አንድ አባባል አለ። እንዲህ የሚል‹‹ ከሌሎች ውድቀት መማርን የመሰለ አሪፍ የማትረፊያ መንገድ የለም።›› እንግዲህ የዚህ ጽሁፍም ዋና ዓላማው ከዚህ የወጣ ወይንም የዘለለ አይደለም።ሴቶችንና የተቃራኒ ጾታ ግንኙነቶችን አስመልክቶ እጅግ ዋጋን ከከፈልኩ በኋላ የተማርኳቸውን እውነቶች በሚከተሉት አስር ነጥቦች እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ።
ኮሌጅ ሳለሁ እኔው ራሴ ‹‹የፍቅር ሀንግኦቨር›› ብዬ ስም ያወጣሁለት ስሜት ሰለባ ነበርሁ። ምን መሰላችሁ፤ ከሴት ጋራ በወጣሁ ምሽት ማግስት ጠዋት ይሰማኝ የነበረውን የባዶነት ስሜት ማለቴ ነው። ስለዚህ ክስተት ቲቪውም ሆነ የምታዩአቸው ፊልሞች አይነግሩአችሁም። ይሁንና በጣም የሚያጋጥም ነገር ነው። የባዶነት ስሜት ብቻም ሳይሆን የጸጸት ስሜት ሳይቀር ይሰማል።
ታዲያ ይህ የፍቅር ሀንግኦቨር ስሜት ለኔ በጣም ያልተለመደ ነገር ነበር። ምክንያቱም ኮሌጅ ሳለሁ ወሲብ ማለት ለኔ እንደ አምላኬ ያህል ስለነበር ነው። ጠዋት ቀን ምሽት ስለወሲብ እንጂ ስለሌላ አላስብም ነበር። ታዲያ ስታስቡት እንዲያ ያመለክሁት ወሲብ ለኔ ፍጹም ርካታን ባመጣልኝ ነበር።ይሁንና እንደጠበቅሁት አላመጣልኝም።
ታዲያ አንተንም እንዲህ ገጥሞህ ያውቅ ይሆን፤ የፍቅር ሀንግኦቨር ይዞህ ያውቃል? ይዞህ ከነበረ ቆም ብለህ ‹‹ ለምን እንዲህ ሆነብኝ፤ወሲብ ለእኔ እጅግ አስፈላጊ ከሆነ ለምን ባዶነትን አስከተለብኝ?›› ብለህ መጠየቅ አለብህ።
እኔ ከዚህ የተነሳ ግራ የተጋባሁ ጊዜ የደረስኩበት ድምዳሜ ታዲያ ‹‹ ብዙ ሴክስ ብፈጽም ርካታው ይመጣል!›› የሚል ነበር። ግን ባዶነቱ ቀጠለ እንጂ አልጠፋም። በስተመጨረሻ ግን አንድ እውነት ገባኝ‹‹ ቅድመ ጋብቻ ወሲብ ለካስ የሚወራለትን ያህል አይደለም! ብዙ ተጋኖ ስለሚወራለት እነጂ የተባለውን ርካታ አያመጣም›› የሚል።
አንድ የገባኝ ሌላ ነገር ሴቶች ስለወሲብ ያላቸው አመለካከት ከወንዱ ፈጽሞ የተለየ መሆኑን ነው። ለምሳሌ አንዲት ሴት ለምን ከርሱ ጋር ወሲብ ፈጸምሽ ስትባል ‹‹ ስለምወደው እኮ ነው!›› ትላለች፤ ባታምንበትም እንኳ ማለት ነው። ይህ ለምን ሆነ ለምንል እንዲህ የሚል አባባል አለ፤‹‹ ሴቶች ፍቅርን ለማግኘት ወሲብን ይጠቀማሉ፤ ወንዶች ግን ወሲብን ለማግኘት ፍቅርን ይጠቀማሉ ! ››
ሴቷ ወሲብን ስትፈጽም የምታልመው አንድ ቀን ይህን ሰው አገባዋለሁ እያለች ሲሆን ወንዱ ግን ከመቼው ማድረግ የፈለገውን ሁሉ አድርጎ ለጓደኞቹ ሄዶ እስከሚያወራ ድረስ ነው የሚያልመው። ልክ እየሰራ እንዳልሆነ ህሊናው ያውቀዋል፤ ግን ማድረጉን ይቀጥላል። ለምን ቢባል ለሥጋዊ ርካታው ሲል! ሌላም ምክንያት ግን አለው፤ የወንድነት መገለጫም እንደሆነ ያስባል። ግን ሴትን ማታለል እንዴት ወንድነት ሊባል ይችላል!
