስጥ ጣሉት። ይህ ሰላም ነው ብላችሁ ሲያዝናናችሁ የነበረው እሳት ወዲያውኑ መልሶ አውዳሚና አጥፊ ሲሆን ታገኙታላችሁ። ቤቱን በሙሉ ያቃጥላል፤ በቤት ውስጥ የነበረውን ሕይወት ሁሉ ያጠፋል፤ የነበረውን እንዳልነበረ ያደርጋል፤ ወሲብም ልክ እንደ እሳቱ ነው። ወሲብ በጋብቻ ቃልኪዳን ውስጥ ሲፈጸም ልክ በተገቢው ማንደጃ ላይ እንዳለው እሳት አስደናቂ፥ ውብና ሰላም የተሞላበት ነው። ግን ልቅ ፍትወት ከጋብቻ ዐውድ ውጭ ሲፈጸም ደግሞ ሰላምና ውብ ሳይሆን አስነዋሪና አስከፊ ይሆናል።

ዛሬ ልቅ የፍትወት ፊልም(ፖርኖግራፊ) ትልቅ የገንዘብ ምንጭ ሆኗል፤ በሰው ሕይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር ያምጣ ቅንጣት ግድ ሳይኖራቸው ገንዘብ ለማጋበስ ሲሉ ብቻ የሚያመርቱት ምርት ሆኗል። እንደገና ተመላልሳችሁ ከነርሱ መግዛት እንድትችሉና እስከመጨረሻ እንደባሪያ ሊገዟችሁ ስለሚፈልጉ እናንተ ማየት የምትፈልጉትን ሁሉ ከማዘጋጀትና ከማምረት አይሰንፉም ተግተው ይሰራሉ። ከአሥር ዓመት በፊት ኒውዮርክ ታይምስ በሜይ 20, 2001 ዓ.ም በወጣው ዕትሙ ላይ «ባለእርቃኖቹ ካፒታሊስቶች » በሚል ርዕስ ባወጣው መረጃ ፥ በአሜሪካ ውስጥ በተደረገው አሰሳ በአንድ አመት ብቻ ከአስራ አንድ ሺህ በላይ በሚሆኑ የልቅ ፍትወት ርዕሶች ፊልሞች ተዘጋጅተው መሰራጨታቸውን ይፋ አውጥቷል። እንደዚሁም በዚሁ ዓመት በታወቀው የሆሊውድ ፊልም ዝግጅት ውስጥ ከአራት መቶ በላይ በሚሆኑ ርዕሶች የልቅ ፍትወት ፊልሞች ተዘጋጅተው መሰራጨታቸውን የተደረገውን ጥናት ዋቢ አድርጎ ዘገባው አስቀምጦታል ። በተመሳሳይ ዓመት ሰባ ሺህ የሚሆኑ የልቅ ወሲብ ድረገጾች ተዘጋጅተው የዓለምን አየር በሙላት እየናኙበት መሆኑን ማወቅ ምንኛ አስደንጋጭ ነው! ይህ መረጃ ከአሥር ዓመት በፊት የነበረውን መረጃ የሚያሳይ ቢሆንም፥ ዓለም በዚህ አንጻር እንዴት ወደ ጥፋት እየገሠገሰች እንደሆነ ለማመላከት በቂ ፍንጭ እንደሆነ ግልጽ ነው። እንዲሁም መረጃው ከአሥር አመት በፊት የነበረውን አሃዝ ሲያሳይ ዛሬ ደግሞ ከአሥር ዓመት በኋላ ምን ያህል በሚያስደነግጥ ሁኔታ እንደሚጨምር ለመገንዘብ ብዙ ዕውቀት አይጠይቅም።

ፖርኖግራፊ ሃይል ምን እንደሚሰጠው፡

ለሕሊና ደህንነት አስፈላጊና ዋና የሚባለው ክፍል፥ ጤናማ በሆነ የወሲብ ሃሳብ ውስጥ መገኘት ነው። እነዚሀ ጤናማ ሃሳቦች መበከል ሲጀምሩ የማንነታችን መገለጫዎች የሆኑ አቋሞቻችን መጣመም ይጀምራሉ። የልቅ ፍትወት ዓለም ባሕልና ፍልስፍና ፍትወት ፥ ፍቅርና መቀራረብ አንድ ናቸው ብሎ ይነግራችኋል። በልቅ ፍትወት ዓለም ሰዎች ከማያውቁት ሰው ጋርና እንደው በአጋጣሚም ካገኙት ጋር ልቅ ወሲብ ይፋጽማሉ። ዋናው ቁምነገር ሆኖ የሚወሰደው በጊዜው የሚገኘው ቅጽበታዊ ደስታና ርካታ ብቻ ነው። ወሲብ ከማን ጋር ላድርግ? ለዚህም ርካታዬ የማንን ገላ ወይንም ሰውነት ልጠቀም? የሚለው ጥያቄ ምንም ከቁጥር የሚገባ ጉዳይ አይሆንም። ልቅ የፍትወት ፍልስፍና ወሲብን በማንኛውም ጊዜ፥ ቦታና ከማንኛውም ሰው ጋር ውጤቱ በመጨረሻ ምንም ይሁን ብቻ መፈጸም እንደሚቻል ነው የሚነግርዎት ።

የፖርኖግራፊ ችግር የሚጀምረው የሚያራምደው ጥልቀት የሌለው አስተሳሰብ ወሲብ በመተማመን በቃልኪዳንና በዕውነተኛ መሰጠት እንዲሁም እርስ በርስ በመፈቃቀድና በዕውነተኛነት መካሄድ እንዳለበት ከመቀበልና ከመተግበር ይልቅ እንደተፈለገው ልቅ በሆነ ሁኔታና ዐውድ መከናወንን ማደፋፈሩ ነው። እሳትን በእሳት ማንደጃ በተገቢው ቦታ መጠቀም ሙቀትም ሌሎችም ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ፣ ወሲብን እንደ እግዚአብሔር ሕግ በተገቢው መንገድና ዐውድ መጠቀም አስደናቂና ውብ ነው። ይህ ትክክለኛው ዐውድ ፥ ከልብ በሚዋደዱና እርስ በርስ በተቀባበሉ፥ እንደዚሁም በዕውነተኛ ፍቅርና ፈቃድ አንዳቸው ለአንዳቸው ራሳቸውን በሰጡ፥ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ አብረው ለመቆየት በወሰኑ ፥ በሁለት ወንድና ሴት መካከል ወሲብ በሚከናወንበት ጊዜ በጣም ፍጹምና ታላቅ ርካታና ደስታ ይገኝበታል።

ከፖርኖግራፊ ሱስ ነጻ ለመውጣት በቅድሚያ ይህንን ስለሚያዘጋጁት ሰዎች ቅጥፈት ማወቅ ተገቢ ነው።

ከምትመለከቱት የልቅ ፈትወት ከቶም ቢሆን የምትማሩት አንዳችም ዕውነት የለም። ከዕውነት ጋር በጣም የተቃረነ አካሄድ ስላለው ፈጽሞ ቁምነገር ሊገኝበት የሚችል ነገር አይደለም። በመሠረቱ ልቅ የወሲብ ፊልም ለገበያ ቀርቦ ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲባል የሚዘጋጅ እንጂ ፥ለትምህርት ተብሎ የሚዘጋጅ አይደለም። ስለዚህ ልቅ የወሲብ ፊልም ብዙ ውሸቶችንና ቅጥፈቶችን አቀናባብሮ የተመልካቾችን ቁጥር ማብዛት ከዛም ሽያጭን በተቻለ መጠን ማሳደግና ሰውን ሕይወቱንም ቦርሳውንም በዝብዞ ማራቆት ነው። ፖርኖግራፊ እጅግ እንደ አሸን የፈላው ፥ ስለወሲብ ስለሴቶች፥ ስለጋብቻና ስለሌሎቸም ተያያዥ ጉዳዮች ፈብርኮ በሚያወጣቸው ቅጥፈቶች ስለሚታገዝ ነው። የሰዎችን ዝንባሌ፥ አስተሳሰብና ሕይወትን ለመበከል ከሚጠቀሙባቸው ቅጥፈቶች መካከል ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋልና እንመልከታቸው።

 • ቅጥፈት ቁጥር 1 ፡- ሴቶች ከሰብዐዊነት በታች የሚገኙ ፍጡራን ናቸው፤
  ፕሌይ ቦይ ተብሎ በሚጠራው የፍትወት መቀስቀሻ መጽሔት ውስጥ ሴቶችን ትንሽ ደስ የምትል ለመጫወቻ የምትሆን ዓይነት እንስሳ አድርጎ ነው የሚያቀርባቸው፤ ፔንት ሀውስ የሚባለው መጽሔት ደግሞ ሴቶችን ለቤት ውስጥ መጫወቻና መዝናኛ የሚሆኑ ልክ እንደ ድመትና እንደውሻ እንደ ቤት ውስጥ እንስሳ አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው። ወይንም እንደው የሰው አካል አንድ ክፍል ብቻ አድርጎ ነው የሚቆጥራቸው። አንዳንድ የልቅ ፈትወት ፊልሞች ላይ ሴቶች ፊታቸው ሳይታይ ኃፍረተ ሥጋቸው ብቻ እንዲታይ በማድረግ ያቀርቧቸዋል። ይህን የሚያደርጉት ምን ዓይነት አስተሳሰብ ለማራመድ መሰላችሁ? ሴቶች ሰብዐዊ ናቸው ሆኖም ለስሜት ማርኪያና መጫወቻ አሻንጉሊት ሆነው ብቻ የተፈጠሩ ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ በሰው ህሊና ውስጥ ለመቅረጽ ነው።