አንድ አሁን የደረስኩበት እውነት ቢኖር ሴትን አከበርካት ማለት ራስህን አከበርክ ማለት ነው። ለምን አንድ ቀን ሁሉ ካለፈ በኋላ መጸጸት አይቀርም። ጸጸቱ ደግሞ ከደስታው ይልቅ ለረጅም ጊዜ አብሮን የሚቆይ ነው። ‹‹ሮብ ሮይ›› በተሰኘው ፊልም ላይ ዋናውን ገጸባህርይ የሚጫወተው ተዋናይ እንዲህ ሲል ይደመጣል ‹‹ አንድ ወንድ ለራሱ የሚሰጠው ስጦታ ቢኖር ከበሬታን ነው!›› ። በልብህ ልክ እንደሆነ የምታውቀውን ወይንም ለሴቷ ይጠቅማል የምትለውን በማድረግ ሴትን ካከበርካት ራስህን ማክበርህ እንደሆነ ልታውቅ ይገባል።አብሮህ ከሚኖር ጸጸትም ለማምለጥህ ማረጋገጫ ይሆንሀል።
ለማለት የፈለግሁት ያኔ አብሬአቸው ስወጣ የነበሩ ሴቶች አብዛኞቹ ዛሬ የሌሎች ወንዶች ሚስቶች ሆነዋል። ታዲያ ዛሬ በነዚያ ወንዶች እግር ራሴን አኑሬ ሳስበው ምነው ባላደረግሁት ማለትም አብሬአቸው ባልወጣሁ ኖሮ ብዬ እቆጫለሁ።ራሴን በራሴ ምታው ምታው ይለኛል።ግን ምን ዋጋ አለው አንዴ ሆኖ አልፎአል!
በሌላ ጎኑ ሳየው ደግሞ እኔም ሳገባ ሚስቴ ከሌላ ሰው ጋር ትወጣ የነበረችና ያም ሰው የፈለገውን አድርጎባት እንደተለያት እያሰብኩ መኖሩን በጭራሽ አልፈልገውም። አንተስ ብትሆን ሚስትህ አንድ ወቅት ከሌላ ወንድ ጋር እንደነበረች ማሰብ የሚቀልህ ይመስልሐል? አያቸሁ በራስ ሲመጣ እንዴት ከባድ እንደሆነ!
ነገሩን ገፋ አድርገን ስናየው ደግሞ ሌላም ገጽታ አለው። ሴቲቱ የአንድ ወላጅ ልጅም እኮ ነች። የእኔ ሴት ልጅ ብትሆን ኖሮስ? እህቴስ ብትሆንስ? እንደእኔ ዓይነቱ ወንድ መጠቀሚያው አድርጎአት ቢተዋት እንደ ቀላል ነገር ሊቆጠር ይገባልን?
እንግዲህ ዛሬ ሴቶችን በሌላ ዓይን ማየት ጀምሬአለሁ፤ አንድ ሌላ ሰው የወደፊት ሚስት፣የሌላ ሰው ልጅ ወይንም እህት እንደሆኑ አድርገን ማሰብ እንድናከብራቸውና እንድንጠነቀቅላቸው ሊረዳን እንደሚችል ተምሬአለሁ።
ኮሌጅ ሳለሁ አንዲት የልብ ወዳጅ ነበረችኝ።የምኞቴን ዓይነት ሴት ነበር ያገኘሁት! ከርሷ ጋር የማሳልፋቸው ጊዜያት ሁሉ እጅግ ጣፋጮች ነበሩ። በቃ ተግባባን ነው የምላችሁ። ግን ታዲያ ጥቂት ቆየንና በእኔ አነሳሽነት ወሲብን መለማመድ ጀመርን።
ብዙም ሳይቆይ የመገናኘታችን ምክንያቱ ወሲብ ብቻ መሆን ጀመረ።እርሷን በይበልጥ ለመቀራረብና ለማወቅ የነበረኝ ጉጉት ሁሉ ጠፋ። ታዲያ በመቀራረብ ፈንታ መራራቅ ጀመርን። ያን ድንቅ ህብረታችንን ወሲብ ገደለው!