 • ቅጥፈት ቁጥር 2፡- ሴቶች አንድ የስፖርት ዓይነት ናቸው፤
  አንዳንድ የስፖርት መጽሔቶች የመዋኛ ልብስ ላይ ብቻ የሚያተኩር ዕትም አላቸው። ይህም በቀላሉ የሚያሳየው ሴቶች ሰብዐውያን ሳይሆኑ በቃ ልክ እንደ አንድ የስፖርት ዓይነት እንደሚታዩ ነው። ልቅ የፍትወት ፍልስፍና ወሲብን እንደ ስፖርት ውድድር አድርጎ ያሳያል፤ በውድድርም አሸናፊና ተሸናፊ እንደሚኖር ሁሉ ወንዱ ራሱን አሸናፊ መሆኑንና አለመሆኑን እንዲመዝንበትና አሸናፊነቱን እንዲኩራራበት ያደፋፍረዋል። ስለዚህ ወንዱ ከስንት ሴት ጋር እንደተኛ ከተኛቸውም ሴቶች ጋር ያደረጋቸውን ነውሮች በማሰላሰል እንዲመሰጥና ራሱን ለዚህ ልቅ ለሆነ ልምምድ እንዲያስገዛ ለማድረግ ታስቦ ነው የተዘጋጀው። ወንዶች ማንነታቸውን የሚፈትኑትና የሚመዝኑት ስንት ሴቶችን ድል በማድረግ ወሲብን በመፈጸማቸው ይሆናል ፤ የእግዚአብሔር ቃል ክብራቸው በነውራቸው እንደሚለው ማለት ነው። ወንዶች ጥንካሬያቸውን የሚያሳዩትና የሚለኩት በሴቶች ጉልበት ላይ ነው ማለት ነው።

 • ቅጥፈት ቁጥር 3፡-ሴቶች ሸቀጦች ናቸው።
  በተለይም ማስታወቂያዎችን ይዘው የሚወጡት መጽሔቶች አንድ በጣም ዘመናዊና የቅርብ ሞዴል መኪና ሲያስተዋውቁ ከመኪናዋ ጋር አንድ በጣም ቆንጆ ሴት አብረው ያወጣሉ። ሰቲቷ መኪናውን ወይ ተደግፋ ወይንም ግር በሚያሰኝ ሁኔታ እላዩ ላይ ተቀምጣ በማሳየት መኪናቸውን ያሻሽጣሉ። ይህ ማስታወቂያ በአንደበት ያልተነገረ ወይም በጽሑፍ ያልሰፈረ መልዕክት ይዞ እንደወጣ ግን ማንም በቀላሉ ሊረዳው አይችልም። መልዕክቱ አንድ መኪና ግዙ ከመኪናው ጋር እሷንም መግዛት ትችላላችሁ። ሴቲቱ እንደ ምርቃት ነች ማለት ነው።የፖርኖግራፊ ማስታወቂያ ደግሞ ሥራቸውን ለማሻሻጥ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሴትን ስብዕና ከማጉደፍም አልፎ ቃላት በማይገኝበት ሁኔታ በማቅረብ በዚህ ንግድ ለተሰማሩና እግዚአብሔርን ለማይፈሩ ጥቂት ግለሰቦች የሃብት ምንጭ ሆነዋል። ይኸው የረከሰ አመለካከት ነው ድንበርና አየር ሳይገድበው አልፎ ተርፎ መጥቶ ዛሬም በየሃገሩ በዝሙት አዳሪነት የተሰማሩትን ሴቶች ወንዶች እንደ ሸቀጥ ገንዘብ ከፍለው በመውሰድ ከሰብዐዊነት ውጭ ሊጠቀሙባቸው የሚፈልጉት። ለምን ቢባል እንደማንኛውም ሸቀጥ ዋጋ ተከፍሎባቸዋል።

 • ቅጥፈት ቁጥር 4 ፡- የሴቶች ዋጋ ባለቸው የሰውነት ቅርጽ መስህብነት አንጻር ነው የሚለካው ፤
  በፖርኖግራፊ ገበያ አይነ ግቡ የሆነ የሰውነት ቅርጽ የሌላት ሴት ትናቃለች ፣ትጠላለች፤ እንደነዚህ ዓይነት ሴቶችን ውሾች፣ ዓሣነባሪዎች፥ አሣማዎችና ከዛም የባሰ ሥም ይሰጧቸዋል። ምክንያቱም ለልቅ ወሲብ ፊልም ንግድ እነርሱ ያወጡትን የውበት መመዘኛ ለማሟላት ስላልቻሉ ብቻ ነው እንዲህ ተብለው የሚጠሩት። ልቅ ፍትወት ስለሴቶች ክብረህሊናና ስብዕና ምንም ግድ የለውም፤ የሚፈልገው ጥሩ ገበያ ይኖረዋል ብሎ የሚያስበውን ገላዋን ብቻ ፤

 • ቅጥፈት ቁጥር 5 ፡- ሴቶች መደፈርን አጥብቀው ይፈልጋሉ፤
  የፖርኖግራፊ ዝግጀት ፍልስፍና ሴቶች «እምቢ» ማለታቸው በተዘዋዋሪ መንገድ «እሺ» ማለታቸው ነው ብሎ ነው የሚደመድመው ፤ በዚህ የፊልም ዝግጅታቸው ውስጥ ሴቶች ሲደበደቡና ሲደፈሩ፣ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ሥቃይ ሲቀበሉ ያሳያሉ፤ በመጨረሻ እነዚያው ሴቶች ያለፉበትን ሁኔታ ሁሉ ልክ እንደወደዱት አድርገው እንዲተውኑ ያደርጓቸዋል። ስለዚህ ይህ አሰራር ወንዶችን ለማዝናናትና ርካታን እንዲያገኙ ለማድረግ ሴቶችን ማሰቃየትና እንደፈለጉ ቢያደርጓቸው ምንም አይደለም የሚል መልዕክት ነው ያለው።

 • ቅጥፈት ቁጥር 6 ፡- ሴቶች መናቅ፣ መጠላትና ዝቅ ተደርገው መታየት አለባቸው፤
  ልቅ ፍትወት ፊልም በሴቶች ላይ የተደረገ ጥላቻና ንቀትን የታጀለ ንግግር የሞላበት ነው፤ በፊልሞቹ ውስጥ ሴቶች ስቃይ ይቀበላሉ፣ በንቀት ይተፋባቸዋል፣ በመቶ በሚቆጠሩ ዘግናኝ መንገዶች ክብራቸውን በሚገፍፍ ሁኔታ ይሰቃያሉ ፤ የሚያሳዝነው ግን ይህን ሥቃይ የሚቀበሉ ሴቶች የበለጠ እንዲያሰቃይዋቸውና እነዲያጎሳቁሏቸው ሲለምኑና ይህንን ጉስቁልና እንደሚወዱት አድርገው እንዲተውኑ ያስገድዷቸዋል። ይህን ሁሉ ነገር የተመለከተ ወንድ ምን ያህል ለሴቶች ክብር ይኖረዋል? ሴቶችን ከልቡ ማፍቀርስ እንዴት ይችላል? ይህ ልቅ የፍትወት ፊልም ዝግጅት ሴቶችን በዚህች ምድር ላይ እንዲጠሉና እንዲናቁ የማድረግ ዘመቻ ነው እንዴ የያዘው?

 • ቅጥፈት ቁጥር 7 ፡- ለአቅመሄዋን ያልደረሱ ሕጻናት ልቅ ፍትወትን መለማመድ አለባቸው፤
  የልቅ ፍትወት ትልቁ ገበያ የሚያተኩረው ሴቶች «ሕጻናትን» ተመስለው የሚፈጽሙት ልቅ ወሲብ ነው። ትልቅ ሴት ነች እንደ ህጻን ሴት እንድትለብስና የህጻን ዓይነት ጫማ እንድታደርግ ፣ ጸጉሯን እንደ ህጻን ሴት እንድትሰራና የህጻናት የጸጉር ጌጥ ጸጉሯ ላይ እንድትሰካ ፣ አሻንጉሊት እንድትይዝ ይደረግና ፣ ልቅ የፍትወት ፊልም እንድትተውን ትደረጋለች። ይህ ምን መልዕክት የሚያስተላልፍ ይመስላችኋል? አዋቂዎች ህጻናትን ለልቅ ፍትወት ቢጠቀሙባቸው ምንም አይደለም የሚል አይደለም? ይህ አካሄድ እነዚህ የልቅ ፍተወት ፊልም አዘጋጆች ህጻናትንም ገና ከጥዋቱ ለዚህ ገበያቸው እያዘጋጇቸው እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

 • ቅጥፈት ቁጥር 8 ፡- ሕገወጥ ወሲብ ልምምድ ደስ የሚል ጨዋታ ነው።
  ልቅ የፍትወት ፊልም ዝግጅት ሥራቸውን ይበልጥ የሚስብና በሱሷቸው የተጠመዱትን የበለጠ ለማስገበር ሲፈልጉ አብዛኛው የተውኔታቸው ታሪክ የሚያጠነጥነው ሕገወጥ ተግባርና ወንጀልን አስታክከው በመስራት ነው። ይህ ማለት ፍትወትን ማጣጣምና የበለጠ መርካት የሚቻለው በደንቡና በአግባቡ ስትፈጽመው ሳይሆን ሕገወጥ በሆነ መንገድና ከወንጀል ጋር ስትፈጽመው ነው የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ።