ሰዎች ከሰዎች ጋራ በተለያዩ ደረጃዎች ማለትም በስሜት፣በአእምሮ፣በአካልና በመንፈስ ህብረትን ያደርጋሉ። ታዲያ እኔና ጓደኛዬ በአካል በሚሆነው ግንኙነታችን ላይ ብቻ ትኩረትን ስናደርግ ሌሎቹ የግንኙነት መስመሮቻችን ተቃጠሉብን። ያን ድርጊት ሳንለማመድ ታግሰን ብንቆይ ኖሮ ርግጠኛ ነኝ ዛሬም አብረን በሆንን ነበር።
ይህ ሁኔታ እጅግ ብዙ ዎች ላይ ሲከሰት ታዝቤአለሁ። ይህ ለምን ይሆናል? ምክንያቱን ቀጥዬ አቀርበዋለሁ።
ከአንዲት ሴት ጋር ወሲብን በፈጸምኩ ጊዜ ሁሉ ሁለት ነገሮች እንደሚሆኑብኝ ታዝቤአለሁ።እንዴት እንደሚከሰቱ አለማስተዋሌ እንጂ ያልተከሰቱባቸው ጊዜያት ነበሩ ለማለት አልደፍርም።ያልኳችሁ ሁለቱ ነገሮች አንደኛው ለሴቲቱ ያለኝ ክብር መቀነሱ ( ባልፈልገውም እንኳ ማለቴ ነው) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሴቲቱ በእኔ እምነት ማጣቷ ነው(እርሷም ሳትፈልገው ማለት ነው)!
ይህ ለምን እንደሆነ አላውቅም።መሆኑን ወይንም መከሰቱን ብቻ ነው የማውቀው።ምናልባትም ስንፈጠር እንደዚያ ተደርገን ተሰርተን እንደሆነ ብዬም አስባለሁ። አንድ ነገር ግን ርግጠኛ ነኝ፤ የእኔ ብቻ ገጠመኝ አይደለም። በሌሎች ሰዎች ህይወትም ደግሞ ደግሞ ሲከሰት ዐይቻለሁኝ።ብዙዎች ከፈጸሙት ቅድመ ጋብቻ ወሲብ የተነሳ የዛሬ ትዳራቸው ለብዙ ቀውስ እንደተዳረገ ለመታዘብ ችያለሁ። አለመተማመንንና አለመከባበርን ይዘው ነው ወደትዳር ህይወት የሚገቡት! እንግዲህ መተማመንና መከባበር ደግሞለአንድ ትዳር ህልውናና ጤንነት ወሳኝ ነገሮች እንደሆኑ ልብ ይሏል!