 • ቅጥፈት ቁጥር 9፡- ዝሙት አዳሪነት በጣም የሚስብና የሚማርክ ሥራ ነው፤
  ልቅ የፍትወት ፊልም የዝሙት አዳሪነትን አስከፊና አስነዋሪ ገጽታ በሚያብረቀርቅ ቀለማት እየቀባባው ሌሎችን እያሳተ ወደዚህ አስነዋሪ ተግባር እንዲገቡ እያደፋፈረ ነው። ሐቁ ግን ፊልም ቀባብቶ እንደሚያቀርባቸው ዓይነት አይደለም፤ ብዙዎች እንደሸቀጥ ከየአገሮች ተገዝተው በባርነት ሥርዐት ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን የሚያውቅ የለም። በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው በልቅ ፊልም ዝግጅት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነው የሚታዩት ሴቶቸ አብዛኛዎቹ በቅርብ ዘመዶቻቸውና በጎረቤቶቻቸው የመደፈር ዕጣ የደረሰባቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በግብረሥጋ ግንኙነት የተነሳ ተላላፊ በሆኑ በማይድኑ በሽታዎች የተያዙ፣ አንዳንዶቹም በያዛቸው የግብረሥጋ ግንኙነት በሽታ የተነሳ በወጣትነታቸው ሕይወታቸው ያለፈ፣ ብዙዎቹ የሚያልፉበትን አስጨናቂና አስቀያሚ ልምምድ ለመርሳት ሲሉ በኃይለኛ አደንዛዥ ዕጽ ሱሶች የተለከፉ ናቸው።

ለፖርኖግራፊ ሱስ ሰበበ መነሾዎች፤

ፖርኖግራፊ አምራች ኩባንያዎች የሴቶችን ሕይወት በማበላሸትና ወንዶችን በአደገኛ ወጥመድ ውስጥ በመክተትና በመበከል ለግምት የሚያስቸግር ትርፍን ያጋብሳሉ፤ የበለጠ ወንዶችን ለማንበርከክና ለማስገበር የሚያስችል ንድፍ በዝግጅታቸው ውስጥ ለማጠናቀር በዛው ልክ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በማውጣት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

ብዙዎቻችን በየትም ቦታ ይሁን መቼም የምንሰማቸውና የምናያቸው ነገሮች ሁሉ በኛ ላይ ተጽዕኖ እንደማያመጡ አድርገን እናስብ ይሆናል። ይህ ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዳልሆነ እገልጽላችኋለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንደምንለው ጥሩ ሙዚቃ ፥ ጥሩ መጽሐፍና ጥሩ ፊልም በሕይወታችሁ ውስጥ ሊቀሩ የሚችሉና ከድሮ አስተሳሰባችን በስንዝር ልክም ቢሆን ፈቀቅ እንዳደረጉን አንክድም። እነዚህን ነገሮች ስንሰማቸው፥ ስናነባቸውና ስናያቸው ዘና ያደርጉናል። ያስተምሩናል፤ በውስጣችን አንድ መልካምና የሚያንጽ ነገር ለመስራት እንደ ክብሪት ሆኖ የሚጭር ነገር ያስቀምጡብናል። ፖርኖግራፊ ግን ውጤቱ ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ተቃራኒ ነው። በኛም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት አሉታዊውን ተጽዕኖ ነው። ምስሎች መቼም ቢሆን በሕሊና ውስጥ ገለልተኛ መሆን አይችሉም፤ ለአንድ ክዋኔ ይገፋፉናል፤ የገበያ ጥናትና የሽያጭ ሥራ ባለሙያዎች አንድን ምርት ለማሻሻጥ በሚፈልጉበት ጊዜ ከምርቱ ጋር በተያያዘ ስሜት ውስጥ የሚከትት አንድ ምስል በማቅረብ በዚያን ወቅት መልዕክታቸውን በማስተላለፍ በሰዎች ሕሊና ውስጥ አትመው ማስቀረት እንደሚችሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የማስታወቂያ ሣይንስ ባለሙያዎች አንድን ምርት ለማስተዋወቅ ሳይንሱን ተከትለው ንድፍ ሲያወጡ የሚያዘጋጁትን ማስታወቂያ፣ ስንት ጊዜ ብትመለከቱ ማስታወቂያው በህሊናችሁ ውስጥ ቀርቶ በሚፈልጉት መጠን ግዢ እንድትፈጽሙ ለማድረግ አስቀድመው በመተንበይ ይደርሱበታል። አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች በማስታወቂያ ያዩትን ምርት ሲገዙ ምልክት የሚሰጡት የዕቃውን ሥም ሳይሆን ዕቃውን ለማስተዋወቅ የተጠቀሙበትን ምስል ነው። አይገርምም? ምናልባትም እኮ ስሙንም ልብ ብለው አልሰሙት ይሆናል! እኔም እግረ መንገዴን አንድ ጥየቄ ልጠይቃችሁ እፈልጋለሁ፤

ለመሆኑ አንድ የደነበረ በሬ ሲያባርረው የነበረው ሰው ነፍስ ይዞት ሲሮጥ የጭቃ ማጥ ውስጥ ሲገባ አስተዋዋቂው «ማምለጥ ነው የሚሻለው ለጫማው ኋላ ይታሰብለታል፤ » ብሎ ባስተዋወቀው ማስታወቂያ ላይ ፣ የየትኛው የጫማ ቀለም ማስታወቂያ ነው ብዬ ብጠይቅ ስንት ሰው መልሱን በትክክል እንደሚመልስ እርግጠኛ አይደለሁም፤ እኔ ግን ደጋግሜ ብዙዎችን ጠይቄአለሁ። ከመቶ ዘጠና አምስቱ መልሱን አልሰጡኝም ፤( በነገራችን ላይ እኔም እንዳልነግራችሁ ስሙን ረስቼዋለሁ ተምታቶብኛል፤ ኪዊ ይሁን ሉዲ ወይም ሌላ ዓይነት ቀለም ላስታውሰው አልቻልኩም። ) በአንጻሩ ምስሉን ግን መቼም ቢሆን አልረሳውም ሁሉም የቴሌቪዥን ማስታወቂያ የተከታተለ ሁሉ አይረሳውም ። የምስል ኃይል እስከዚህ ድረስ ነው።

የልቅ ፍትወት ፊልሞች በሰው በተለይ በወንድ ሕይወት ላይ የሚያደረሱት ተጽዕኖዎች ምንድናቸው?

ልቅ የፍትወት ፊልሞች በሕሊናቸን ውስጥ ማስቀመጥ የሚፈልጉት ምን ዓይነት ሃሳቦችን ነው? መጥፎ ነገር በሕሊናችን ውስጥ ልክ እንደቆሻሻ መጥቶ ከተዘረገፈ ፣ ሕሊናችን አስተሳሰቡ ሁሉ ይበከልና የጤናማ ሃሳብ ችግር እጦት ስቃይ ውስጥ እንገባለን። ሕሊና ደህንነቱ በሚገባ እንዲጠበቅ አስፈላጊ ነው የሚባለው ዋና ነገር ፥ ጤናማ በሆነ የወሲብ ሃሳብ ውስጥ መገኘት ነው። ይህ ጤናማ ሃሳብ ከውጭ ወደ ውስጥ በዘለቀ መርዛማ ሃሳብ ከተበከለ ፥አስተሳሰባችን በአንድም ሆነ በተለያየ አቅጣጫ መጣመሙ አይቀሬ ነው። የአስተሳሰባችን አካሄድ የሚቃኘውም ከዛ አንጻር ይሆንና እንቸገራለን።

የልቅ ፍትወት ፊልም ሱስ፡- የልቅ ፍትወት ፊልም ጎታችነት

ልቅ የፍትወት ፊልምን ያየ ሁሉ ወዲያውኑ በሱሱ ይጠመዳል ማለት አይደለም። አንዳንዶች ቀድሞውኑ ሴትንና ወሲብን እንዲሁም ትዳርንና ልጆችን በተመለከተ የተመረዘ አስተሳሰብ በሕሊናቸው ውስጥ ተሞልተው ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ሁሉንም እንዳለ መቀበል የሚወዱ በቀላሉ ስሜታቸው ወደ ፈለገው የሚመራቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ የልቅ ፍትወት ፊልም አዘጋጅ ካምፓኒዎች እናንተ ማን ሁኑ ማን እነርሱ ግድ የላቸውም ። እነርሱ የሚፈልጉት በዚህ ሱስ ወጥመድ ውስጥ ገብታችሁ የምርቶቻቸው ጥገኛ እንድትሆኑ ብቻ ነው። ለነርሱ ትልቁ ጉዳያቸው ገበያቸውና ትርፋቸው ብቻ ነው። ዶ/ር ቮክቶር ክላይን የተባሉ ምሁር ሱስ በውስጣችን ሊያድግ የሚችልባቸውን ደረጃዎች በርከት አድርገው አስቀምጠዋል። ከነርሱም መካከል አራቱ የሚከተሉት ናቸው። በሱሱ መጠመድ፥ የሱሱ ፍላጎት ማደግ፣ ሱሱን በጣም የመላመድ ስሜትና በመጨረሻም በተግባር ውስጥ መውደቅ ናቸው። እኔ ደግሞ ከነዚህ ውጭ በልቅ የፈትወት ፊልም ሱስ ለመጠመድ ቀዳማይ ምክንያት የሚሆን ደረጃ አለ ብዬ አምናለሁ፤ በልጅነት ጊዜ ለዚህ ፊልም መጋለጥ። የሚለውን መጨመር እፈልጋለሁ። እስቲ እነዚህን ደረጃዎች በዝርዝር እንቃኛቸው።

በልጅነት ዕድሜ ለዚህ ፊልም የመጋለጥ ደረጃ
ብዙዎች በዚህ የልቅ ፍትወት ፊልም ሱስ የተጠመዱ ሰዎች ታሪካቸው ሲጠና ፡ ገና ከልጅነታቸው ጊዜ ጀምሮ ለዚህ ፊልም እይታ ስለተጋለጡ እንደሆነ ተደርሶበታል። ይህንን ልቅ የሆነ የወሲብ ፊልም ማየት የጀመሩት ገና በህጻንነታቸው ነው። የቤታቸውን ደፍ የረገጠው በሕይወታቸው ማለዳ ላይ ነው። ይህ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው።

በልቅ ፍትወት ሱስ የመጠመድ ደረጃ
በተደጋጋሚ የልቅ ፍትወት ፊልምን ማየት ስናዘወትር ፣ ፍላጎቱ የሕይወታችን አንዱ ክፍል መሆን ይጀምራል፤ ስለዚህ በዚህ ወቅት ወጥመድ ውስጥ ገብታችኋልና በቀላሉ ከወጥመዱ መላቀቅ አትችሉም።