አንድ በቅርብ የተጋቡ ባልና ሚስትን አውቃለሁ፤ በወር ከአንድ ጊዜ ያነሰ የወሲብ ህብረት ነው ያላቸው። እርሱ አያከብራትም፤ይህን በደንብ ታውቃለች።እርሷም አታምነውም።ስለዚህ ራሷን ለርሱ መስጠትን በፍጹም አትፈልግም። ይህ አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም ከምንገምተው በላይ አውነትና በጣምም የተለመደ ነው።ይሁንና ማንም ስለዚህ ጉዳይ በአደባባይ በግልጽ አይናገርምም ሆነ አያስተምርም።ቲቪ ላይ የምናያቸው ቕድመጋብቻ ፈጻሚ ጥንዶችም ስለዚህ ምንም የሚሉት ነገር የለም። በቃ ምን አለፋችሁ ሁሉ ሰው እንዳለ እያወቀ ሊናገረው የማይፈልገው እውነት ቢኖር ይሄ ነው።
ለምን ትሉ ይሆናል። መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። እኔ ለርሷ ያለኝን አክብሮት እርሷም በእኔ ያላትን እምነት እንደጠበቅን ወደ ትዳር ስለምንገባ ነው። አንድ የተማርኩት ነገር ቢኖር ሴት ልጅ ወንዱን ካላመነችው መላው እኔነቷን ልትሰጠው አትፈልግም፤ከእርሱ ጋር መሆንም ደስታን አይሰጣትም።
ውስጠ ምስጢሩ እንዲህ ነው።ሴቶች ወሲብን ተጠቅመው ፍቅርን ለማግኘት ስለሚሞክሩና ወንዶችም በፍቅር አሳብበው ወሲብን ስለሚያገኙ ከዚህ የተሳሳተ መሠረት ላይ ቆመው ወሲብን ይፈጽማሉ።ሴቲቱ ጓደኛዋን ላለማጣት ስትል ድርጊቱን መፈጸሟን ትቀጥላለች።ወንዱም ከጓደኝነታቸው ይልቅ ወሲቡን ስለሚፈልገው ህብረታቸው ይቀጥልና ልክ ጋብቻው ተሳክቶ ከተፈጸመ በኋላ ሴቲቱም የምትፈልገው ሰው እጁዋ መግባቱን ስታረጋግጥ እርሱን ለማግኘት ስትል ትፈጽም የነበረውን ወሲብ ችላ ማለት ትጀምራለች።እንዲያውም ከጋብቻ በፊት ወሲብ እናድርግ ብሎ እርሷን በመገፋፋቱ በልቧ ጥላቻና ቂምን መቋጠሯ ስለማይቀር ስለወሲብ ማሰብ እንኳ አትፈልግም።ወንዱም ቢሆን ወሲብን ለራሱ ርካታ እንጂ ከርሷ ጋር ፍጹም አንድ ለመሆን ሲል ስለማያደርገው (ይህንን ስሜቱን እርሷ በደንብ ታውቅበታለች) የተበላሸ የወሲብ ህይወት መኖርን ይያያዙታል።
ይህን ሁሉ ፈጥሬ የማወራችሁ አይምሰላችሁ።አይደለም! ዛሬ ከኮሌጅ ህይወት ወጥቻለሁ። በዙሪያዬ ብዙዎች ሲያገቡ እያየሁ ነው።ታዲያ ይህን ያልኩዋችሁን ሁሌም በብዙዎች ትዳር እየታዘብኩ አለሁ።መፍትሔው ታዲያ ምንድነው ትሉ ይሆናል፤ መልሴ ‹‹ መጠበቅ፣ መጠበቅ አሁንም እስከጋብቻ ድረስ ታግሶ መጠበቅ!!!›› የሚል አጭርና ግልጽ መልስ ነው። ታግሶ የጠበቀ ወንድ ለሚስቱ ያለው ክብር ከፍተኛ ይሆናል፤ ሚስቲቱም እንዲሁ! ስለዚህ አንዳቸው ላንዳቸው ያላቸው ፍቅር ትኩስና ከፍተኛ ስለሚሆን የወሲብ ህይወታቸውም ጣፋጭና የተሳካ ይሆናል።
ወሲብ ምስጢራዊ ነገር ነው። አልፎ አልፎ የሚደረግ ነገር እንኳ ቢሆን በሰዎች ህይወት ውስጥ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ መተሳሰርን የሚፈጥር ነገር ነው። ታዲያ ችግሩ እዚህ ጋ ነው፤ ከሌሎች ሴቶች ጋር ብዙ ውስጣዊ መተሳሰርን ፈጥሬ ካለፍኩ ከወደፊቱዋ ሚስቴ ጋራ የጠበቀ መተሳሰር እንዳይኖረኝ እንቅፋትን ፈጥሮብኝ ያልፋል።ልክ እንደ ስኮች ቴፕ ፕላስተር ማለት ነው። ስኮች ቴፕን ደጋግማችሁ የተጠቀማችሁበት ጊዜ የማጣበቅ ሐይሉ እያነሰ ሄዶ በስተመጨረሻ ከምንም ነገር ጋር መጣበቅ ያቅተዋል።
ከጋብቻ በፊት ከሌሎች ሴቶች ጋራ መጣበቅ ከጀመርኩ ከወደፊቷ ሚስቴ ጋራ እንደሚገባኝ መጣበቅ ይሣነኛል፤በርሷም ሊኖረኝ የሚገባኝ ደስታ ይቀንሳል፤የሚገባትንም ፍቅር መስጠት እቸገራለሁ። ይሁንና ዛሬ ታማኝ ሆኜ የማሳልፋት እያንዳንዲቷ ቀን ለነገዋ ሚስቴ ተገቢ ፍቅርና አክብሮትን እድሰጣት የሚያስችለኝን ግኝኙነት እንድፈጥር ይረዳኛል።
የሚገርም ነው! ማህበረሰባችን ምንዝርናን ማለትም በጋብቻ ውስጥ ያለ ዝሙትን አወግዛለሁ ይላል። በሌላ ጎን ግን ቅድመጋብቻ ወሲባዊ ግንኙነቶችን ሲኮንን አይታይም።የጊዜን ስሌት ስናወጣው ቅድመጋብቻ ወሲብ እኮ ያው ምንዝርና ማለት ነው። ምንዝርና የትዳር ህብረትን ምን ያህል እንደሚጎዳ ሁላችንም የምናውቀው ነው።ቅድመጋብቻ ወሲብ የሚያመጣው ቀውስ ግን ከዚህ ያልተናነሰ ነው።በጋብቻ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን መተሳሰርና መጣበቅ እጅጉን ይጎዳል!
ወሲብ ትዳርን ለማሟላት የተፈጠረልን ወይንም የተሠጠን ነገር እንጂ የትዳር የመጨረሻው ግብ አይደለም። እኔ የተማርኩት ነገር ይህንንም ነው። ልክ ኬክ ከተጋገረ በኋላ በስተመጨረሻ ለማሳመርና ለማጣፈጥ ብለን እንደምናለብሰው ዓይነት ክሬም ወሲብም ሌሎች የግንኙነታችን ክፍሎች ሁሉ በሚገባ የሚሰሩ ከሆነ ወሲብም ለትዳራችን ልዩ ማጣፈጫ ይሆነናል ማለት ነው። ሌሎች የግንኙነታችን ክፍሎች የሰመሩ ከሆኑ የወሲብ ህይወታችንም የተሳካ ይሆናል። ለዚህም ነው ጥሩ የወሲብ ህይወት እንዳለኝ ለማወቅ ከወደፊቷ ሚስቴ ጋራ አብሬ በመተኛት መፈተሽ የሌለብኝ! በሌሎች የግንኙነት መስመሮች የተሳካልን ከሆንን በወሲብም ጉዳይ እንዲሁ መሆኑ አይቀሬ ነው።
ሌላም ያስተዋልኩት አንድ ነገር አለ። ይኸውም ወሲብን የግንኙነቶቻችን መሰረትና መለኪያ አድርገን የምንወስደው ከሆነ የተሳካ የወሲብ ሕይወት እንዳይኖረን እንቅፋት ይሆናል።እንግዲህ አስቡበት! የፈጸምነውን ወሲብ ለግንኙነታችን ጤናማነት መለኪያ እያደረግን ሁሌም በመነጽር የምንፈትሸው ከሆነ ወዳቂ መሆናችን የማይቀር ነው። ለምን ቢባል እንድንደሰትበት የተሰጠንን ነገር በገዛ እጃችን መታሰሪያችን ስለምናደርገው ነው።
ይሁንና በሌሎች የግኝኙኘታችን መስመሮች ላይ ተግተን ከሰራንና ወሲብንም ዋና ጉዳይ ካላደረግነው ጣፋጭ የሆነ የወሲብ ህይወት እንዲኖረን የሚያስችለን መሥመር ውስጥ ገባን ማለት ነው። ስለዚህ የምንፈጽመውን ወሲብ ሁሌም አሪፍና አስደናቂ የማድረግ ግዴታ ውስጥ አንገባም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሁሌም አስደናቂ መሆን አይችልምና!