የሱሱ እያደገ መምጣት
አንዳንድ የልቅ ፍትወት ምሥሎችን በማየት ትጀምራላችሁ፤ ቀድሞ ያ የምታዩት እንዳላስጠየፋችሁና እንዳልጠላቸሁት ሁሉ አሁን ማድነቅና ራሳችሁንም በስሜት ውስጥ መሆን ትጀምራላችሁ።

ከሱሱ ጋር በጣም የመላመድ ደረጃ
በዚህ የሱስ ደረጃ ላይ ስታዩት የሚያስደንቃችሁ ምስል ስሜት አልሰጥ እያላችሁ ትቸገራላችሁ፤ በጊዜው ስታዩት ስሜት ውስጥ ሲከታችሁ የነበረው ምስል አሁን ምንም ስሜት አልሰጣችሁ ይላል። በዚህ የተነሳ መበሳጨት መነጫነጭ ትጀምራላችሁ። የበለጠ የሚያስደንቅ ፊልም እንዲመጣላችሁ ትፈልጋላችሁ፤ በቀላሉ አታገኙም ፤ ይህም በባህርያችሁ ላይ ከባድ ለውጥ ማምጣት ይጀምራል።

የሱሱ የጡዘት ደረጃ
ይህ በወንዶች ላይ የሚታየው እጅግ በጣም የሚያስደነግጠው ደረጃ ነው። በዚህ ደረጃ በሱሱ የተጠመደው ሰው በቀጥታ ያየውን በተግባር ለመግለጽ የሚፈልግበት ደረጃ ነው። አንዳንዶች በቀጥታ ተንቀሳቃሽ ፊልሙን ሳይመለከቱ ከሥዕልና ከፕላስቲክ ምሥሎች እይታ በኋላ በቀጥታ ወደተጨባጩ ዓለም ዘው ብለው ይገባሉ። ይህም ራሰቸውን ለጥፋት ከመዳረግ ባለፈ የሌሎችንም ሕይወት ወደ ጥፋት ይልካሉ።

ፖርኖግራፊ ሱስ፡- እኔስ?

እስካሁን በዝርዝር ከተመለከትናቸው የሱስ ደረጃዎች መካከል አንዳቸውም በናንተ ሕይወት ውስጥ እንደሚታይ ምልክት ካያችሁ ፣ አሁኑኑ ከዚህ ችግር ራሳችሁን ነጻ ማውጣት ይኖርባችኋል፤ ፖርኖግራፊ አብዝቶ ሕይወታችሁን እየተቆጣጠረው ነውን? ይህንን አደገኛ ቀንበር ከላያችሁ አውርዳችሁ ለመጣል አቅዳችኋልን? ወይስ ባላቸሁበት ሁኔታ እንደዚሁ እንደተበከላችሁ መቀጠል ትፈልጋላችሁ?

የፖርኖግራፊ ሱስ፡- ታዲያ ምን ላድርግ?

የመጀመሪያው እርምጃ ፖርኖግራፊ ሱስ ጋር እያታገላችሁ እንደሆነ አምናችሁ ተቀበሉ። እመኑኝ ይህ ጉዳይ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ብዙዎች የሚያልፉበት፣ ያለፉበትና እያለፉም ያሉበት ነገር ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶች በሱሱ ተለክፈው በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በእርግጥም የሚያስደንቅ ክስተት አይደለም። የልቅ ወሲብ አምራች ኩባንያዎች አናንተን የመሳሰሉትን ለማጥመድ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ማጥፋታቸውን አትርሱ። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች እውነትም ወጥመዱ ስለያዘላቸው መደነቅ ይገባል እንዴ? በፍፁም። ምናልባትም አንዳንዶቻችሁ ከዚህ በፊት በሕይወታችሁ ባለፈ የወሲብ ትንኮሳ ምክንያት ወደዚህ ሱስ ተገፋፍታችሁ ይሆናል። ሆኖም ከዚህ በኋላ ራሳችሁን ከዚህ ቀንበር ነጻ ለማወጣት ብቻችሁን ለመታገል እንደማትችሉ ማወቅ አለባችሁ። እርዳታ ያስፈልጋችኋል።

ይህን አደገኛ የሱስ ቀንበር ከላያችሁ ላይ ለማስወገድ ሊረዳችሁ የሚችል አንድ ሰው ያስፈልጋችኋል። ምሥጢር አድርጎ ደብቆ መቆየትን ማስወገድ ይጠበቅባችኋል። አለበለዚያ ከዚህ ሱስ ለመገላገል ትቸገራላችሁ። ይህም ማለት ይህን ችግራችሁን ሁሉም ሰው ማወቅ አለበት ማለት አይደለም። ልታምኑትና የበሰለ ነው እንዲሁም መንፈሳዊና ለማማከርም የበቃ ነው የምትሉትን ሰው መርጣችሁ ችግራችሁን በግልጽና በዝርዝር ነግራችሁ አዋዩት። በተለይ የምታማክሩት ሰው በሱስ ችግር ላይ የማማከር ልምድ ያለው ቢሆን ይመረጣል።

ለመሆኑ ከፖርኖግራፊ ነጻነት ይኖር ይሆን.