ይህን ስል ምን እያሰባችሁ እንደሆነ አውቄአለሁ። አውነቴን ነው አግኝቻለሁ። ‹ይህን› የሚበልጥ ነገር እንዳገኘው ወሲብ በተወሰነ ደረጃ ረድቶኛል ብል አልተሳሳትኩም። ያም ያገኘሁት ነገር እግዚአብሔር ነው።
ግድ የላችሁም እንደምንም ጊዜ ሰጥታችሁ አስጨርሱኝ።አጋነንክ ትሉኝ ይሆናል ግን አይደለም ስሜት የሚሰጥ ነገር ስለሆነ የምነግራችሁን እንደምንም ስሙኝ። እግዚአብሔር መጀመሪያውንም ሲሰራን ያለርሱ ሌላ ፍጹም ርካታን ሊሰጠን የሚኖር ነገር እንዳይኖር አድርጎ ነው የፈጠረን።የሰውአፈጣጠር ሥርዓት ውስጥ ይህንን ጨምሮ ነው የሰራን። አንድ ሰው ጥሩ አድርጎ እንዳስቀመጠው ‹‹ በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ እግዚአብሔር ብቻ ሊሞላው የሚችል የእግዚአብሔርን ቅርጽ የያዘ ባዶስፍራ አለ!››
ለዚህም ነው ሰዎች ሥራን፣ ጓደኞቻቸውን፣ ፋሽንንና ሌሎችንም ነገሮች ብንቀያይር እንኳ የመጨረሻውን ርካታ ማግኘት የሚሳነን።ርካታ አልሰጥ ያሉንን እንተውና ደግሞ ወደሌሎች እንዞራለን።ይሁንና ይህንኑ ርካታ ወደ ጌታ እስካልመጣን ድረስ ፈጽሞ አናገኘውም። ምክንያቱም እርሱ ብቻ ሊሰጠን የሚችለው ነገር ነውና!
እግዚአብሔር እጅግ ስለሚወደን በእርሱ እንጂ በሌላ እንድንረካ በፍጹም አይፈልግም።ለእኛ ሁሌም እጅግ የተሻለውን ነገር ያውም እርሱን ይመኝልናል።ምንም ይሁን ማንም ከእግዚአብሔር ይልቅ ጠቃሚ የሆነ የለም።እኔ ራሴ የዚህ ነገር ምስክር ነኝ። ዕቃን በመግዛት፣በወሲብ ሽርሽሮች ብዛት ሊረካና ሊሞላ ያልቻለውን ህይወቴን ገብቶ ያሳረፈኝ እግዚአብሔር ነው። በግልጽ ለመናገር ኢየሱስን ወደ ህይወቴ እንዲገባ ስጋብዘው ኢየሱስ እንዲህ አለኝ‹‹ወደ እኔ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር አይራብም፣ በእኔ የሚያምንም አይጠማም።(ዮሐ 6፤35)›› እነዚህ ቃሎች በህይወቴ እውን ሆኑ።ከጌታ ጋር ህብረት ማድረግ የጀመርኩ ዕለት በውስጤ ያለውና በእግዚአብሔር ብቻ እንዲሞላ የተሠራው ክፍተቴ ተሞላና ፍጹም የሆነ ርካታን አገኘሁ። ባዶነት ፍጹም ተሰምቶኝ አያውቅም። እግዚአብሔርን ማወቄ ከወሲብ ይልቅ እጅግ ጥልቅ የሆነ ርካታን እንደሰጠኝ አየሁ።
አሁንማ ወሲብን ከፈጸምኩ ዓመታት ተቆጠሩ። ግን ጭራሹኑ ወሲብን ሳልፈጽም እስከትዳሬ ቀን ድረስ ቆይቼ ቢሆን ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ! ግን አልችልም! ምክንያቱም ዛሬ እምቆጭባቸው ብዙ ያለፉና ጥሩ ያልሆኑ ትዝታዎች አሉኝ። ቁጭቶቼ ያኔ በወሲብ ካገኘሁት ጊዜአዊ ደስታ ይልቅ ይኸው እስከዛሬ ድረስ ያናውዙኛል። ሴት እህቶቼን እንዴት እንደተጫወትኩባቸው ሳስብ አሁን ድረስ እቆጫለሁ።ስለወደፊቱም ትዳሬ፣ ካገባሁ ማለቴ ነው፣የተሳካና የሚጸና ይሆንልኝ ይሆን ብዬም እጨነቃለሁ።እግዚአብሔር አምላክ ግን ስላለፉት ድርጊቶቼም ሆነ ስለወደፊቱ ህይወቴ እንዳልጨነቅ እየረዳኝ ነው። እኔን በመለወጥ ሂደት ላይ ነው፣ እስካሁንም ብዙ ለውጦኛል።
ያ ብቻም አይደለም። ወሲብን ለመፈጸም እስከትዳር ድረስ መቆየት የምችልበትንም አቅም እግዚአብሔር እየሠጠኝ እንዳለም አይቻለሁ። እውነት ነው አንዳንዴ ትግል አለብኝ ግን ትልቁ እግዚአብሔር እያሳለፈኝ እስካሁን አለሁ። በርሱ ዘንድ ሁሉ ይቻላል። እያንዳንዱ ቀን፣ሳምንትና ዓመት ባለፈ ቁጥር ታግሼ ከመጠበቄ የተነሳ ጥሩና የተሳካ ትዳር እንደሚኖረኝ አስባለሁ። በዚህ እንደ ወንድ ለህይወቴ እጅግ ወሳኝ በሆነ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርን በመታመኔ ከርሱ ጋራ ያለኝ ህብረት በጣም ጠንካራ ሆኖአል።
እንደባልና እንደአባት ከሰዎች ጋራ ጥሩ ግንኙነቶችን መፍጠር ከፈለግህ መሥራት ልትጀምርበት የሚገባህ ጥሩ ስፍራ ቢኖር አንተው ራስህ ጋ ነው! ምስጢሩ ትክክለኛ ሚስት ለማግኘት ወይንም ትክክለኛ የሆኑ ልጆችን ለማፍራት ቆርጦ መነሳት አይደለም። ይልቁንም ቁልፉ ከራስህ መጀመር ነው። አንተን ጥሩ ባልና አባት ሊያደርግህ የሚችል በጣም ወሳኝ የሆነ ግንኙነት ቢኖር ከእግዚአብሔር ጋራ ያለው ግንኙነትህ ነው።
እግዚአብሔር የወሲብ፣ የፍቅርና የግንኙነቶች ሁሉ ፈጣሪ ነው።እንድንደሰትባቸው ብሎ የፈጠረልን ነገሮች ናቸው።ስለአጠቃቀማቸው እርሱ ያወጣልንን ስርዓት ከተከተልን በሚገባ እንደሰትባቸዋለን።አንድ የተረዳሁት ነገር ቢኖር እግዚአብሔር የሞራል አስከባሪ በመሆን ‹‹ይህን አድርግ፣ ይህን አታድርግ!›› እያለ አለቃ ወይንም መሪ መሆኑን ለማሳየት የሚሞክር አለመሆኑን ነው። ለምሳሌ ያህል ‹‹ከጋብቻ በፊት ወሲብን አትፈጽም! ›› ሲል ለራሴ ጥቅም ብሎ ነው። እርሱ ራሱ ስለሰራኝ ለእኔ የተሻለውንና የተሟላ ደስታ ሊሠጠኝ የሚችለውን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል።
መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እየሱስ ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ በሰው አምሳል ወደ ምድር በመምጣት የእግዚአብሔርን ማንነት በግልጽ ያሳየን የእግዚአብሔር ትክክለኛ አምሳያ ነው። ባጭሩ የእግዚአብሔርን ማንነት በግልጽ አሳይቶናል። ታዲያ እንዴት ነው ከርሱ ጋራ ህብረትን መፍጠር የምንችለው?