ፖርኖግራፊ በተለያዩ ቅጥፈቶች ነው የሚያስቱን። በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ ደግሞ በእውነት መንገድ ይመራናል። ኢየሱስም አለ፡- «እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በዕውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ። እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል። አላቸው »1 ኢየሱስን የሰሙት ሰዎች ይህ አባባሉ አስቀየማቸው ለመከራከርም ፈለጉና እንዲህ አሉት፡- «የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ?» አሉት።2 ኢየሱስም ሳይሰለች እነርሱ የኃጢአት ባርያዎች እንደሆኑ ለማስረዳት አልቦዘነም ፤ እንዲህም አላቸው። «እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢዓት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢዓት ባርያ ነው፤ . .. . እንግዲህ ልጁ አርነት ቢያወጣችሁ አርነት ትወጣላችሁ »3

ኃጢዓት ባርያ ብቻ አይደለም የሚያደርገን፣ ከእግዚአብሔርም ያርቀናል። ማንም ፍጹም አይደለም። ማንም በእግዚአብሔር አይን ጻድቅ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የተነገረን እንዲህ ተብሎ ነው። «እኛ ሁላችን እንደበጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ። እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በርሱ ላይ አኖረ። »4 እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ፍርድና ቅጣት ይገባን ነበር። ሆኖም መሐሪና አፍቃሪ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ ግን ለበደላችን መፍትሄ ሰጠን። በኩነኔ ውስጥ እንዳንወድቅ የመዳኛ መንገድን አዘጋጀልን። እርሱ ራሱ በእኛ ፈንታ ቅጣታችንን ለመክፈል ወሰነ። ኢየሱስ ክርስቶስ የኦግዚአብሔር ልጅ ስለእኛ ተሰቃየ ፤ ኃጢዓታችን ይቅር ይባል ዘንድ ስለእኛ ሲል በመስቀል ላይ ሞተ። እንደተናገረውም በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ በድል ተነሣ። አሁን ከርሱ ጋር ግንኙነትን እንድንጀምር ዕድል ሰጥቶናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ አስገራሚ ቃላት መካከል ይኼኛው በጣም ይደንቀኛል። «በኃጢዓታችን ብንናዝ ኃጢዓታችንን ይቅር ሊለን ከዓመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። »5

እጅግ በጣም አስፈላጊው ግንኙነት

ውስጣችሁ ያለውን ባዶ ቦታ ለመሙላት የቅርብ አጋርን ለማግኘት ባደረጋችሁት ጥረት ፖርኖግራፊ ፈጽሞ ባዶአችሁን አይሞላም፤ እኛ በእግዚአብሔር የተፈጠርነው ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲኖረንና እርሱ የእኛ የቅርብ አጋር እንዲሆነን ነው። ይህንንም ጥልቅ የሆነው ፍቅር የተገለጸልን እንዲህ በማለት ነው።- « በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዷልና።»6 ልቅ የሆነው የፍትወት ፊልም በሰው ሕይወት ውስጥ ካደረሰው ጥፋት፣ ውድመትና መበከል ለመታደግ በአንጻሩ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ። « እኔ ሕይወት እንዲሆንላችሁ እንዲበዛላችሁም መጣሁ » አለ።7 እግዚአብሔር አምላክ ይህንን ይቅርታና ምህረት አቅርቦልናል። ይቅር እንዲላችሁና ወደ ሕይወታችሁም እንዲገባ ለመጠየቅ ትፈልጋላችሁ? አሁኑኑ ፈቃዳችሁን ግለጹለት። ይህንን ፍላጎታችሁን በቃላት ለመግለጽ ከፈለጋችሁ ከዚህ በታች ያለውን ጸሎት በመጸለይ እርሱን ጠይቁት።

« የተወደድክና የተከበርክ አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፣ ኃጢዓት በመስራት አንተን በድያለሁ። በመስቀል ላይ በመሞት ኃጢዓቴን ሁሉ ስለወሰድክልኝ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። ምህረትህን መቀበል እፈልጋለሁ። ካንተ ጋር የጠበቀና የሰመረ ግንኙነት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። የሕይወቴ ጌታና አዳኝ ሆነህ ወደ ሕይወቴ ትገባ ዘንድ እጠይቅሃለሁ። ካንተ ብቻ የሚገኝ ትክክለኛውን ሕይወት ስጠኝ። በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ሥም ፤ አሜን! »

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ዮሐ. 8፥31-32 (2) ዮሐ. 8፥-33 (3) ዮሐ. 8፥-34-35 (4) ኢሣ. 53፥6 (5) 1ኛ ዮሐ. 1፥9 (6) ዮሐ.3፥16 (7) ዮሐ.10፥10


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More