እግዚአብሔር ለእኛ እውነተኛ ፍቅር ስላለው እንድናውቀው ይፈልጋል። ይሁንና ይህ እንዳይሆን ግን አንድ እንቅፋት አለ። ይኸውም ኀጢአታችን ( ማለትም ሰውንና እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ መውደድ አለመቻላችን) በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ጣልቃ በመግባት ህብረትን እንዳናደርግ እንቅፋትን ፈጥሮብናል።
ስለሆነም እየሱስ የእኛን ሁሉ ሐጢአት በጫንቃው ላይ በመሸከም በመስቀል ላይ በፈቃዱ ሞቶልናል።ይህን ያደረገው እኛ ፍጹም ይቅር እንድንባልና በእግዚአብሔርም ተቀባይነትን እንዲኖረን ነው። በእኛ ፈንታ በመደብደብ በመዋረድ በመገረፍና በመሰቀል ታላቅን ዋጋ ከፍሎልናል። በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ተነስቶአል።ስለዚህ ዛሬ ለዚህ ለከፈለልን ታላቅ መስዋዕት እርሱን ወደ ህይወታችን እንዲገባ በመጋበዝ ምላሽ እንድንሰጠው ይጠብቅብናል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ኖረው ካለፉ ወንዶች ሁሉ የላቀ ስብዕና የነበረው ወንድ ነበር። ሰዎች ግን ይህኛውን የማንነቱን ክፍል ብዙም ትኩረት አይሰጡትም፣ ግን በጣም እውነት የሆነ ነገር ነው። ስለዚህ ወደ ህይወትህ እንዲገባ ስትጋብዘው በምድር ላይ ከኖሩ ከማናቸውም ሰዎች ይልቅ ሰው መሆን ምን ማለት መሆኑን ጠንቕቆ የሚያውቀውን ሰው ነው እየጋበዝክ ያለኸው! ስለዚህ እውነተኛ ሰው እንድትሆን ይረዳሃል ፤ ይሁንና የሆሊውድ ፊልሞች የሚያሳዩንን ዓይነት ሰው ሳይሆን በህይወቱ ፍጹም የተሳካለትና ለሌሎችም ሕይወት ትርጉምን በመሥጠት በጣም ውድ የሆነ ህይወትን የሚኖር ዓይነት ሰው ያደርግሀል!
እውነተኛው ወንድ ምን ይመስል ይሆን ? እውነተኛ ወንድ እንደተኩላ ዓይነት ሰው አይደለም፤ የራሱ ፍላጎት መርካቱን ብቻ አያስብም። ይልቁንም እንደ እረኛ ለሌሎች ደህንነት የሚያስብ ዐይነት ባህርይ ያለው ሰው ነው። ከክርስቶስ ጋራ ያለህ ህብረት ባደገ መጠን እውነተኛ ሰው ወይንም እውነተኛ ወንድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እየተረዳህ ትመጣለህ። ክርስቶስም ስለሴቶች ያለህን አስተሣሰብና ለእነርሱ የምታደርውን ክብካቤ ይለውጠዋል።
ለዘለዓለም የሚዘልቅ ግንኙነትን ከክርስቶስ ጋራ መመስረት ትችላለህ። ‹‹ በርሱ ሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና።››ዮሐ 3፡16 እምነት ማለት መተማመን ማለት ነው።ስላንተ በተከፈለው በክርስቶስ መስዋዕት ላይ ስትተማመን የዘላለም ህይወትን ታገኛለህ፤ይህም ማለት ከእግዚአብሔር ጋራ አሁን የሚጀምርና በህይወት ዘመንህ ሁሉ የምትቀጥለው ግንኙነት ማለት ነው። አሁን በልብህ እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት ለመጀመር ፍላጎቱ ካለህ ቀጥሎ የምታገኘውን ሀሳብ በሚመችህ መንገድ ለእግዚአብሔር ከልብህ በመናገር ግንኙነቱን መጀመር ትችላለህ።
‹‹ ውድ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! በሐጢአቶቼ አንተን እንደበደልኩ አውቃለሁ። ኃጢአቶቼን ሁሉ ተሸክመህ በመስቀል ላይ ስለተሰቀልክልኝም አመሰግናለሁ።ይቅርታህን ለመቀበል እፈልጋለሁ።ካንተ ጋራ የጠበቀ ግንኙነትን መመስረት እፈልጋለሁ። ጌታዬና አዳኜ ሆነህ ወደሕይወቴ እንድትገባ እለምንሀለሁ። አንተ የምትፈልገውን ዓይነት ሰው እንድሆንልህ እባክህን እርዳኝ። አሜን!››
ተጨማሪ ምክርና ርዳታን ለማግኘትና በእግዚአብሔር ዕውቀት ለማደግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ማቴዎስ፣ ማርቆስ ፣ ሉቃስና ዮሓንስ የመሳሰሉትን ወንጌላት እንድታነብ አበረታታሀለሁ።
ሰላም !
► | ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች) |
► | ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ |
► | ጥያቄ አለኝ |